በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴን ለማክበር በየዓመቱ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ።
በአውሮፓውያኑ 1970 በዩናይትድ ስቴትስ የተጀመረው ይህ አከባበር አሁን በዓለም ዙሪያ ታስቦ ይውላል።
የምድር ቀን ምንድን ነው? እና መቼስ ታስቦ ይውላል?
በምድር ቀን አካባቢን የመጠበቅን አስፈላጊነት ለማጉላት ያለመ ዓለም አቀፍ ዝግጅት በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ ዛሬ ሚያዝያ 22 (ሚያዝያ 14/2016 ዓ.ም.) ይካሄዳል።
ይህ ቀን በአሜሪካው ሴናተር እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ በጌይሎርድ ኔልሰን እንዲሁም በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ተማሪ በሆነው ዴኒስ ሃይስ ነው እአአ በ1970 መታሰብ የጀመረው።
ሁለቱም በአሜሪካ ያለው የአካባቢ ጉዳት ያሳስባቸው ነበር። ለዚህም በ1969 በሳንታ ባርባራ ካሊፎርኒያ የተከሰተው የነዳጅ መፍሰስ አንደኛው ተጠቃሽ በምድር ላይ ያገጠመ ጉዳት ነው።
በዚህም ሳቢያ ሕዝቡን ለማሳተፍ እና የአካባቢ ጥበቃን ወደ አገራዊ አጀንዳነት ለመቀየር የምድር ቀን ሃሳብን ይዘው ብቅ አሉ።
የመጀመሪያው የመሬት ቀን በመላዋ አሜሪካ 20 ሚሊዮን ሰዎች ማሰባሰብ ችሎ ነበር።
እአአ በ1990 ደግሞ ዓለም አቀፍ ለመሆን በቃ። እንደ አዘጋጆቹ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ደግሞ 200 በሚጠጉ አገራት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይሳተፉበታል።
“የምድር ቀንን ማክበር ለብዙ ሰዎች የመጀመሪያው የአካባቢ ጥበቃ ተግባር ነው” ሲሉ የኧርዝዴይ.ኦርግ (earthday.org) ፕሬዝዳንት ካትሊን ሮጀርስ ተናግረዋል።
ለዘንድሮው የምድር ቀን ምን ተዘጋጀ?
ዘንድሮው መሪ ቃል “ፕላኔት እና ፕላስቲክ” የሚል ነው። ይህም የፕላስቲክ ብክለት በሰው ልጆች እና በምድራችን ደኅንነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለማስገንዘብ ነው።
ከአየር ንብረት ለውጥ እና ንፁህ የኃይል ምንጭ ጀምሮ እስከ የዛፍ ተከላ ጥቅሞች ድረስ ያሉ የተለያዩ የአካባቢ ጉዳዮች ከዚህ ቀደም ተነስተዋል።
የዘንድሮው ትኩረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዚህ ዓመት (2024) መጨረሻ ላይ ከስምምነት ይደርስበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ታሪካዊው የፕላስቲክ ስምምነት በፊት የሚካሄድ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ከ50 በላይ አገራት የፕላስቲክ ብክለትን በ2040 ማስቆም እንዲቻል ጠይቀዋል።
የምድር ቀን አዘጋጆች ግን ከዚህ የበለጠ እንዲሠራ ይፈልጋሉ። በ2040 ሁሉም የፕላስቲክ ምርቶች 60 በመቶ እንዲቀነሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰዎች በበጎፈቃደኝነት የጽዳት ሥራ እንዲያከናውኑ ወይም በፕላስቲክ ብክለት ስለሚደርሰው ጉዳት የበለጠ እንዲያውቁ አዘጋጆቹ ጠቁመዋል።
የምድር ቀን ምን አሳክቷል?
የምድር ቀን ከተጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአሜሪካ የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ተቋቋመ። የንጹህ አየር ስምምነቶችን ጨምሮ በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ሕጎች ወጥተዋል ወይም ተጠናክረዋል።
በቅርብ ጊዜ ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎችን መትከል፣ አርሶ አደሮችን በዘላቂ የግብርና ተግባራት መደገፍ እና በመላው ዓለም ስለአየር ንብረት የማስተማር ፕሮጄክቶች እየተከናወኑ ነው።
አንዳንድ ታዛቢዎች ደግሞ የአካባቢ ጉዳዮችን አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎችን እንዲሆኑ ለማድረግ የምድር ቀን ሚና እንደነበረው ይጠቅሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ኢቮ ደ ቦር “የአካባቢ ተግዳሮቶቻችንን ሕብረተሰቡ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ዝርዝሮች ውስጥ ደረጃቸው እያሽቆለቆለ ባለበት ሁኔታ እንደ ምድር ቀን ያሉ አጋጣሚዎች የረዥም ጊዜ ጥቅምን ያስታውሰናል” ብለዋል።
በ2015 (እአአ) መገባደጃ ላይ የተደረሰውን የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን በይፋ ለመፈረም የ2016 የመሬት ቀን በምሳሌታዊነት ተመርጧል ።
አገራት የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመገደብ በጋራ ሲስማሙ ያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ተቺዎች ስለ ምድር ቀን ምን ይላሉ?
አንዳንድ ተቺዎች እነዚህ ስኬቶች የተሳሳተ የለውጥ ስሜት እንዳይፈጥሩ ያስጠነቅቃሉ።
ከዓለም ሙቀት መጨመር እስከ አንዳንድ ዝርያዎች መጥፋት ድረስ ያሉ ብዙ የአካባቢ ጥበቃ ጠቋሚ ምልክቶች በሰዎች ምክንያት በፍጥነት እያሽቆለቆሉ ናቸው። እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች እነዚህን አዝማሚያዎች ለመግታት ወይም ለመቀልበስ ያስገኙት ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።
አንዳንድ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ደግሞ የምድር ቀንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምንም ለውጥ ሳይፈጥሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራቸውን ለማስተዋወቅ እየተጠቁመበት ነው ተብለው ተከሰዋል።
ይህም ‘ግሪንዎሺንግ’ (አረንጓዴ እጥበት) በመባል ይታወቃል። ይህም በአካባቢ ጥበቃ ስም የተለያዩ ጥቅሞች እና ፍላጎት ማሳካት ማለት ነው።
ለምሳሌ በአካባቢ ጥበቃ ዘመቻዎቿ የምትታወቀው ግሬታ ተንበርግ የምድር ቀን “በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ለፕላኔቷ ያላቸውን ‘ፍቅር’ የሚገልጹበት አጋጣሚ ሆኖ ሳለ፤ በተመሳሳይ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያጠፏት ነው” ስትል እአአ በ2022 በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራለች።
የምድር ቀን አዘጋጅ ሮጀርስ “አረንጓዴ እጥበት እየተፈጠረ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ይህ ደግሞ በጣም ያበሳጫል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እኛ ያመጣነው ጉዳይ ባይሆንም ግን የምድር ቀንን አንዳንዶች ለራሳቸው ጥቅም [በተሳሳተ መልኩ] ለማዋል እንደሚጠቀሙ እናውቃለን” ብለዋል።
“መንግሥታት ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እና የሚዋሹትን መቆጣጠር አለባቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )