የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች ለምን አገዛዙን ይክዳሉ? Leave a comment

ከጥቂት ወራት በፊት በኩባ የሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ወደ ደቡብ ኮሪያ በመኮብለል አገዛዙን መክዳታቸውን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት በቅርቡ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

ሰሜን ኮሪያን የከዱ ዜጎች ጉዳይ ይፋ ለመሆን በርካታ ወራትን ይፈጃል።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ሰሜን ኮሪያን ከድተው ወደ ደቡብ ኮሪያ ካቀኑ በኋላ ከማኅበረሰቡ ጋር በመደበኛነት ከመዋሃዳቸው በፊት ሥልጠናዎችን መውሰድ ስላለባቸው ነው።

በቅርቡ በኩባ ከሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ የከዱት ከፍተኛ ዲፕሎማት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ እንደነበሩ የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት (ኤንአይኤስ) ይህንን አስመልክቶ ለቢቢሲ ማረጋገጫ አልሰጠም።

ዲፕሎማቱ የ52 ዓመቱ ሪ ጊዩ እንደሆኑ የደቡብ ኮሪያው ቾሱን ኢልቦ የተሰኘው ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸዋለሁ በማለት አስነብቧል።

ኮብልለው የመጡ የሰሜን ኮሪያ ዜጎችን ወደ ማኅበረሰቡ የሚያዋህደው የደቡብ ኮሪያው የውህደት ሚኒስቴር እንደገለጸው ዲፕሎማቶችን፣ ዲያስፖራዎችን እና ተማሪዎችን ጨምሮ ወደ 10 የሚጠጉ ታዋቂ ሰሜን ኮሪያውያን ባለፈው ዓመት ከድተዋል።

ይህም ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ተገልጿል። የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች በተለምዶ የአገዛዙ ልሂቃን ተደርገው ስለሚወሰዱ የእነሱ መክዳት በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎችን እና ዘላቂነት በተመለከተ ጥያቄዎች ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።

የኤምባሲዎች መዘጋት

ዲፕሎማቶቿ እየከዱ ያስቸገሯት ሰሜን ኮሪያ በተለያዩ አገራት ያሉ በርካታ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎችን ለመዝጋት ተገዳለች።

ሰሜን ኮሪያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት እና ኤምባሲዎችን ጨምሮ ከሁለት ዓመታት በፊት በተለያዩ አገራት 53 የዲፕሎማሲ ተልዕኮ ጽህፈት ቤቶች የነበሯት ቢሆንም በዘንድሮው ዓመት የካቲት ወር ወደ 44 ወርዷል።

በቅርቡም በኔፓል፣ በስፔን፣ በአንጎላ፣ በኡጋንዳ፣ በሆንግ ኮንግ እና በሊቢያ ያሏትን የቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን እና ኤምባሲዎችን ዘግታለች።

እነዚህ ኤምባሲዎች የተዘጉት በሰሜን ኮሪያ ላይ በተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ምክንያት እንደሆነ የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ገልጿል።

ተንታኞች በበኩላቸው አገሪቱ ይህንን እርምጃ የምትወስደው እያካሄደች ባለችው አንዳንድ ነገሮችን መልሳ የማዋቀር ጥረት አካል እንደሆነ ይገልጻሉ።

“በቅርቡ የተዘጉት የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎች የተቋቋሙት በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና 1970ዎቹ ይህም ሰሜን ኮሪያ እና ደቡብ ኮሪያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምጽ ለማግኘት ሲወዳደሩ ነው” ይላሉ በኮሪያ ዩኒቨርስቲ የብሔራዊ ውህደት እና ጥምረት ተቋም ዳይሬክተር ናም ሱንግ ዎክ።

“አሁን ግን ያለው እውነታ ያ አይደለም። ሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማጠናከር የምትፈልገው ፀረ አሜሪካ አቋም ካላቸው አገራት ጋር ነው። ይህም የተባበሩት መንግሥታትን ማዕቀብ በማምለጥ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንዲያስችላት ነው” ይላሉ ዳይሬክተሩ።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት በተለያዩ አገራት የሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች ግማሹን የሥራ ማስኬጃ በግል መሸፈን ያለባቸው ሲሆን፣ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት የጣለው ማዕቀብ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ፈታኝ እንዳደረገው ነው።

በዚህ እና በተጨማሪም “ከሰሜን ኮሪያ አገዛዝ በሚደርስባቸው ጫና እየከዱ ነው” ይላሉ።

ዲፕሎማቶቹን እያጋጠሟቸው ያሉ ምጣኔ ሀብታዊ ፈተናዎችን በተመለከተ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከድተው የገቡ ሰዎች የሰጡት ምስክርነት ያስረዳል።

በቅርቡ በኩባ ከሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ የከዱት ሪ ጊዩ ከደቡብ ኮሪያው ቾሱን ጋዜጣ አድርገውት በነበረው ቆይታ የሰሜን ኮሪያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞች “ክራባት ያሰሩ ለማኞች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

ይህ አነጋገራቸው በከፍተኛ ማኅበራዊ ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚቆጠሩት ዲፕሎማቶች ምን ያህል አነስተኛ ክፍያ እንደሚከፈላቸው ያሳየ ነው።

ቅጣት ፍራቻ

በእነዚህ የፋይናንስ ችግሮች እየተፈተኑ ያሉት የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች ኃላፊነታቸው የከበደ ነው።

ሁለቱ ኮሪያዎችን ለማዋሃድ የነበረውን ዕቅድ በመሰረዝ ተቋማትን ያፈረሱት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን “የሁለቱ ኮሪያ ፖሊሲዎችን” ጠበቅ አድርገው ዲፕሎማቶቻቸው እንዲከተሉ የምርመራ እና የዲሲፒሊን እርምጃዎች እንደሚወስዱም በደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የመረጃ አገልግሎት የሰሜን ኮሪያ ተንታኝ የነበሩት ክዋክ ጂል ሰፕ ይናገራሉ።

“ዲፕሎማቶች ስጋት ያደረባቸው ሲሆን፣ የቤተሰቦቻቸውም የወደፊት ዕጣ የበለጠ የሚያሳስባቸው ሁኔታ ላይ ናቸው” ይላሉ።

ከ65 ዓመታት በኋላ ከጥቂት ወራት በፊት በኩባ እና በደቡብ ኮሪያ መካከል የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኩባ በሚገኙ የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች ላይ ጫና ሳያሳድር አልቀረም። ለረጅም ዓመታት ኩባ ከጥንት አጋሮቿ አንዷ ከሆነችው ሰሜን ኮሪያ ጎን መሆኗን ስትገልጽ ቆይታለች።

በአውሮፓውያኑ 2016 አገዛዙን የከዱት በዩናይትድ ኪንግደም የሰሜን ኮሪያ ምክትል አምባሳደር ታዬኤ ዮንግ ሆ በቅርቡ ከከዱት ሪ ጊዩ ጋር የቅርብ ባልደረባ እንደነበሩ በፌስቡክ ገልጸዋል።

“የሪ የመጨረሻ ዋነኛ ተልዕኮ የነበረው ኩባ እና ደቡብ ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ መከላከል ነበር። የአገዛዙን ትዕዛዛት ለማስፈጸም ቢሞክርም ኩባ ለደቡብ ኮሪያ ያላት ዝንባሌ እያደገ በመምጣቱ የመሳካቱ ዕድል አልነበረውም” ይላሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ በ2019 በአጭሩ በተቀጨው የአሜሪካ የሰሜን ኮሪያ የመሪዎች ስብሰባ ላይ በተሳተፉ ዲፕሎማቶች ላይ መገደል እና ከአገር መባረረን ጨምሮ የከፉ ቅጣቶች ተፈጽሞባቸዋል ተብሏል።ቴ ኦንግ-ሆየዲፕሎማሲ ክህደት አንድምታ

የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ አገዛዙን የሚከዱ ሲሆን፣ ሪፖርት የማይደረጉትን ጨምሮ ትክክለኛው ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል።

ተንታኙ ክዋክ እንደሚሉት አገዛዙን ከከዱት ቀደምቶች መካከል በኮንጎ የሰሜን ኮሪያ ኤምባሲ የመጀመሪያ ፀሐፊ የነበሩት እና በአውሮፓውያኑ 1991 ወደ ደቡብ ኮሪያ የሸሹት ቴ ኦንግ-ሆ በቀጣዮቹ ዲፕሎማቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ ይጠቁማሉ።

“የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት የሆኑት የከዱትን ታያኤን ማየት ይችላሉ። ቴ አገዛዙን ከድተው በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ተመራጭ የምክር ቤት አባል እና የገዢው ፓርቲ ጠቅላይ ምክር ቤት አባል መሆን እንደሚቻል አሳይተዋል” ይላሉ።

በተለያዩ ውጭ አገራት ተሰማርተው ለሚገኘው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማቶች አገዛዙን መክዳት ከተራ ዜጎች ጋር ሲወዳደር ቀለል ያለ ይሆናል። ነገር ግን እነሱም ቢሆኑ በሰሜን ኮሪያ ያሉ የቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት ማረጋገጥ አለመቻላቸው ፈተና ይሆንባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop