የተከፋፈሉት የህወሓት አመራሮች ለፖለቲካ ግቦቻቸው “ኃይል ላለመጠቀም” መፈራረማቸው ተገለጸ….. Leave a comment

ክፍፍል እና እሰጣገባ ውስጥ ያሉት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች የፖለቲካ ግቦቻቸውን ለማሳካት “ኃይልን ላለመጠቀም” መፈራረማቸውን የትግራይ የሃይማኖት አባቶች ይፋ አደረጉ።

ለሁለት የተከፈለው ህወሓት አመራሮች የሆኑት የአቶ ጌታቸው ረዳ እና የዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ፊርማ ያረፈበት ይህ ሰነድ፣ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ “የበላይነት ለማረጋገጥ ወደ ማንኛውም ዓይነት የአመጽ ተግባር” እንደማይገቡ የሚገልጽ ነው።

የትግራይ ክልል የሃይማኖት አባቶች የሁለቱን የህወሓት አመራሮች የስምምነት ፊርማ ይፋ ያደረጉት ዛሬ አርብ የካቲት 7/2017 ዓ.ም. በመቀለ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የሃይማኖት አባቶች፤ ላለፈው አንድ ዓመት እሰጥ አገባ ውስጥ የቆዩትን ሁለቱን ቡድኖች ለማስማማት “ለሁለት ወራት” ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱ ፖለቲካዊ ጎራዎች “ችግሮቻቸውን እና የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሲጠይቁ፣ ሲለምኑ እና ጫና ሲያደርጉ” እንደነበረም ተናግረዋል። በዚህ ጥረት መነሻነትም ሁለቱ አካላት “የሥነ ምግባር መመሪያ” የተሰኘ ሰነድ እንዲፈርሙ እንደቀረበላቸው ተጠቅሷል።

የሃይማኖት አባቶቹ፤ “ሁለቱም ‘ከአባቶቻችን ውጪ አንሆንም’ ብለው ጥያቄዎቻችንን ተቀብለዋል” ሲሉ ሰነዱን ተቀብለው ፊርማቸውን ማኖራቸውን አስታውቀዋል። በመግለጫው ላይ የተነበበው የሰነዱ ሙሉ ይዙት እንደሚያስረዳው ሁለቱ አካላት የተፈራረሙት ከሦስት ሳምንት በፊት ጥር 12/2017 ዓ.ም. ነው።

መግለጫው ላይ የተጠቀሰው ቀን እንደሚያሳየው ሁለቱ አካላት ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት፤ በክልሉ የሚገኙ ወታደራዊ አመራሮች፤ በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ወደሚመራው የፓርቲው ክንፍ ያደላ መግለጫ ከመስጠታቸው ከሁለት ቀናት በፊት ነው።

ጥር 15/2017 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት ወታደራዊ አመራሮቹ በአቶ ጌታቸው የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በሌላ እንዲሰተካ “መወሰናቸውን” ገልጸው ነበር።

ከዚህ መግለጫ በፊት ስምምነት ላይ እንደተደረሰበት የተገለጸው ሰነድ እንደሚያሳየው፤ ሁለቱ አካላት የተፈራረሙት ለትግራይ ሕዝብ ካላቸው “የጋራ ኃላፊነት” የተነሳ እንዲሁም የሕዝቡን “ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ” ካላቸው “ኃላፊነት እና ቁርጠኝነት” እንደሆነ “በሥነ ምግባር መመሪያው” ላይ ተጠቅሷል።

በአምስት አንቀጾች የተዋቀረው “የሥነ ምግባር መመሪያው”፤ ኃይል አለመጠቀምን እንዲሁም ተንኳሽ ንግግር እና የጥላቻ ቃላት መቃወምን የተመለከቱ ክፍሎች አሉት። “ማስፈራሪያ እና አመጽ መቃወም”፣ “የሚዲያ አጠቃቀም እና የመረጃ አሰጣጥ” እንዲሁም “አፈጻጸም እና ክትትል” የሚሉትም ከሰነዱ አንቀጾች መካከል ናቸው።

በሰነዱ ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው “ኃይልን ያለመጠቀም ዋስትና” የሚለው አንቀጽ ነው። በዚህ አንቀጽ ላይ ሁለቱ አካላት “የፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ኃይል መጠቀምን እንደሚቃወሙ” አስፍሯል።

አንቀጹ፤ “ሁሉም አለመግባባቶች በሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ [መንገድ] ሕግ እና ሥርዓት ጠብቀን ለመነጋገር ቃል እንገባለን” የሚል የሁለቱ አካላት ስምምነትም ተካትቶበታል። ሁለቱም አካላት፤ “አባላቶች እና ደጋፊዎቻቸው” ወደ “አመጽ እንዲቀላቀሉ እንደማይቀሰቅሱ፣ እንደማይደግፉ፣ እና እንደማይፈቅዱ” እንደተስማሙም ተገልጿል።

ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ተስማምተውባቸዋል ተብለው ከተዘረዘሩ መርሆዎች መካከል ማስፈራራት እና አመጽን መቃወምን የሚመለከተው የሰነዱ ክፍል ይገኝበታል። በዚህ አንቀጽ መሠረት፤ መመሪያውን የተቀበሉት ሁለቱ አካላት “ማስፈራራት በማንኛውም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው” መግባባት ላይ ደርሰዋል።

የሁለቱ ቡድኖች አባላቶች እና ደጋፊዎቻች “በማንኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም የማስፈራራት ተግባር ውስጥ እንዳይገቡ” ለማድረግ “ኃላፊነት እንደሚወስዱም” በንባብ የቀረበው “የሥነ ምግባር መመሪያ” ያስረዳል።

“ፈራሚ አካላት የመደራጀታቸንን ኃይል ለማሳየት ወይም የበላይነታችንን ለማረጋገጥ ወደ ማንኛውም ዓይነት የአመጽ ተግባራት አንገባም፣ አንፈቅድም” ሲሉ በሰነዱ ቃል መግባታቸው ተገልጿል። ሁለቱ ቡድኖች በደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን “ማንኛውም ዓይነት የጥሰት አካሄድ ለመግታት አስፈላጊ እርምጃዎችን” የመውሰድ ኃላፊነትን እንደተቀበሉም ተጠቅሷል።

የሁለቱ ቡድኖች አመራሮች እንደተፈራረሙት የተገለጸው “የሥነ ምግባር መመሪያ”፤ “ተንኳሽ ንግግር እና የጥላቻ ቃላትን” መቃወምን የሚመለከት ክፍልንም ይዟል። በሰነዱ መሠረት ሁለቱ አካላት፤ “ጎጠኝነት እና ፖለቲካዊ አመለካከትን” መሠረት ያደረገ “ጥላቻ፣ አድልዎ ወይም አመጽን የሚያነሳሳ ንግግር” ከማድረግ ለመቆጠብ ተስማምተዋል።

በቡድኖቹ የሚደረግ ንግግር “በግለሰቦች ማንነት ወይም ሌሎች ማንነታዊ መለያዎችን ላይ ያተኮረ ጥቃት” እንዳይሆን የተስማሙት ሁለቱ ወገኖች፤ “በጉዳዮች ላይ ያተኮረ፣ ክብርን የጠበቀ ዴሞክራሲያዊ ንግግር እና ፖለቲካዊ ውይይቶች ለማዳበር ቃል እንገባለን” በሚል እንደተስማሙ ሰነዱ ያስረዳል።

በሰነዱ መሠረት፤ እነዚህን የሥነ ምግባር መርሆዎችን የማስፈጸም እና የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ሁለቱ አካላትን ለማቀራረብ ሲሠሩ ለቆዩት የሃይማኖት አባቶች ነው። ሁለቱ ቡድኖች የስምምነቱን ይዘቶች ጥሰው ሲገኙ “በአስቸኳይ እና በግልፅነት ለመፍታት” እንደተግባቡም ተጠቅሷል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው “የሥነ ምግባር መመሪያ” መሠረት ይህ ሰነድ ይፋ የሚደረገው ሁለቱ ተፈራራሚ አካላት በተገኙበት “አሸማጋዮች” ለሕዝብ በሚሰጡት መግለጫ አማካኝነት ነው። ይሁንና የዛሬውን መግለጫ የሰጡት ሁለቱን አካላት ሲያሸማግሉ የቆዩት የሃይማኖት መሪዎች ናቸው።

በሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት አንድኛውን የህወሓት ክንፍ የሚመሩት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌላኛውን ክንፍ የሚመሩት የፓርቲው ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን በመግለጫው ላይ አልተገኙም።

የሃይማኖት አባቶቹ፤ ከሦስት ሳምንት በፊት የተፈረመውን የስምምነት ሰነድ ይፋ ለማድረግ የዘገዩበትን ምክንያት በመግለጫው ላይ አልጠቀሱም። እስካሁን ድረስም ተፈራርመዋል ከተባሉት የህወሓት አመራሮች በኩል በይፋ የተሰጠ መግለጫ ወይም አስተያየት የለም።

ይህ ስምምነት መፈረሙ የተገለጸው በሁለቱ የህወሓት አንጃዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ያባባሰው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እና ሕጋዊነት ጉዳይን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት የሰጠው ማሳሰቢያ ተግባራዊ ባለመሆኑ በህወሓት ላይ ዕግድ መጣሉን ባስታወቀ ማግስት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ በመጠናቀቁ ለሕጋዊነት የሚያስፈልገውን ነገር እስኪያሟላ ድረስ ፓርቲውን ለሦስት ወራት ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማገዱን ሐሙስ የካቲት 5/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop