የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ……. Leave a comment

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የመሠረቱት ማዕከል ይፋ አደረገ።

የቀድሞው የለውዝ ገበሬ ከየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዚደንት በላይ የኖሩ ሲሆን ባለፈው ጥቅምት 100ኛ የልደት በዓላቸውን አክብረው ነበር።

በዓለም ዙሪያ ለዲሞክራሲ እና ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገተው የካርተር ማዕከል እሑድ ከሰዓት በኋላ በጆርጂያ ፕላይንስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል።

የዴሞክራት ፓርቲው ካርተር እአአ ከ1977 እስከ 1981 አሜሪካ በኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲያዊ ቀውሶች በተከበበችበት ወቅት በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል።

ከዋይት ሃውስ ሲወጡ ዝቅተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ቢኖርም ባከናወኑት የሰብዓዊነት ሥራ የኖቤል የሠላም ሽልማትን በማሸነፍ ስማቸውን ተክለዋል።

“አባቴ ለእኔ ብቻ ሳይሆን በሠላም፣ በሰብዓዊ መብቶች እና ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ ፍቅር ለሚያምኑ ሁሉ ጀግና ነበር” ሲሉ ልጃቸው ቺፕ ካርተር ተናግረዋል።

ካርተር ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት የጆርጂያ ግዛት ገዥ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል ሌተናንት እና ገበሬ ነበሩ። አራት ልጆች፣ 11 የልጅ ልጆች እና 14 የልጅ ልጅ ልጆች አይተዋል።

ለ77 ዓመታት በትዳር አብረዋቸው የኖሩት ባለቤታቸው ሮዛሊን ካርተር እአአ ህዳር 2023 ህይወታቸው አልፏል።

እአአ ከ2018 ከጆርጅ ኤችደብሊው ቡሽ ሞት በኋላ በህይወት ያሉ በዕድሜ ትልቁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ።

ጂሚ ካርተር እና ባለቤታቸው ሮዛሊን

ካርተር ባለፈው ዓመት ባልታወቀ ህመም ምክንያት የሚከታተሉትን ህክምናን አቁመው በምትኩ በቤት እንክብካቤ ማግኘት ጀመረው ነበር።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ዓለም “ልዩ መሪ፣ አስተዳዳሪ እና ሰብአዊ መሪ አጥታለች” ብለዋል።

ባይደን “ውድ ጓደኛዬ” እና “የመርህ፣ የእምነት እና የትህትና ሰው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። “ጥሩ ሰዎች በመሆናችን ትልቅ ህዝብ መሆናችንን አሳይቷል። ጨዋ፣ የተከበረ፣ ደፋርና ሩህሩህ፣ ትሁት እና ጠንካራ ነበሩ” ብለዋል።

“ጂሚ በመሪነት ዘመኑ ያጋጠሙት ፈተናዎች ለአገራችን ወሳኝ ጊዜ ላይ የመጡ ሲሆኑ የሁሉም አሜሪካውያን ህይወት እንዲሻሻል የተቻለውን ሁሉ አድርጓል” ሲሉ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፈዋል።

“ለዚህም ሁላችንም የምስጋና ባለዕዳ ነን” ብለዋል።

የካርተር ፕሬዚደንትነት ዘመን ስምንት አሜሪካውያን ለሞት ያበቃውን የኢራን እገታ ቀውስ ጨምሮ የኢኮኖሚ ችግሮችን እና በርካታ የውጭ ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ባደረጉት ትግል ይታወሳል።

እአአ በ1978 በመካከለኛው ምስራቅ አስደናቂ የውጭ ፖሊሲ ድል በማስመዝገብ በአሜሪካ ካምፕ ዴቪድ በግብጽ እና በእስራኤል መካከል ስምምነት እንዲፈረም አስችለዋል።

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በመተባበር ለሠላምና ለሰብአዊ መብት ሥራዎች ራሳቸውን የሰጡ የዓለም መሪዎችን ያቀፈውን ዘ ኤልደርስ የተሰኘውን ቡድንን አቋቋሙ

የፎቶው ባለመብት,Reuters

የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ

ከጂሚ ቀጥሎ የመጡት ሪፐብሊካኑን ሮናልድ ሬገንን በከፍተኛ ድምጽ ተመርጠው የጂሚ ካርት ስኬት ከሁለት ዓመት በኋላ የሩቅ ትዝታ መስሎ ነበር። የዋጋ ግሽበት እና የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን በማንሳት ፕሬዚዳንቱን እንደ ደካማ መሪ በመግለፍ ሬገን ለድል በቅተዋል።

ካርተር እአአ በ1980 በተካሄደው ምርጫ በከፍተኛ ድምጽ ተሸንፈዋል። ስድስት የአሜሪካ ግዛቶችን እና ዋሽንግተን ዲሲን ብቻ አሸንፈዋል።

ከእንዲህ ዓይነቱ ከባድ ሽንፈት በኋላ ካርተር በተደጋጋሚ በሪፐብሊካኖች የሊበራል ኢፍትሃዊነት ምሳሌ ተደርገው ይገለጹ ነበር።

ዛሬም ብዙ ቀኝ ዘመሞች የካርተርን የመሪነት ዓመታት በማንሳት ያፌዛሉ። ከዓመታት በኋላ ግን የሰብዓዊ ጥረቶቻቸው እና ቀላል የአኗኗሩ ዘዬን በመምረጣቸው በብዙ አሜሪካውያን ዘንድ አዲስ ምስል ለመፍጠር ቻሉ።

ከኋይት ሃውስ ከወጡ በኋላ ከፖለቲካ በፊት ወደ ኖሩበት እና መካከለኛ ወደሚባለው ባለሁለት መኝታ ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ የተመለሱ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ከመንበራቸው ከወረዱ በኋላ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘውን የግለ ታሪክ መጽሐፍ ህትመት ውል እና በየመድረኮቹ በመገኘት ከሚደረግ ንግግር ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል። እአአ በ2018 ለዋሽንግተን ፖስት ሃብታም መሆን እንደማይፈልጉም ተናግረዋል።

ይልቁንም የተቀረውን የህይወት ዘመናቸውን ዓለም አቀፋዊ የእኩልነት እና የበሽታ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል።

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በመተባበር ለሠላምና ለሰብአዊ መብት ሥራዎች ራሳቸውን የሰጡ የዓለም መሪዎችን ያቀፈውን ዘ ኤልደርስ የተሰኘውን ቡድንን አቋቋመዋል።

እአአ በ2002 የኖቤል የሠላም ሽልማት ሲቀበሉ (ሽልማቱን ያገኙ ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው) “በምድር ላይ በጣም አሳሳቢው እና ሁሉን አቀፍ ችግር የሆነው ሃብታም እና ድሃ በሆኑ ሰዎች መካከል እያደገ ያለው ልዩነት ነው” ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን እና ባለቤታቸው ሂላሪ ክሊንተን ባወጡት መግለጫ “ለተሻለ፣ ፍትሃዊ ዓለም ያለመታከት ሠርተዋል” ሲሉ የሰብዓዊ፣ የአካባቢና የዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን አንስተዋል።

“ፕሬዘደንት ካርተር በእምነት እየተመሩ እስከ መጨረሻው ድረስ ሌሎችን ለማገልገል ኖረዋል” ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለካርተር “ጨዋነት” አመስግነው “በጸጋ፣ በክብር፣ በፍትህ እና በመደገፍ መኖር ምን ማለት ነው የሚለውን ሁሉንም አስተምረዋል” ብለዋል።

ሪፐብሊካኑ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በበኩላቸው ካርተር “ቢሯቸውን ያከበሩ” እና “የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው ብቻ ያላበቃ ነበር” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

የቀብር ስነ-ስርዓታቸው በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚፈጸም ፕሬዝደንት ባይደን ተናግረዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop