የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ በአውሮፓ ዲሞክራሲ ላይ ከፍተኛ ስጋት የጋረጡት ሩሲያ እና ቻይና ሳይሆኑ “ከውስጥ የመነጨ ነው” ሲሉ ጠንከር ያለ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
ቫንስ በጀርመኗ ሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ በሚያደርጉት ንግግር በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሊደረጉ ስለሚችሉ ውይይቶች ይጠቅሳሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
ይልቁንም ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ መንግሥታት ከእሴቶቻቸው አፈግፍገዋል፤ እንዲሁም የመራጮችን ስጋት ገሸሽ አድርገው በስደት እና በመናገር ነጻነት ላይ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ችላ ብለዋል ብለዋቸዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሚናገሩበት ወቅት በአዳራሹ ውስጥ ጸጥታ ሰፍኖ የነበረ ቢሆንም በኋላ በጉባኤው ላይ በርካታ ፖለቲከኞች ሲያወግዙ ተደምጠዋል።
የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ቫንስ የትራምፕ አስተዳደር በተደጋጋሚ የሚለውን በመጠቀም አውሮፓ “የራሷን መከላከያ ለማጠናከር በከፍተኛ ሁኔታ መንቀሳቀሰስ” አለባት ሲሉ ተናግረዋል።
የዩክሬንን ጦርነት አስመልክቶ የጠቀሱት ቫንስ ” ምክንያታዊ የሆነ እልባት” ሊደረስ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የየአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያስችል ንግግር ለመጀመር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ማስታወቃቸው በርካቶችን አስደንቋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዓመታዊው ጉባኤ ላይ የተለመዱት የደህንነት እና የመከላከያ ውይይቶችን አላነሱም። በአጠቃላይ ንግግራቸው በባህል ጦርነቶች ላይ እንዲሁም ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ባነሷቸው ቁልፍ ጭብጦች ላይ ያተኮረ ነበር።
የአውሮፓ ህብረት አመራሮችን የመናገር ነጻነትን እያፈኑ ነው ሲሉ ክስ አቅርበውባቸዋል። አህጉሪቱን በገፍ ለሚገቡ ስደተኞች ተጠያቂ አድርገው፤ መሪዎቹንም “ከአንዳንድ መሰረታዊ እሴቶቻቸው” እያፈገፈጉ ነው ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ፣ ቫንስ ከአሜሪካ ቅርብ የአውሮፓውያን አጋሮች ጋር “ግጭትን ለማነሳሳት እየሞከረ ነው” ሲሉ ወቅሰውታል።
በሩሲያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ማክፋውል በበኩላቸው ቫንስ የተናገሩት “ዘለፋ እና እውነትነት የሌለው ” ሲሉ ለፖለቲኮ ተናግረዋል።
ቫንስ 20 ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ዩኬን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሃገራትን እየጠቀሱ ወቅሰዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም አንድ የቀድሞ የጦር ሰራዊት አባል በጽንስ ማቋረጫ ክሊኒክ በር ላይ ላይ ተገኝቶ ጸሎት በማድረግ የማዕከሉን የተጠበቀ ዞን ጥሷል በሚል ክስ የተመሰረተበትን ግለሰብ ጉዳይ አንስተዋል።
ደህንነቱ የተጠበቀ ዞን በአውሮፓውያኑ 2022 የተደነገገ ሲሆን በጽንስ ማቋረጫ ማዕከላት የሚደረጉ ተቃውሞዎችን፣ ትንኮሳዎችን፣ እንዲሁም የሻማ ማብራትም ሆነ ሌሎች ተግባራትን ይከለክላል። ይህ ዞን የማዕከላቱን 150 ሜትር ይሸፍናል።
ቫንስ ይህንን አንስተው “በተለይም የብሪታንያ ሃይማኖተኞች መሰረታዊ ነጻነቶች” ስጋት ላይ ወድቀዋል ሲሉ ተከራክረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)