የጋዛ ነዋሪዎች በተኩስ አቁም ፋታው የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን እየፈለጉ ነው Leave a comment

27 ህዳር 2023

ለሳምንታት የዘለቀውን ጦርነት ለቀናት ጋብ ያዳረገው በእስራኤል እና በሐማስ የተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ አራተኛ ቀኑን ይዟል። ከመስከረም 26/2016 .. ጀምሮ ለሰባት ሳምንት ያህል የማያባራ ቦምቦች የዘነቡባት ጋዛ ላለፉት ጥቂት ቀናት እፎይታ አግኝታለች። በጋዛ ሰርጥ ያሉ ፍልስጤማውያንም ከአየር ጥቃት ስጋት በትንሹም ቢሆን ተላቀው ነዳጅ እና እርዳታ ለማግኘት ረጃጅም ወረፋዎችን ሲጠብቁ ይታያል። እነዚህ አራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታንም በአግባቡ ለመጠቀም በርካቶች የተለዩዋቸውን የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻችን ፍለጋ ላይ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት የጋዛ ሰርጥ አስፈላጊ መሠረታዊ ፍጆታዎችን ለማግኘት ይሯሯጣሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ በባሕር ዳርቻዎች ላይ በጽሞና ይራመዳሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የተቀየሩ የቀድሞ ቤቶቻቸው የነበሩበትን ስፍራዎች ጎብኝተዋል። ከፍርስራሾቹ መካከልም የተረፉ ዕቃዎች ካሉ እየፈለጉ ይገኛሉ። ለአፍታም ቢሆን ውጊያው መቆሙ በርካታ ፍልስጤማውያንን ቢያስደስትም ከሐዘን ጋር የተቀላቀለ ነው። በተለይም ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው በፍርስራሽ ክምሮች ስር ለሆኑት ደግሞ ሐዘናቸው የከፋ ነው። የተገደሉባቸውንም ከፍርስራሾች ስር አውጥተውም መቅበር እና እርማቸውን ማውጣት ይፈልጋሉ። በርካቶችም የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን በእስራኤል ጥቃቶች ከማጣታቸው በተጨማሪም ለዓመታት የለፉበት ንብረታቸው በደቂቃዎች ወድሟል። የተኩስ አቁም ፋታውን ተከትሎ በደቡባዊቷ ኻን ዩኒስ ግዛት ወደ ፍርስራሽነት ወደተቀየረው የቀድሞ ቤታቸው ከመጡት መካከል አንዷ ታሃኒ አል ናጃር አንዷ መሆኗን ሮይተርስ ዘግቧል።

58 ዓመቷ ታሃኒ ሰባት የቤተሰብ አባሎቿ በእስራኤል አየር ጥቃት ተገድለውባታል። በፍርስራሾቹ ውስጥም ጥቃቱ ያልጎዳቸውን ንብረቶች ስትፈልግ ኩባያዎችን አገኘች። እስራኤል ከሰሜናዊ ጋዛ እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ መስጠቷን ተከትሎ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውን ተፈናቅለዋል። ከእነዚህም መካከል በደቡባዊ ጋዛ ናስር ሆስፒታል ውጭ በድንኳኖች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ በርካቶች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ይጠባበቃሉ። የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ሰብለ ቱማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት መሬት ላይ ያለው ሁኔታፍጹም አስከፊመሆኑን ነው። በጋዛ እርዳታ መግባት መጀመሩን ተቋማቸው እንደ በጎ ዕድል ቢያየውም ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋል ብለዋል። መሠረታዊ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የሕክምና ግብዓቶች፣ ተጨማሪ ነዳጅ እና ምግብ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል። በርካቶች ሲሸሹ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በለበሷት ልብስ ብቻ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በአግባቡ መታጠብ ዕድልን እንዳላገኙ ገልጸዋል በርካታ የሕዝብ መጠለያዎች በተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን የተጨናነቁ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤቶች እና ማዕከላት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን ተጠልለው ይገኛሉ። የተኩስ አቁም ፋታውን ተከትሎም በከበባ ስር በምትገኘው ጋዛ ውስጥ አንዳንድ ዕቃዎች ገብተዋል ተብሏል።

ሐማስ በመስከረም መጨረሻ አስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1 ሺህ 200 ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም 240 ታጋቾች ተወስደዋል። እስራኤል ምላሽ ነው ባለችው የማያባራ የአየር ጥቃት 14 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከእነዚህም ውስጥ 40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል። የጋዛ ሰርጥ ወደ ሕጻናት የመቃብር ስፍራነት እየተቀየረችም ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋዛን አስከፊ ሁኔታ ገልጾታል። ሰባት ሳምንታትን ያስቆጠረው ጦርነት የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ፋታን አግኝቷል። በኳታር አሸማጋይነት ሐማስ እና እስራኤል ውጊያውን ለቀናት ጋብ ለማድረግ በደረሱት ስምምነት ነው ፋታ የተገኘው። በአራቱ ቀናትም ሐማስ 50 ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን፣ እስራኤል በእስር ቤቶቿ ካሉት በሺዎች ከሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መካከል 150 ሕጻናት እና ሴት ፍልስጤማውያንን የምትለቅ ይሆናል። በተኩስ አቁም ፋታው የመጀመሪያ ቀን አርብ ዕለት 150 እስከ 200 የሚደርሱ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች በግብፅ በኩል ባለው የድንበር ማቋረጫ በኩል ወደ ጋዛ ሰርጥ ገብተዋል። ይህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ጋዛ ሰርጥ የገባው ከፍተኛው የእርዳታ መጠን ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት አሁንም ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። በጋዛ የመገናኛ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል። ነገር ግን ከጋዛ ሰርጥ የሚወጡ ምሥሎች እንደሚያሳዩት በርካቶች ነዳጅ እና እርዳታዎችን ለማግኘት ረጃጅም ወረፋዎችን ሲጠብቁ ታይተዋል። ወረፋዎቹ በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው የድንበር ማቋረጫ ራፋህ ከተማም በረጅሙ ታይተዋል።

ምግብ የጫኑ ተሽከርካሪዎች፣ ውሃ፣ ነዳጅ እና የሕክምና ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪኖችም እንዲሁ ቅዳሜ ማለዳ በግብፅ በኩል ባለው የራፋህ የድንበር ማቋረጫ በኩል እየተጠባበቁ ነበር። የእስራኤል ጦር አራት ነዳጅ እንዲሁም አራት የምግብ ማብሰያዎችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ቅዳሜ ማለዳ ጋዛ ገብተዋል ብሏል። ተሽከርካሪዎቹ ከማለፋቸው በፊት በእስራኤል ወታደሮች በጥብቅ ከመፈተሻቸው ጋር ተያይዞም ሂደቱ ዘገምተኛ ነው ተብሏል። የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ በበኩሉ 61 የእርዳታ እህል፣ የመጠጥ ውሃ እና መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከራፋህ ወደ ሰሜን ጋዛ ማቅናታቸውን አስታውቋል። ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም የውጊያው ማዕከል ወደሆነችው ሰሜናዊ ጋዛ የገባው ከፍተኛ እርዳታ መሆኑ ተነግሯል። የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ በደቡብ እስራኤል ኒትዛና የድንበር ማቋረጫ በኩል 226 የእርዳታ መኪኖች እንደሚገቡ ይጠበቃል ብሏል። እነዚህም ተሽከርካሪዎች ወደ ግብፅ ካቀኑ በኋላ በራፋህ በኩል አድርገው ወደ ጋዛ ይገባሉም ተብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want