የአሜሪካ ባሕር ኃይል የእስራኤላዊያንን መርከብ አግተው የነበሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር አዋለ Leave a comment

28 ህዳር 2023

የአሜሪካ ባሕር ኃይል እሑድ ዕለት የመን ድንበር አቅራቢያ ከእሥራኤል ጋር ግንኙነት ያለውን የጭነት መርከብ አግተው የነበሩ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገለጹ። ታጣቂዎቹ በጀልባ ሊያመልጡ ቢሞክሩም የአሜሪካ የጦር መርከብ ተከታትሎ ይዟቸዋል። የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዳለው ታጣቂዎቹ ከተያዙ በኋላ በየመን የሚገኙ የሁቲ አማፂያን ሁለት ሚሳዔል ወደ ጦር መርከቡ ተኩሰዋል። የሁቲ አማፂያን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ጋር ጦርነት መግባቷን ተከትሎ ጥቃት ለማድረስ ቃል ገብተው ነበር። በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን ገድሎ 240 ደግሞ አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል የአፀፋ ጥቃት ማድረግ የጀመረችው። እስራኤል ዘመቻ ከጀመረች በኋላ በጋዛ ሰርጥ 14500 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። የሁቲ አማፂያን ራሳቸውን በኢራን የሚደገፈውየተቃዋሚዎች ክንፍአባል አድርገው አውጀዋል። ሴንትራል ፓርክ የተሰኘ ስም ያለው መርከብ እሑድ ዕለት ጥቃት እንደደረሰበት የመርከቡ ባለቤት ኩባንያ መግለጹ ይታወሳል። ሴንትራል ፓርክ፤ ዞዲያክ ማሪታይም የተባለው ኩባንያ ንብረት ሲሆን መቀመጫውን ለንደን ያደረገ በእስራኤላዊያን የሚተዳደር ዓለም አቀፍ የመርከቦች አስተዳዳሪ ነው። ዞዲያክ ማሪታይም እንደሚለው በመርከቡ ከሚገኙ 22 ሠራተኞች መካከል የሩሲያ፣ ቪየትናም፣ ቡልጋሪያ፣ ሕንድ፣ ጆርጂያ እና ፊሊፒንስ ዜጎች ይገኙበታል። የመርከቡ ዋና ካፒቴን ደግሞ የቱርክ ዜጋ ናቸው። አማፂያኑ ፎስፎሪክ አሲድ ጭኖ እየተጓዘ ያለው መርከብ ወደ የመን ወደብ የማይመጣ ከሆነ ጥቃት ለማድረስ ዝተው ነበር።

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በለቀቀው መግለጫ ዩኤስኤስ ሜሰን የተባለው ጦር መርከብ ከአጋር መርከቦች ጋር በመሆን የንግድ መርከብ እንዲለቀቅ አጋቾቹን ጠይቋል። አምስት የታጠቁ ሰዎች በአነስተኛ ጀልባ በፍጥነት ሊያመልጡ ሲሞክሩ ነው ዩኤስኤስ ሜሰን ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው። ይህ ከሆነ በኋላ ሁለት ሚሳዔሎች ወደ ጦር መርከቡ ቢተኮሱም ዒላማቸውን ሳይመቱ ቀርተዋል። የሁቲ አማፂያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።  እስራኤል ዘመቻዋን በጀመረች ወቅት በርካታ ሚሳዔሎችና ድሮኖች ወደ እስራኤል ተኩሰው ነበር። አሜሪካ እንደምትለው ሁሉም የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ቀይ ባሕር ላይ በሰፈረው የጦር መርከቧ ከሽፈዋል። ባለፈው ሳምንት የሁቲ አማፂያን ቀይ ባሕር ላይ የእስራኤል ንብረት የሆነ የጭነት መከርብ አገትን ቢሉም እስራኤል ግን መርከቡ የሷ እንዳልሆነና እስራኤላዊያን እንደማይገኙበት ተናግራለች። የየመን አማፂያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በሳዑዲ አራቢያ ከሚደገፍ የየመን መንግሥት ጋር የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop