በትግራይ የተካሄደው ጦርነት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዕልቂት ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ለመፈናቀል እና ለስደት ዳርጓል።
ከእነዚህም መካከል የማሾ ፀጋይ ቤተሰቦችን መፈናቀል እና ስደት፣ ረሃብ እና ሞት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሦስት ጊዜ ተፈራርቀውበታል።
ከ40 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተከሰተው ረሃብ እና በወቅቱ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ማሾ በ1977 ዓ.ም. ወደ ሱዳን ተሰደደች። በዚሁ ጊዜም የማሾ ወንድም ብርሃነም ከወላጆቹ ጋር ወደ ሱዳን ተሰደው ነበር።
ማሾ ጦርነቱ ሲያቃ በ1988 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ተመልሳ ኑሯዋን ሑመራ ውስጥ ስትጀምር ወንድሞቿን ግን በሕይወት አላገኘቻቸውም ሁሉም በጦርነቱ ሞተው ነበር።
ወንድሟ ግን ወደ አገሩ ሳይመለስ ሱዳን ውስጥ ትዳር መሥርቶ ሁለት ልጆች ከወለደ በኋላ በህመም ምክንያት ወደ አገራቸው ሳይመለሱ እዚያው ፖርት ሱዳን ውስጥ አረፉ።
በስደት እና በጦርነት ቤተሰቦቿን ያጣችው ማሾ ለሁለቱ የወንድሟ ልጆች አክስት በመሆኗ ወላጆቻቸውን በስደት አገር ያጡትን ህጻናት ከሱዳን አስመጥታ የማሳደጉን ኃላፊነት ወሰደች።
ወደ አገሯ ተመልሳ ሑመራ ውስጥ ትዳር መሥርታ ኑሮን ለማሸነፍ እና የወንድሟን ልጆች ለማሳደግ በቀን ሥራ፣ በንግድ እና በቻላችው ሁሉ ትታትር ነበር፤ ነገር ግን በ2013 ዓ.ም. በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ሌላ ቀውስ ይዞባት መጣ።
ማሾ የራሷ አንድ ልጅ የነበራት ሲሆን፤ ያሳደገቻቸውን የወንድሟ ልጆች ሳምሪ እና ሄለንን ፈጽሞ ከልጇ ሳትለው “ልጆቼ” ነው የምትላቸው።
በትግራይ ደም አፋሳሹ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሁለቱ ሴት ልጆች የቤተሳባቸው የቀደመ ዕጣ ተከተላቸው። ታላቅየዋ ሳምሪ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ስትሰለፍ፣ ሄለን ደግሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሰደደች።
በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አካይነት ከአገር የወጣችው የ17 ዓመቷ ሄለን አሁን በደላሎች ታግታ እንግልት እየደረሰባት መሆኑን እና ለማስለቀቅ ከአቅም በላይ ገንዘብ እንደተጠየቀች ማሾ ትናገራለች።

መፈናቀል፣ ስደት፣ እገታ. . .
የማሾን ቤተሰብ የሌሎችንም ኑሮ ያወደመ እና ሕይወታቸውን ያመሳቀለው ጦርነት ከመነሳቱ በፊት “ልጆቼ ተምረው፣ ተመርቀው፣ ሥራ ይይዙልኛል፤ ለራሳቸው ተርፈው እኔን ይጦሩኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር” ትላለች።
ይሁን እንጂ ልጆቿ ከትምህርታቸው እና ከወደፊት ተስፋቸው ተስተጓጉለው ወደ ጦርነት እና ወደ ስደት በማምራታቸው ተስፋዋ ጨነገፈ። ማሾም ከእሷ ጀምሮ ቤተሰቧ በማያባራ የጦርነት፣ መፈናቀል፣ የስደት እና የእንግልት ሰለባ መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝናታል።
በትግራይ ጦርነቱ ከቆመ ከሁለት ዓመት በላይ ቢሆንም አሁንም የወጣቶች ስደት አልተገታም። በተጨማሪም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ይሆናሉ የሚባሉ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም በተፈናቃዮች መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ።
ጦርነቱን ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ የሚል ሲሆን፣ ይህንን ዕውን በማድረግ በኩል የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት አካላት የሚጠበቅባቸውን ያህል አልፈጸሙም በሚል ተስፋቸው እየተሟጠጠ መምጣቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
መቀለ ውስጥ በሚገኝ መጠለያ የምትገኘው ማሾ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ከመሆኗ በተጨማሪ ከወራት በፊት በሕገወጥ መንገድ ወደ ስደት የወጣችው የ17 ዓመቷ ልጇ ሄለን ሁኔታ ሌላ ጭንቀት ፈጥሮባታል።
ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከየመን እና ራጎ ከሚባል ስፍራ እየደወሉ ሄለን እንድትለቀቅ በተደጋጋሚ ከአቅሟ በላይ ገንዘብ እንድትከፍል እየጠየቋት ነው። ለዚህም ማሾ ገንዘቡን ለማሰባሰብ በመቀለ ጎዳናዎች እየለመነች ትገኛለች።
“ማን እንደወሰዳት አላውቅም፤ የመን ስትደርስ 115,000 ብር ክፈይ አሉኝ። ከዚያም ሰዎች ረድተኝ ከፈልኩ። ወደ ራጎ ስትሄድ ተጨማሪ ገንዘብ ጠየቁኝ። እስከ 300 ሺህ ብር የሚደርስ ብር ይጠይቁኛል። በየጊዜው መጠኑ ይጨምራለረ” ትላለች።
ሄለን ከመሰደዷ በፊት ወደ መኖሪያቸው የሚመለሱበትን ጊዜ በጉጉት ትጠብቅ እንደነበረ የምትናገረው ማሾ፣ “ተመልሰን የራሷን ሥራ የመጀመር ፍላጎት ነበራት. . . ‘በድንኳን ውስጥ እስከ መቼ ይዘለቃል? ትለኝ ነበር።”
ማሾ በሐዘን ተሰብራ እያለቀሰች ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ጦርነቱ ምክንያት ነው ትላለች “[ጦርነቱ] ባይነሳ ይህ መፈናቀል አይፈጠርም ነበር፤ ልጄም. . . ስደትን በፍጹም አታስበውም ነበር። ይህን ሁሉ ስቃይ የፈጠረብኝ ይህ ጦርነት ነው” ስትል ታማርራለች።
አሁን ከአንድ ወር በላይ የሄለንን ድምጽ አልሰማችም።
ራጎ በሳዑዲ አረቢያ እና በየመን መካከል የሚገኝ ስደተኞች የሚሻገሩበት ድንበር ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአካባቢው በታጣቂዎች እና በወታደሮች እንደሚገደሉ እና እንደሚታሰሩ የመብት ድርጅቶች ሪፖርት ያመለክታል።
አርሶ ከመብላት የሰው እጅ ወደ መጠበቅ
ፈቂጦር ሐጎስ የስምንት ሰዎች ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው፤ በክረምት አርሰው በበጋ ወደ ገበያ የሚያቀርቡ ትጉህ ገበሬ እና ነጋዴ ነበሩ።
ልጆቻቸውን እስከ 12ኛ ክፍል ያስተማሩት አርሶ አደሩ፣ የክረምት ወቅት መልካም ሲሆን ፀሐይ ወጥታ እስክትጠልቅ አርሰው ከ40 እስከ 100 ኩንታል በቆሎና ሰሊጥ ያገኙ ነበር።
ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ማይካድራ አካባቢ ተፈናቅለው መቀለ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠግተው የሚገኙት ፈቂጦር፣ አሁን ለዕለት የሚጎርሱትን እርዳታ በመጠባበቅ ከ40 ሰዎች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ይኖራሉ።
“የነበረን ፀጋ አሁን ከየት ይገኛል?” በማለት በሕዝቡ ላይ ለደረሰው ቀውስ እና ውድመት የክልሉን አመራሮች ተጠያቂ በማድረግ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቀያቸው እንደሚመለሱ ተስፋ አድርገው እንደነበር ይናገራሉ።
አሁን ግን ወደ ቤታቸው የመመለስ ተስፋቸው እየተሟጠጠ ከመምጣቱ በተጨማሪ ሌላ ዙር አለመረጋጋት ወይም ጦርነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ፈቂጦር እና ሌሎች ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ገልጸዋል።
“. . . ከሌሎች ጋር እንዳጋጩን ሁሉ አሁን እርስበርስ እንዳያጋጩን ነው የምንሰጋው። ባለፈው ሳናገናዝብ ግጭት ውስጥ እንድንገባ ያደረጉትን ይበቃል። አብረን የምንኖር ገበሬዎች ነን ልንላቸው ይገባል። በባለፈው ጦርነት ጉዳት ያልደረሰበት የለም። ስለዚህ [ሕዝቡን] ማጋጨት ይብቃችሁ ልንላቸው ይገባል” ብለዋል።
ከሰቲት ሁመራ መፈናቀላቸውን የሚናገሩት የ73 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ ገብረመድኅ ሐጎስ በጦርነቱ ምክንያት ግማሹ ቤተሰባቸው ወደ ሱዳን ተሰዷል።
ከግብርና ሥራቸው በየዓመቱ እስከ 65 ኩንታል ሰሊጥ እና እስከ 120 ኩንታል ማሽላ ያመርቱ የነበረ ሲሆን፣ አምስት ልጆቻቸውን በማስተማር ሁለቱ ሥራ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ጦርነቱ ሁሉንም ነገር አመሳቅሎት ንብረታቸውን አጥተው ቤተሰባቸው ለስደት እና ለመፈናቀል ተዳረገ።
አሁን “በልጆቼ ናፍቆት እና በችግር ውስጥ ነው ያለሁት። በሞት እና በሕይወት መካከል ነው እየኖርኩ ያለሁት” በማለት በምሬት የሚናገሩት አቶ ገብረመድኅን፣ ጦርነቱ ሲቆም በአጭር ጊዜ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ቢያደርጉም ሊሳካ አልቻለም።
“ሁሉም ሰው በስምምነቱ ተደስቶ ነበር፤ . . . [ለመመለስ] ተስፋ አድርገን ነበር። ይሁን እንጂ ችግሩ ያለው ከትግራይ መሪዎች ጋር ነው። እኛን ሊመልሱን አልቻሉም፤ ግድ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ትርጉም በሌለው በራሳቸው ሽኩቻ ውስጥ ነው ጊዜውን ያሳለፉት” በማለት ወቅሰዋል።
በእንጥልጥል ያለው የተፈናቃዮች ጉዳይ
በመቶ ሺዎችን ለህልፈት ዳርጓል የተባለው የትግራይ ጦርነት ካበቃ በኋላ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች ተፈናቅለው እዚያው በክልሉ ውስጥ እና ድንበር ተሻግረው ከ60,000 በላይ ደግሞ በጦርነት ውስጥ በምትገኘው ሱዳን ውስጥ ይገኛሉ።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች የሚገኙባቸው ኡምራኩባ፣ ተንድባ እና ሃሼባ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ግድያ እና አፈናን ጨምሮ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የተፈናቀሉት የአማራ ክልል የይገባኝ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረው እና በጦርነቱ ወቅት ከተቆታጠረው የምዕራብ ትግራይ አካባቢ ነው። ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በጊዚያዊ መጠለያዎች በአስቸጋሪ ውስጥ እንደሚገኙ ይነገራሉ።
በተለያዩ ጊዜያትም በክልሉ መዲና መቀለን ጨምሮ በአዲግራት፣ በአክሱም፣ በዓብይ አዲ፣ በሽሬ እና በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ተፈናቃዮች የፌደራል መንግሥቱ እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ቀያቸው እንዲመልሷቸው የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል።
ባለፈው ዓመት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ወደ በምዕራብ ትግራይ ያለው ውስብስብ ሁኔታ ተስተካክሎ ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሥራ “እስከ ሰኔ መጨረሻ (2016ዓ.ም)” ይመለሳሉ በማለት ተናገረው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግብራዊ አልሆነም።
የምዕራብ ትግራይ ሲቪል ማኅበረሰብ ሊቀመንበር አቶ ፀጋይ ተጠምቀ በዜጎች ላይ የደረሰው መፈናቀል በሁሉም ወገን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኗል በማለት በተለይ የክልሉ መሪዎች
“ሕዝቡን በመካድ ፖለቲካዊ ቁማር እየተጫወቱ ነው” ሲል ይኮንናሉ።
ችግሩ የተፈናቃዮች ብቻ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ፀጋይ ጫናው ባስጠለላቸው ማኅበረሰብም መሆኑን ይጠቅሳሉ። “የሚኖሩተረ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፤ መድኃኒት እና የምግብ ከኅብረተሰቡ ነው የሚያገኙት” በማለት ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ ይጠይቃሉ።
“ተስፋ መቁረጥ የሰው ልጅ ትልቁ ሞት ነው። መንግሥታት እየቀለዱ ነው፤ በዚህ ምክንያት በብስጭት እና በተስፋ መቁረጥ ምክንያት ወደ ስደት የሚያመሩ ወጣቶች ብዙ ናቸው” ይላል።
በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ ያለው በህወሓት አመራሮች መካከል የቀጠለው ፖለቲካዊ አለመግባባት ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ የሚነሷቸው ቅሬታዎች ትኩረት እንዳያገኙ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የተባለው የመብት ተሟጋቹ ይገልጻል።
የተፈናቃዮቹ ጉዳይ በሁሉም ወገን የመደራደሪያ እና ፍላጎትን የማስፈጸሚያ አጀንዳ የሆነ እንደሚመስል የሚናገሩት የተቋሙ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ፣ ፖለቲካዊ ፍላጎት እንቅፋት መሆኑን ያመለክታሉ።
በደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ይህ የተፈናቃዮች ጉዳይ እልባት ካገኘ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ እግሩን ይተክላል የሚል ዝንባሌ ያለው ይመስላል” በማለት፣ ጉዳዩን አንዱ ወገን ካስፈጸመው “ሌላኛው ተቀባይነት፣ እውቅና እንዲሁም አጀንዳ ያጣል” ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ በአካባቢዎቹ ያሉ ታጣቂዎችን አለማስወጣቱ እንዲሁም በአማራ ክልል የተደራጁት አስተዳደሮች ባለመፍረሳቸው ተፈናቃዮችን ለመመለስ ከባድ የደኅንነት ስጋት እንደሆነ ይናገራሉ።
ስለዚህም የፕሪቶሪያው ስምምነት አንድ አካል የሆነውን ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስን ቅድሚያ በመስጠት የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣናት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ተቋም ምክትል ዳይሬክተሩ ጥሪ ያቀርባሉ።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)