አድናን አል-ቡርሽ ይባላል። በጋዛ ድንኳን ቀልሶ ለቢበሲ ይዘግባል። የሚላስ የሚቀመስ የለምና በቀን አንድ ጊዜ ይመገባል። የማይበላበትም ቀን አለ። ምግብ ጠፍቶ ሳይሆን በሌላ ምክንያት።
ባለቤቱንና 5 ልጆቹን ከእስራኤል የአየር ላይ መቅሰፍት ለማዳን ቀን ተሌት ላይ ታች ይላል።
ጋዜጠኛ አድናን በጋዛ በየዕለቱ ከሞት ጋር ይተናነቃል። ታሪኩን በራሱ አንደበት፦
ሞትና ሕይወት
ባለፉት 6 ወራት ክፉ ከምላቸው ምሽቶች አንዱ ከባለቤቴና ከ5 ልጆቼ ጋር በካን ዩኑስ ደጅ አስፋልት ያደርንበት ዕለት ነው።
ብርዱ የከፋ ነበር። ልጆቼን ምን እንደማደርግላቸው ግራ ገባኝ።
ከሰማይ ቦምብና ድሮን መዝነቡ ሲበረታ ወደ ፍልስጤም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቢሮ ደጅ ተንፏቀን ደረስን።
እዚያም ያው ነው። ሌሊቱን እንዲችው ድሮን ሲያንዣብብን ነጋ።
ከቀናት በኋላ ከጎዳና ተነሳን።
አንድ የሚከራይ አፓርታማ አገኘን። ገና ተከራይተን መኖር እንደጀመርን የቤቱ ባለቤት ደወለ።
ምነው? አልኩት። በፍጥነት ውጣ አለኝ።
የእስራኤል መከላከያ አፓርታማውን ሊያጋየው እንደሆነ መረጃው እንደደረሰው ነገረኝ።
ዕቃዎቻችን በፌስታል ሸክፈን ልጆቻችንን አዝለን ቶሎ ለቀን ወጣን። ከዚያ ግን ወዴት እንደምንሄድ ግራ ገባን።
ቤታችን ጃባሊያ ነበር።
ቦምቡ ሲጠናብን ጨርቄን ማቄን ሳንል ከዚያ ወጣን።
ይህን ያደረግነው የእስራኤል መከላከያ ሁሉም ሰው ከሰሜን ጋዛ ወደ ደቡብ ጋዛ እንዲሄድ ባዘዘው መሠረት ነበር።
ምን ዋጋ አለው። በደቡብ ጋዛም ሞት እንደ ጥላ ተከትሎን መጣ።
በየቀኑ የሚሰማኝ ስሜት የመዋረድ፣ የቁጣ፣ የአቅም ማጣት፣ የመሸነፍ ስሜት ነው።
የገዛ ቤተሰቤ፣ የገዛ ልጆቼን መከላከል አለመቻሌ ይነደኛል።
ጎዳና በወጣን በስንተኛው ሳምንት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ማዕከላዊ ጋዛ ኑሰይራት አንድ አፓርታማ አገኘን።
ቤተሰቤን እዚያ አስገብቼ እኔ ወደ ካን ዩኑስ ተመለስኩ። ናስር ሆስፒታል ደጅ ድንኳን ቀለስኩ።
በድንኳን ውስጥ እየኖርኩ ለቢቢሲ መዘገቤን ቀጠልኩ።
ይሁንና በየቀኑ ስለቤተሰቤ መጨነቄ አልቀረም። ሞተው ይሆን እያልኩ እብሰለሰላለሁ።
ደግሞ ክፋቱ ስልክና ኢንተርኔት በተደጋጋሚ ይቋረጣል። አንዳንድ ጊዜ ለ5 ተከታታይ ቀናት ምንም ዓይነት ግንኙነት ላይኖር ይችላል። ይህ አስጨናቂ ነው። ሞት ነው።
በካን ዩኑስ ድንኳን ውስጥ 7 የምንሆን የቢቢሲ ሠራተኞች አለን። ሁላችንም በቀን አንድ ጊዜ ነው የምንበላው።
አንዳንዴ ደግሞ ምግብ ኖሮ አንበላም። ምክንያቱ የመጸዳጃ እጦት ነው።
በዚህ ሁኔታ እየኖርኩ (መኖር ከተባለ) ከባድ መርዶ ደረሰኝ።
የአልጀዚራው ባልደረባዬ ዋል አል ዶህዶህ ቤተሰቡ እንደተገደለበት ሰማሁ።
ሚስቱ፣ ወንድ ልጁ፣ የ7 ዓመት ሴት ልጁ እና የ1 ዓመት የልጅ ልጁ በሁለት የእስራኤል የአየር ጥቃቶች ተገደሉ።
አል ዶህዶህ የ20 ዓመት ጓደኛዬ ነው።ለቅሶ ልደርሰው እንኳ አልቻልኩም።
በዚያው ሰሞን በርካታ መርዶዎች ይደርሱኝ ነበር።
የዘመድ አዝማድ ሞት በረከተ። እስከ አሁን ብቻ 200 ዘመድ ወዳጆቼን አጥቻለሁ።
ያን ቀን ሐዘኑ በረታብኝ መሰለኝ ቀጥታ ለቢቢሲ ቴሌቪዥን እየዘገብኩ አለቅስ ነበር።
እንባዬ በጎንጮቼ ላይ እንዲሁ ከፈቃዴ ውጭ ይፈሱ ነበር። በተለይ የጓደኛዬ ዋል አል ዶህዶህ የደረሰበት መሪር ሐዘን ሰበረኝ።
ለላፉት 15 ዓመታት ከጋዛ ሆኜ ዘገባ ሠርቻለሁ። እንዲህ ዓይነት ጉድ ግን ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።
ሐማስ ጥቃት የከፈተባት ዕለት
ኦክቶበር 7 ሐማስ ጥቃት ሲፈጽም ገና ማለዳ 12፡00 ሰዓት ነበር። ልጆቼን የቀሰቀሳቸው የሮኬት ፍንዳታ ነበር ።
ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ሮጬ ፎቅ ላይ ወጣሁ። ሮኬቶች ሲምዘገዘጉ ተመለከትኩ።
ሐማስ ድንበር ጥሶ ገብቶ ጥቃት ማድረሱን ስሰማ ደነገጥኩ።
ምላሹ ከዚህ ቀደም ከሆነው በብዙ የከፋ እንደሆነ ያኔውኑ ተረድቼ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ቅጥ ያጣ ይሆናል አላልኩም።
አሁን እንደ ጋዛ ጤና ጥበቃ መረጃ 34ሺህ ፍልስጤማዊያን ነው የተገደሉት።
ብቻ ከሐማስ ጥቃት በኋላ ነገሮች መልካቸውን እንደሚቀይሩ ገብቶኝ ነበር።
በ2ኛው ቀን፣ መጪው ጊዜ ስላሰጋኝ፣ ቶሎ ብዬ ገበያ ወጣሁ።
በጃባሊያ ወደማዘወትረው ትንሽዬ ሱፐር ማርኬት ሄድኩና አንዳንድ ምግቦችን ሸማመትኩ። በርካታ ሰው መጪው ጊዜ ስላሳሰበው እየሸመተ ነበር። ትርምስ አይጣል ነው።
አስቤዛ ገዝቼ ከቦታው እንደለቀቅኩ ከባድ ፍንደታ ሰማሁ። በ10 ደቂቃ ልዩነት ሱፐርማርኬቱ አፈር ሆኗል። እየሸመቱ የነበሩ 69 ሰዎች እዚያው ተቀበሩ።
የዚያች ትንሽዬ ሱፐርማርኬት ባለቤት ፊቱ አሁንም ድረስ በዐይን ሕሊናዬ ይመጣል።
ከጦርነቱ በፊት ጃባሊያ የምታምር ትንሽ ከተማ ነበረች።
ተወልጄ ያደኩባት፤ ክፉ ደጉን ያየሁባት ውብ ከተማ።
እኔና ቤተሰቤ ቀላልና ደስ የሚል ሕይወት ነበር የምንመራው። ሁሉም ነገር በቅጽበት ወደ ‘ነበር’ ተቀየረ።
ከሁሉ በላይ ሰሜን ጋዛ ካን ዩኑስን ስንለቅ የነበረው ስሜት ልብ ይነካ ነበር።
10 ሆነን በአንድ መኪና ውስጥ ታጨቅን። መንገዱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተሞልቷል። ግማሹ በጋሪ፣ ግማሹ በሎሪ።
ነፍሳቸውን ለማትረፍ በሚሞክሩ ሰዎች ይቅበዘበዛሉ። በመሀሉ ደግሞ አልፎ አልፎ ቦምብ ይወድቃል።
ሁሉም ፍልስጤማዊያን ፊት ላይ ከባድ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ይታያል።
ጉዞውን ቀጠልን።
ልጆቼ ደጋግመው “ባባ ወዴት ነው የምንሄደው?” ይሉኛል።
“ ባባ! ነገ እንመለሳለን?” ይሉኛል።
ለአንዱም ግን መልስ አልነበረኝም።
በቤታችን ጃባሊያ ጥያቸው ከመጣሁት ንብረቶች መካከል የልጆቼ የልጅነት ፎቶዎችና ከባለቤቴ ጋር ቀለበት ያሰርንበት የፎቶ አልበም ይዣቸው አለመውጣቴ ጸጸተኝ።
ያንኑ ቀን ማምሻውን ግን ቤቴ ሙሉ በሙሉ በቦምብ መውደሙን ሰማሁ። ትቢያ ሆነ።
በቅርብ ርቀት እርሻ ነበረችኝ። እሷም ነዳለች።
“የምበላው ይተናነቀኛል”
ከካን ዩኑስ ሆኜ ሥራዬን ቀጠልኩ።
ድንገት ግን የእስራኤል ጦር ከስፍራው በፍጥነት ልቀቁ አለን። ወደ ራፋህ ሂዱ ተባለ።
ራፋህ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤሞች ናቸው ያሉት። ሰው በሰው ላይ ነው የተደራረበው። የት እናርፋለን?
በተለይ የእስራኤል ጦር እየገሰገሰ መሆኑን ስንሰማ በጭንቀት ተሰቃየሁ። ቤተሰቤንና እኔ ከእንግዲህ ላንገናኝ ይሆን እያልኩ ተሸበርኩ።
ግራ ገባኝ። በትክክል ማሰብ አቆምኩ።በቃ አእምሮዬ መሥራት አቆመ።
ሥራ ማቆም አለብኝ የሚል ሐሳብ መጣብኝ። ከሞትንም ከቤተሰቦቼ ጋር አብረን ነው መሞት ያለብን ብዬ ወሰንኩ።
በዲሴምበር 11 ወደ ቤተሰቦቼ ዘንድ ሄድኩ። ልጆቼ ሲያዩኝ አንገቴ ላይ ተጠመጠሙብኝ። በሕይወት አሉ። ሌሊቱን እንዲሁ እንደተቃቀፍን አደርን።
ቤተሰቤን ይዤ ወደ ራፋህ መጣሁ። ቢቢሲም ሠራተኞቹን ወደዚያው አዛወረ።
ብዙ አሰቃቂ ክስተቶች በዐይኔ ተመልክቻለሁ። በርካታ የጅምላ መቃብሮችን አይቻለሁ።
በጥር ወር ለምሳሌ በርካታ ሬሳ መጣ።
የጓደኛዬ የአልጀዚራው ዋል አል ዳህዱህ ትልቁ ልጅ አስክሬን ስመለከት ደነገጥኩ።
ለአባቱ እንዴት ብዬ ልንገረው? ማንስ ይንገረው? ምክንያቱም በቅርብ ነው ቤተሰቡን የቀበረው።
የበኹር ልጁ ሐምዛም የአልጀዚራ ዘጋቢ ነበር። ሐምዛና ባልደረቦቹ በእስራኤል የአየር ጥቃት ነው የተገደሉት።
በጋዛ ጦርነት እስከ አሁን ከመቶ በላይ ጋዜጠኞች ተገድለዋል። በየቀኑ የምናየውና የምንሰማው ሞት ብቻ ነው።
በመጨረሻ መልካም ዜና ሰማሁ።
የቢቢሲ ሠራተኞች ቤተሰቦች ከጋዛ እንዲለቁ ተፈቀደ።
ከ4 ሳምንታት በኋላ በግብጽ ባለሥልጣናት በኩል ቤተሰባችን ከራፋህ ድንበር ማስወጣት ቻልን። እኔም ከዚያ ወጣሁ።
ይህን ማስታወሻ የምጽፈው ከኳታር ሆኜ ነው።
ይህን በምጽፍበት ወቅት በተወልኩባት ጃባሊያ ሰዎች የሚበሉት አጥተው ስቃይ ላይ ናቸው።
እኔ ግን በዚህ ሆቴል ውስጥ ያማረ ምግብ ይቀርብልኛል።
ይህን ባሰብኩ ቁጥር ምግብ አይዋሃድልኝም። የምበላው ይተናነቀኛል።
መርዝ የማላምጥ ይመስለኛል።
ወደ ጋዛ መመለስ እሻለሁ-ያ መቼ እንደሚሆን አላውቅም። ምናልባት አንድ ቀን።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ(BBC)