የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ነው – የዓለም ጤና ድርጅት……. Leave a comment

በአፍሪካ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ (ኤምፖክስ) ዓለም አቀፍ አሳሳቢ ድንገተኛ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ሆኗል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አውጇል።

ቀደም ሲል የዝንጀሮ ፈንጣጣ ይባል የነበረው ተላላፊው በሽታ ኤምፖክስ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተ ወቅት ቢያንስ 450 ሰዎችን መግደሉ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው እና በምሥራቅ አፍሪካ ተሰራጭቷል። የበሽታው አዲስ ዝርያ የሚሰራጭበት ፍጥነት እና ከፍተኛ የሞት ምጣኔው ሳይንቲስቶችን አሳስቧል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በሽታው በአፍሪካ እና በሌሎች አካባቢዎች የመስፋፋት ዕድሉ “በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

“ይህን ወረርሽኝ ለማስቆም እና ሕይወትን ለመታደግ የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ምላሽ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ኤምፖክስ የሚተላለፈው በቅርብ ግንኙነት፣ ለምሳሌ በግብረ ስጋ ግንኙነት፣ በቆዳ-ለቆዳ ንክኪ እና ከሌላ ሰው ጋር በመነጋገር ወይም በመተንፈስ ነው።

ጉንፋንን የሚመስሉ ምልክቶች፣ የቆዳ ቁስሎችን ያስከትላል። ለሞት ሊዳርግም ይችላል። ከ100 ሰዎች አራቱ ለሞት የመዳረግ ዕድል አላቸው።

ክላድ 1 እና ክላድ 2 የተሰኙ ሁለት ዋና ዋና የኤምፖክስ ዓይነቶች አሉ።

ከዚህ ቀደም እአአ በ2022 ኤምፖክስ የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋ በሚል ታውጆ ነበር።

በአንፃራዊነት ቀላል በሆነው ክላድ 2 የተከሰተ ነው።

የአሁኑ ግን በጣም ገዳይ የሆነው ክላድ 1 የተሰኘው እና ቀደም ባሉት ወረርሽኞች ከታመሙት እስከ 10 በመቶ የሚሆኑትን የገደለው ዝርያ ነው በመሰራጨት ላይ የሚገኘው።

መስከረም አካባቢ በቫይረሱ ላይ ለውጥ ታይቷል። ቫይረሱ ተለውጦ ወደ ክላድ 1ቢ ተብሎ የሚጠራውን የመጣ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በፍጥነት እየተሰራጨ ይገኛል።

አንድ ሳይንቲስት ይህንን አዲስ ዝርያ “እስካሁን ካሉት በጣም አደገኛው” ብሏል።

ከጥር ወዲህ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ13 ሺህ 700 በላይ ኤምፖክስ ያለባቸው ሰዎች የታወቁ ሲሆን ቢያንስ 450 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ከዚያ በኋላም በቡሩንዲ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በኬንያ እና በሩዋንዳ ተከስቷል።

ኤምፖክስ እንደ ድንገተኛ የሕዝብ ጤና አደጋ መታወጁ ምርምር፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና አደጋ እርምጃዎችን በፍጥነት ለመውሰድ እንደሚያግዝ ተስፋ ይደረጋል።

የዌልኮም ትረስት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ጆሲ ጎልዲንግ “ጠንካራ መልዕክት ነው” ብለዋል።

የኤሞሪ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ቦጉማ ቲታንጂ በበኩላቸው እርምጃው “የቀውሱን ከባድነት ያሳያል” ሲሉ ገልጸዋል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባው ፕሮፌሰር ትሩዲ ላንግ ደግሞ “አስፈላጊ እና ወቅታዊ” ነው ብለዋል።

ነገር ግን አዲስ ዝርያ በመከሰቱ “ብዙ የማይታወቁ ነገሮች በመኖራቸውን መታረም አለበት” ሲሉ አክለዋል።

ሐምሌ 2022 ላይ ቀለል ያለው ክላድ 2 የኤምፖክስ ዝርያ አውሮፓ እና እስያን ጨምሮ ወደ 100 በሚጠጉ አገሮች ተሰራጭቷል።

ዝርያው በፍጥነት የተስፋፋ ሲሆን ከ87 ሺህ በላይ ሰዎችን ሲይዝ፤ 140 ሰዎች መሞታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አመልክቷል።

ምንም እንኳን ማንም ሰው በኤምፖክስ በሽታ ሊያዝ ቢችልም፤ ወረርሽኙ በአብዛኛው ከወንዶች ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት በፈጸሙ ወንዶች ላይ ያተኩራል።

ወረርሽኙ ለችግር የተጋለጡ ቡድኖችን በመከተብ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ማክሰኞ ዕለት የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ሳይንቲስቶች ኤምፖክስ ድንገተኛ የሕዝብ ጤና አደጋ ሲሉ አውጀዋል።

የድርጅቱ ኃላፊ ዣን ካሴያ በሽታውን ለመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“ይህንን ስጋት ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ በፍጥነት ጠንካራ ጥረት ማድረግ አለብን” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop