ኳታር በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚደረገውን የተኩስ አቁም ድርድር የአሸማጋይነት ሚናዋን እንደገና እያጤነችው ነው ሲሉ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ።
አገሪቱ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲኖር እና የእስራኤል ታጋቾችን ለማስፈታት ከግብጽ እና ከአሜሪካ ጋር በመሆን ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሼክ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል-ታኒ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር በሚሞክሩ ሰዎች ምክንያት ዶሃ “እየተበዘበዘች እና እየተበደለች ነው” ብለዋል።
አሁን እየተካሄደ ያለው የሰላም ድርድርም “አሳሳቢ ምዕራፍ ላይ ደርሷል” ሲሉ ገልጸዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማረጋገጥ የተደረገው ሙከራ ከባድ እና በአብዛኛው ያልተሳካ ቢሆንም ኳታር ሐማስን ጨምሮ ከሁሉም ወገኖች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላት ሲሆን ማንኛውንም ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ እንደሆነች ይገለጻል።
ሐማስ 40 ሴቶችን፣ ህጻናትን እና አረጋውያን ታጋቾችን የሚለቅበት የስድስት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሐሳብ በአሸማጋዮች ቢቀርብም ሐማስ በይፋ ውድቅ አድርጎታል።
ንግግሮቹ ሊሳኩ የሚችሉበትን ዕድል በግልጽ ጥያቄ ውስጥ ያስገባችው ኳታር አሁን ደግሞ የአሸማጋይነት ሚናዋን እንደገና መገምገም ጀምራለች።
ነጥብ ለማግኘት በሚፈልጉ ፖለቲከኞች ጥረቷ እየተናጋ መሆኑን ሼክ መሐመድ ገልጸዋል።
“እንደ አለመታደል ሆኖ በዚህ ድርድር ለትንሽ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በደል ሲፈጸም አይተናል” ሲሉ በዶሃ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
“ይህም ማለት ኳታር አጠቃላይ ሚናዋ እንዲገመገም ወስናለች። አሁን ድርድሩን ለመገምገም እና ተደራዳሪ ወገኖች በዚህ ሽምግልና ውስጥ እንዴት እንደሚሳተፉ እናጤናለን።”
ጠቅላይ ሚንስትሩ ማንንም በስም ባይጠቅሱም አንዳንድ የአሜሪካ ምክርቤት አባላት በሐማስ ላይ በቂ ጫና አላሳደረችም በማለት ኳታርን ተችተዋል። የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት በይፋ ውድቅ ካደረገ በኋላ፤ አሜሪካ ቡድኑን “የተኩስ አቁም እንቅፋት ነው” ስትል ከሳለች።
በእስራኤል እና በኢራን መካከል ውጥረቱ እየጨመረ መጥቶ የጋዛው ጦርነት ወደ ሰፊ ቀጠናዊ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል የሚል አዲስ ስጋት በተፈጠረበት በአሁኑ ሰዓት የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር የግጭቱን መስፋፋት በማስጠንቀቅ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና ጦርነቱን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ከሊባኖስ ግዛት ወደ ሰሜናዊ እስራኤል በተተኮሱ ጸረ ታንክ ሚሳኤሎች 14 የአገሪቱ ወታደሮች መቁሰላቸውን እና ስድስቱ የከፋ ጉዳት እንዳጋጠማቸው የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ በቅርቡ ቴል አቪቭ የሔዝቦላ አዛዦችን እና ተዋጊዎችን የገደለችበትን ጥቃት ለመበቀል በአረብ አል-አራምሼ አካባቢ ወታደራዊ ዒላማዎችን ማጥቃቱን አስታውቋል።
እንደ ሐማስ ሁሉ በእስራኤል፣ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሔዝቦላህ፤ የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ በሚባል ደረጃ ከእስራኤል ጦር ጋር ተኩስ ሲለዋወጥ ቆይቷል።
ጦርነቱ የተቀሰቀሰው መስከረም 26 ሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ግዛት ዘልቀው በመግባት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ገድለው 253 የሚሆኑትን ደግሞ አግተው ከወሰዱ በኋላ ነው።
እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት ነው በሚል በጀመረችው የማያባራ ጥቃት ከ33 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል። አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው ሲል በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።
በህዳር ወር ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ 105 ታጋቾችን ሐማስ ሲለቅ በምላሹ ደግሞ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ የነበሩ 240 ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈተዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት 133 ታጋቾች በጋዛ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል። አራቱ ከጦርነቱ በፊት የተወሰዱ ሲሆኑጨ ከ30 በላይ የሚሆኑት መሞታቸውንም አስታውቀዋል።
ሐማስ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከእስራኤል ጋር “ከባድ እና እውነተኛ” የታጋቾች ልውውጥ ስምምነት ላይ ለመስማማት ዝግጁ ነኝ መሆኑን ጠቅሶ አሁን የቀረበውን ሐሳብ ውድቅ አደረጓል ።
የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ዘላቂ የተኩስ አቁም ጥያቄውን እንደሚቀጥልበትም አረጋግጧል።
የእስራኤሉን ተደራዳሪ ቡድን እየመራ ያለው የእስራኤሉ ስለላ ተቋም ሞሳድ እሑድ ዕለት እንዳስታወቀው የሐማስ አቋም የጋዛ መሪው ያህያ ሲንዋር “የሰብዓዊ ስምምነትን እንደማይፈልግ እና ታጋቾችን የማስመለስ ውጥረቱን መጠቀሙን እንደቀጠለ መሆኑን ነው” ብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በበኩላቸው “ዋናው ነጥብ ሐማስ ያንን ስምምነት መውሰድ አለበት። ካልሆነም ለምን እንደማይወስዱት ለዓለም እና ለፍልስጤም ህዝብ ማስረዳት አለባቸው” ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት አንድ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣን ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ሐማስ በመጨረሻው የተኩስ አቁም ሐሳብ ከተቀመጡት መስፈርቶች ውስጥ አንዱን የሆነውን ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወታደሮችን ጨምሮ ከ50 ዓመት በላይ ሆናቸው እና የጤና እክል ያለባቸው ሚለውን መስፈርት የሚያሟሉ 40 ታጋቾች እንደሌለው አስታውቋል።
የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው ታጋቾቹን ለማግኘት በቂ ጊዜ እና ደህንነት ለመስጠት የተኩስ አቁም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሼክ መሐመድ አክለውም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና ጦርነቱን እንዲያቆም ጥሪ አቅርበዋል። በጋዛ ውስጥ ያሉ ሲቪሎች “ከበባ እና ረሃብ” እንደተደቀነባቸው በማስጠንቀቅ እርዳታ እንደ “ፖለቲካ መሣሪያ” ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተደገፈ አንድ መረጃ ባለፈው ወር እንዳስታወቀው 1.1 ሚሊዮን ሰዎች የከፋ ረሃብ እየተጋፈጡ ሲሆን በሰሜን ጋዛ ረሃብ ሊከሰት መቃረቡን አስታውቋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤልን የእርዳታ አቅርቦት እገዳዎች፣ የቀጠለውን ግጭት እና ስርዓት አልበኝነትን ምክንያት በማለት ተጠያቂ አድርጓል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው በጋዛ ያለውን ረሃብ አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያቀርቡትን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረገ እና እስራኤል “በሰብዓዊነት ላይ ከሚገባው በላይ እየሄደች ነው” ብሏል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከእስራኤል አሽዶድ ወደብ ወደ ጋዛ መግባቱን አስታውቋል። ረቡዕ ዕለት ደግሞ በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ክረም ሻሎም በኩል ስምንት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የጭነት መኪናዎች ዱቄት ሲያጓጉዙ ነበር ብሏል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሰባት የዎርልድ ሴንትራል ኪችን ረድኤት ሠራተኞችን መገደላቸውን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡትን ሃሳብ ለማሟላት እስራኤል ባለፈው ሳምንት በሰሜን ጋዛ ጋር አዲስ ማቋረጫ ከፍታለች።
“ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር በስልክ ከተነጋገርኩ በኋላ ሦስት ሺህ ምግብ እና ቁሳቁስ የያዙ የጭነት መኪናዎች ወደ ጋዛ ተንቀሳቅሰዋል። ይህም ከሳምንት በፊት ከነበረው ዕለታዊ መጠን ከ 50 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል” ሲሉ ባይደን ኤክስ ላይ ጽፈዋል ።
በጋዛ ትልቁ የሰብኣዊ እርዳታ ድርጅት ሆነው የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ (አንርዋ) ማክሰኞ ባወጣው ዘገባ “ወደ ጋዛ የሚገባው የሰብዓዊ አቅርቦቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ አልታየም ወይም ወደ ሰሜን ጋዛ ተደራሽነት የለውም” ብሏል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ፡-(BBC)