ኤርትራ የቀድሞ ሠራዊት አባላትን ለሥልጠና ስትጠራ ዜጎች ከአገር የሚወጡበትን መንገድ አጠበቀች…… Leave a comment

የኤርትራ መንግሥት የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ የክፍሎቻቸው ለዳግም ሥልጠና እንዲመለሱ እና ሌሎችም ከአገር ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዳጠበቀ በኤርትራ ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ለቢቢሲ አረጋገጡ።

በዚህ መመሪያ መሠረት ከ60 ዓመት በታች የሚገኙ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ተመዝግብው ወደ ማሠልጠኛ እንዲገቡ፤ እንዲሁም ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ ተገቢውን ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡ ያዛል።

ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው የአሥመራ ከተማ ነዋሪዎች ይህ የኤርትራ መንግሥት ትዕዛዝ በይፋ የተገለጸ አለመሆኑን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚያስረዱት ይህ ትዕዛዝ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያወቁት ከአገር ለመውጣት እና የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ቀበሌዎች በሄዱበት ወቅት በኃላፊዎች በተደረገላቸው ገለጻ ነው።

ለራሷ እና ለቤተሰቧ ደኅንነት ስትል ስሟን ያልገለጸች አንዲት በአውሮፓ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ኤርትራዊት፤ እናት እና አባቷ ሊጠይቋት ወደምትኖርበት ሀገር ለመጓዝ የመውጫ ቪዛ ጠይቀው እናቷ ሲፈቀድላቸው የቀድሞ የኤርትራ ሠራዊት አባል የሆኑት አባቷ ቪዛ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግራለች።

ይህ በአካባቢ መስተዳደሮች በኩል ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኤርትራ መንግሥት ትዕዛዝ ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም የሚመለከት በመሆኑ በነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃትን እንዳስከተለ ቢቢሲ ያናገራቸው የአገሪቱ ዜጎች ገልጸዋል።

በዋና ከተማዋ አሥመራ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች “ወቅታዊ ሁኔታን” ለማብራራት በሚል ከነዋሪዎች ጋር በተጠሩ ስብሰባዎች ላይ “ሴቶችም ጭምር” ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ መረጃዎችን እየተሰጡ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ጠቁመዋል።

በዚህ ወታደራዊ የክተት ጥሪ ያገቡ እና ልጆች ያሏቸው ሴቶች ሳይቀሩ ወደ ነበሩባቸው የጦር ክፍሎች እንዲመለሱ የታዘዙ ሲሆን፣ በኤርትራ ከሚካሄደው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ኮብልለው ተደብቀው የሚገኙ አባላትም ያለቅጣት ወደ ክፍላቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነ ተገልጿል።

እንዲሁም ከባድ ወንጀል ከፈጸሙት በስተቀር በተለያዩ ምክንያቶች እና ጥፋቶች በእስር ቤት የሚገኙ የሠራዊቱ አባላትም ተለቅቀው፤ በጥሪው መሠረት ወደነበሩባቸው የጦር ክፍሎች እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን በኤርትራ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ አመልክተዋል።

የኤርትራ መንግሥት ለዞን አስተዳደሮች ባስተላላፈው እና በቀበሌዎች አማካኝነት ተግባራዊ እየሆነ ያለው ይህ የክተት እና የሥልጠና ጥሪ፤ የሠራዊት አባላት ወደ ከክፍላቸው እንዲመለሱ የሚያዝ ሲሆን፣ በተለያዩ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ደግሞ ከአገር ሲወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ያዛል።

ቀደም ሲልም ኤርትራውያን ከአገር ለመውጣት ማሟላት የሚገቧቸው ነገሮች ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት እና የመንግሥት ፈቃድ የማግኘት ግዴታ የነበረባቸው ሲሆን፣ አሁን ግን የበለጠ መጥበቁን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከ70 ዓመት በታች የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ከ60 ዓመት በታች ሆነው ከሠራዊቱ የተሰናበቱ የቀድሞ አባላት ከአገር ለመውጣት በሚፈልጉበት ጊዜ በቅድሚያ ከአገሪቱ ሕዝባዊ ሠራዊት ጽህፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ በተላለፈው መመሪያ መሰረት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች እንዲሁም በየትኛውም ዕድሜ ሆነው ያልወለዱ ከአገር እንዳይወጡ ተከልክለዋል።

ኤርትራ ውስጥ በርካታ ሴቶች ከኢትዮጵያ፣ ቱርክ እና አረብ ኤምሬትስ አነስተኛ ሸቀጦችን በማምጣት እና ሀገር ውስጥ በመሸጥ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። የሀገሪቱ መንግስት የተላለፈው አዲሱ ክልከላ ሴቶችን ማካተቱ፤ በዚህ አይነቱ አነስተኛ የንግድ ሥራ ቤተሰባቸውን በሚያስተዳድሩ ሴቶች ላይ ስጋት መፍጠሩን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ይህ መመሪያ መጥበቁን እና ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በመደበኝነት ወደተለያዩ አገራት በመጓዝ ይነግዱ የነበሩ ሴቶች፤ የአውሮፕላን ትኬት ከቆረጡ በኋላ ከአገር መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።

የኤርትራ መንግሥት ለቀድሞ የሠራዊት አባላቱ ወደ ጦሩ እንዲመለሱ ዳግም ጥሪ ያወጣው እና ሌሎች ደግሞ ከአገር እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጉ የተሰማው ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ግንኙነት መቀዛቀዙ እየተነገረ ባለበት በወቅት ነው።

በዚህ ሳምንት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ በጻፉት አስተያየት ኤርትራ ሌላ ዙር ግጭት በቀጣናው ልትከፍት ትችላለች በሚል ከስሰው ነበር። ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ፅሁፍ ምላሽ የሰጡት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ይህንን ክስ በማስተባበል በተቃራኒው የቀጠናው ችግሮች ምንጭ ኢትዮጵያ ናት በማለት ወቅሰዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop