” የተማሪዎች ዕለታዊ የምግብ ተመን ወጪ 100 በሆነበት ማግስት አንድ ዳቦ ለቁርስ ማቅረብ ማሻሻል አይደለም ” -የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች…… Leave a comment

በትላንትናው ዕለት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከተሻሻለው የምግብ ሜኑ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው የተፈጠረ ግርግር ለተማሪዎች መጎዳት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል።

ለአለመግባባቱ መነሻ የሆነው በትምህርት ሚኒስቴር በተሻሻለው እና በሁሉም የዩኒቨርሲቲዎች ወጥነት ያለው የምግብ ሜኑ እንዲኖር የሚያዘውን መመሪያ ተከትሎ ” ዩኒቨርሲቲው አግባብ ባልሆነ መንገድ ተግባራዊ እያደረገው ነው ” በሚል ነው።

ዩኒቨርስቲው ከቅዳሜ 12/04/2017 ዓ/ም ጀምሮ አንድ ዳቦ ለቁርስ እየቀረበ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

” ከዚህ በፊት ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዕለታዊ ለቁርስ ይቀርብልን የነበረው ዳቦ ምንም እንኳን መጠኑ በጣም አነስተኛ ቢሆንም ሁለት ነበር አሁን ግን የተማሪዎች ዕለታዊ የምግብ ተመን ወጪ 100 በሆነበት ማግስት አንድ ዳቦ ለቁርስ ማቅረብ ማሻሻል አይደለም ” ሲሉ ወቅሰዋል።

በዚህ የምግብ አቅርቦት ደስተኛ ያልሆኑ የዋና ግቢ እና የዓዲ ሓቂ ግቢ ተማሪዎች ድርጊቱን በመቃወማቸው ለድብደባ እና ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የቲክቫህ ኢትዮጵያ መቐለ ቤተሰብ አባል ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ በመቐለ ዩኒቨርስቲ የአሪድ የተማሪዎች ምግብ ቤት ሰራተኛን አነጋግሯል።

እኚሁ ሰራተኛ ፤ ” ግርግሩ በቁርስ ሰዓት ነበር የጀመረው ተማሪዎቹ በቁርስ ሰዓት ሲቅርብላቸው የነበረው ሁለት ዳቦ ግራሙ ጨምሯል በማለት አንድ ዳቦ እንዲሰጣቸው ተደረገ ተማሪዎቹ ዳቦው አንድ መሆኑን እና የተጨመረ ግራም እንደሌለ ተናግረው የዩኒቨርስቲው አመራሮች እንዲያነጋግሩዋቸው ጠየቁ ” በማለት የጉዳዩን መነሻ አብራርተዋል።

” ይሁን እንጂ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መልስ ባለመስጠታቸው የተቆጡ ተማሪዎች የምግብ ጠረጴዛዎችን ፣ የምግብ ቁሳቁሶችን ፣ መስታወቶችን እና ሌሎች ነገሮች ወደ መስበር ተሸጋግረዋል በምግብ ቤቱ ሰራተኞች ላይ ግን ያደረሱት ጉዳት የለም ” ብለዋል።

በቁርስ ሰዓት በአሪድ ካምፓስ የጀመረው ግርግር ወደ ዓዲ ሓቂ ካምፓስ በመዝለቅ እስከ እራት ሰዓት ድረስ በዩኒቨርስቲ ንብረቶች ላይ ውድመት መድረሱን ተገልጿል።

የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን ወደ ካምፓሶቹ የፀጥታ አካላት መላኩ ተነግሯል።

በዚህም ሳቢያ በፓሊስ እና በተማሪዎቹ መካከል በተፈጠረ ግጭት ተማሪዎች የድብደባ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

በሁለቱ ካምፓሶች ግን ለጊዜው ግምቱ ያልተጣራ ንብረት መውደሙን ለመረዳት ተችሏል።

በመቐለ ዩኒቨርስቲ አሪድ እና ዓዲ ሓቂ ካምፓሶች  የተፈጠረው ግርግር በአሁኑ ሰዓት ሙሉ በሙሉ ቆሟል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የዩኒቨርስቲውን የኮሙኒኬሽን ኮርፓሬት ስለ ተፈጠረው ግርግር ማብራርያ እንዲስጥ ያቀረበው ጥያቄ ” የጉዳዩ መነሻ እና መድረሻ የሚመለከት ይፋዊ መግለጫ በሚድያ እስከሚሰጥ ጠብቁ የሚል ”  ምላሽ ተሰጥቶታል።

በኃላም ተቋሙ ማብራሪያ አውጥቷል።

በዚህም ፦

– በሃገር ደረጃ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሃገራዊ የምግብ ሜኑ በትምህርት ሚኒስቴር ጸድቆ ለትግበራ መላኩን ገልጿል።

– ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎች ህብረት ጋር በመነጋገር የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምግብ ሜኑን አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አመልክቷል።

– በሜኑው ላይ የሚስተካከሉ ነገሮች ካሉ ብሄራዊ  ሜኑ በይዘት እና በጀት ደረጃ እስካልተለየ ድረስ ጥያቄዎች በተማሪዎች ህብረት በኩል ቀርበው ማስተካከል እንደሚቻል አመልክቷል።

– በሃገር ደረጃ ተግባራዊ የሆነውን የምግብ ሜኑ ተቃውሞ የዩኒቨርሲቲውን መሰረተልማት ማጥፋት እና የካፊተርያ እና የጥበቃ ሰራተኞች ላይ ጉዳት ማድረስ ተማሪዎችን እንዲሁም ማህበረሰቡን እና ሃገሪቱን የሚጎዳና  ተግባር እንደሆነ ገልጿል።

– ተማሪዎች ቅሬታቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ እንዳለባቸው አሳስቧል።

ጉዳዩን በተመለከተ የመቐለ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ህብረት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ ስለመሆናቸው የሚገልጽ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው የአቋም መግለጫ ከሚመለከታቸው የማኔጅመንት አካላት ጋር በተደረገ ውይይት ያለኣግባብ የታሰሩ ተማሪዎች እንዲፈቱ እና ያለ መረጃ በተማሪዎች ላይ እርምጃ እንዳይወሰድ መወያየታቸውን ይገልጻል።

በተጨማሪም አዲሱ ሜኑ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እስከሚሆን ድረስ በነባሩ ሜኑ እንዲቀጥል ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል።

ህብረቱ ለተማሪዎች ሰላማዊ ጥያቄ ከተማሪዎች ጎን እንደሚቆም ይሁን እንጂ በዋና ግቢ ካፍቴሪያ እና በኣዲ ሓቂ ተማሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት እና ስህተት ፈጽሞ መደገም የለበትም ብሏል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (@tikvahethiopia)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop