የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከዋልታ ቴሌቪዥን ቆይታ አድርገው ነበር።
በዚህም ወቅት ፥ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ/ም በሲስተም ችግር ምክንያት በተፈጠረው እክል ተዘርፎ የተወሰደውን ባንኩ ገንዘብ እያስመለሰ መሆኑንና ከ801 ሚሊዮን ብር የቀረው 25 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ 30 የባንኩ ሰራተኞች በግብይት ላይ መሳተፋቸውን ተከትሎ አሁን ላይ ከስራ ታግደው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ፥ ባንኩ በምን የሕግ አግባብ ነው ሰዎች ነጻ ሆኖ የመገመት መብታቸው ተጥሶ ፎቷቸው የተሰራጨው ? የሰዎችን ምስል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዴት አሰራጨ በሚል ተጠይቀዋል።
አቶ አቤ ፤ ” እኛ ዛሬም ድረስ ወንጀለኛ ናቸው የሚል ቃል አልወጣንም። ይሄን ገንዘባችንን ወስደዋል መልሱ ነው ያልነው መውሰዳቸውን 101% እናውቃለን ” ሲሉ ገልጸዋል።
” ዛሬ ያለንበት ሁኔታ እና መጀመሪያ ላይ የነበረው ይለያያል። እሁድ የነበረው ታሪክ ‘ ባንኩ ማን ብር እንደወሰደበት አያውቅም ‘ የሚል ነው በተለይ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲቀለድ ነበር እኛ ግን ‘ እናውቃለን መልሱ ስንል ‘ ነበር ምላሹ ‘ አያውቅም ‘ የሚል ነበር በኃላ 1 ሳምንት ሰጠን በተደጋጋሚ አስጠነቀቅም እንዲመልሱ ከዛ ስም እና ፎቷቸው እዲወጣ ወደማድረጉ ገባን ” ብለዋል።
” ምስል አታሰራጭ የሚል በህገ-መንግስቱ አልተገለጸም። ሲቀጥል 15 ሺህ ሰው በኮንቬንሽናል ህግ ሊፈታ የሚችል ችግር አይደለም ” ያሉት ፕሬዜዳንቱ ” naming and shaming የሚል ህግ አለ ገንዘብ የወሰደውን ሰው ስሙን አውጥቶ ያያችሁት ንገሩትና ይመልስ ነው ያልነው ” ብለዋል።
” ነጻ ሆኖ የመገመት መብቴ ተነክቷል ” የሚል ካለ ይክሰሱንና ካሳ ይጠይቁ ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አቤ ” ‘ እኔ ሰርቂያለሁ ስሜን ግን ለጥፏል ‘ የሚል ይምጣና ይክሰሰኝ ካሳውን እንከፍላለን ” ሲሉ ተናግረዋል።
” ያደረግነው ነገር በተወሰነ ደረጃ ወቀሳ ሊቀርብበት የሚችል ነገር ነው። ለችግሩ መፍትሄ ግን ያደረግነው ብቻ ነበር። ነገሩ ከህግም ከፖሊስም አቅም በላይ ነው ይሄን ሁሉ ሰው ማሰር አይችሉም፤ ፍርድ ቤት ይሄን ሁሉ ሊዳኝ አይችልም። የህግ ጥያቄ ቢነሳም ትክክለኛው መፍትሄ ያደረግነው ብቻ ነበር እሱንም አማራጭ ስላልነበረን ነው ያደረግነው ያን ማድረጋችን ህዝቡ እንዲያውቀው ሆኖ የወሰደው ሁሉ ተሰልፎ መጥቶ መለሰ ” ብለዋል።
” ገንዘቡ የህዝብ ነው እያስመለስን የቀረው ከ801 ሚሊዮን ብር 25 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው ፤ የማሰባሰቡ ስራ 96.8 በመቶ ደርሷል ” ሲሉ አሳውቀዋል።
” ምንም እንኳን ልጆች ቢያጠፉም ወላጆች መጥተው አርመዋልና የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ጨዋ ነው ፤ አሁንም አዋቂ አለ ፣ የሚያስትምር አለ፣ ሽማግሌ አለ፣ ጨዋ ወላጅ አለ ማለት እፈልጋለሁ ” ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ(@tikvahethiopia)