ኬነሳ ሙሉነህ ትባላለች።
ትውልደ ኢትዮጵያዊት ነች።
በሃያዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል እያለች የቤተሰቦቿን ሕልም ዕውን ለማድረግ በህክምና ዶክትሬቷን ያዘች።
የማኅበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ እና ‘ተጠቃሚ’ ናት።
ሦስት፣ አራት የንግድ ድርጅቶችን መሥርታ ስኬታማ አድርጋቸዋለች።
ለስኬቴ ማህበራዊ ሚዲያ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የምትለው ኬነሳ አብዛዎቹን ስራዎቿንም የምትሰራው በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ነው።
“ሙሉ” የተሰኘ የፋሽን መለያ አላት።
ለፋሽን ሥራዎቿ የሚሆን ልብስ የምታመርትበት የራሷን ፋብሪካ ፓኪስታን ውስጥ ገንብታለች።
ኑሮዋን ዱባይ አድርጋ የፋሽን መለያ ልብሶቿን በእስያ፣ አፍሪካ እና አውሮፓ ገበያዎች እየሸጠች ነው።
የሕይወት ጉዞ ተሞክሮዋን እና የቢዝነስ ፈጠራ ሐሳቦችን በተመለከተ ትምህርት ትሰጣለች። ኬነሳ ሙሉነህ. . .
ኬነሳ ትውልዷ ድሬዳዋ ቢሆንም ያደገችው እስከ ሦስት ዓመቷ ብቻ ነው።
ገና በጨቅላነቷ ሶስት ዓመቷ እያለ ነው ከወላጆቿ ጋር ወደ ኔዘርላንድስ ያመራችው።
ከወላጆቿ ጋር መሄዷ አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ የኢትዮጵያ ወግ ባሕልን ከእነርሱ እንድትማር አስችሏታል።
ያደገችበት የኔዘርላንድስ ባህልም “ሌላ ማንነቴ ነው” ትላለች ኬነሳ።
አሁን እየሰራቻቸው ላሉ ስራዎች ያሏት ድርብርብ ማንነቶች የሁለቱን አገራት ዜጎች በማግኘት ረገዱ እንዳገዟት ትገልጻለች።
ኢትዮጵያውያኑ ወላጆቿ ለልጃቸው ያለሙት የህክምና ዶክተር እንድትሆን ነበር።
ህክምና ማጥናት ፍላጎቷ ባይሆንም ህክምና አጠናች።
በእርግጥ ባደገችበት አገር ልጆች ፍላጎታቸውን መርጠው እንዲያሟሉ ይበረታታሉ።
ሌሎች የትምህርት ቤት ጓደኞቿም ያደረጉት ይህንኑ ነው።
ኬነሳ ግን የወላጆቿን ፍላጎት ለማሳካት የሕክምና ትምህርት ቤት ገባች።
ትምህርቷንም አጠናቃ ‘ዶክተር’ ሆነች።
ነገር ግን በሕክምና ሙያው ከምርቃት በኋላ አንድም ቀን ሐኪም ሆና አልሰራችበትም።
“የወላጆቼን ፍላጎት አሟልቻለሁ፤ አሁን ደግሞ የአኔን ፍላጎት ላሟላ ብዬ የራሴን ሥራ ጀመርኩ” በማለት ሙሉ በሙሉ ከሕክምና ሥራ የተለየ ሥራ መጀመሯን ትናገራለች።
በተመረቀችበት የሕክምና ሙያ ባትሠራበትም ሕክምና መሟሯ ግን የቀጣይ ሕይወቷን የሚቀይር አጋጣሚ እንደፈጠረላት ትናገራለች።
ነገሩ እንዲህ ነው።
የሕክምና ትምህርቷን የማጠናቀቂያ የመጨረሻው ዓመት ላይ የመመረቂያ ጽሑፍ እንድታዘጋጅ በአማካሪዋ ዘንድ ይነገራታል።
ኬነሳ ያቀረበችው የምርምር ጽሑፍ መነሻ ሃሳብ ‘ነርሶች በህመም ወይም በሌላ ምክንያት ከሥራ ቦታ በሚቀሩበት ወቅት ባሉበት ቦታ ሆነው ሥራቸውን መሥራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት’ የሚል ነበር።
ያዘጋጀችው የምርምር ጽሑፍ በአማካሪዋ ዘንድ አድናቆትን አስገኘላት።
ወደ ተግባር መቀየር እንደሚችልም አማከሯት።
ኬነሳ አላመነታችም።
ወዲያውኑ የምርምር ሥራዋን ወደ ተግባር ቀይራ የራሷን የመጀመሪያ ድርጅት መሰረተች።
ከአንድ ዓመት በላይ ሰራችበት።
ከዚሁ ድርጅት በአማካይ በወር እስከ አንድ ሽህ የአሜሪካን ዶላር ገንዘብ ታገኝበት እንደነበር ታስታውሳለች።
ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ድርጅቱን የመግዛት ፍላጎት አሳደረ።
ድርጅቱ ተሸጠ።
ኬነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድርጅቱ ሽያጭ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ካዝናዋ አስገባች።
“ገንዘቡ ድጋሚ ካልተሠራበት ሊያልቅ ይችላል፤ እንዲያም ሆኖ ግን በዚያ ዕድሜ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማግኘት ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
የድርጅቱ መመሥረት እና መሸጥ ለኬነሳ ሁለት ነገር አምጥቷል።
አንደኛው ሃብት አፈራችበት፣ ሁለተኛው “ችግርን በማጥናት መፍትሔውን ማፈላለግ እንዳለብኝ ትምህርት አገኘሁበት” በማለት የምርምር ሥራዋን አስተዋጽዖ ትገልጻለች. . .
ሌላ ድርጅት ለመፍጠር ያነሳሳት ደግሞ የምትወደው ስፖርት ነው።
ክብደት ማንሳት ከሚያስደስቷት አካላዊ እንቅስቃሴዎች መካከል አንዱ ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋመችውን ድርጅት ከሸጠች በኋላ ግን ትኩረቷን “የአሜሪካ ፉትቦል” መጫወት አደረገች።
ነገር ግን ይህ የስፖርት አይነት በኔዘርላንድስ በሴቶች ዘንድ አልተለመደም።
አሰልጣኞችን ስትጠይቅ የአሜሪካን ፉትቦል ኔዘርላንድስ ውስጥ ለሴቶች አለመኖሩን ይነግሯታል።
ምን ማድረግ እንዳለባት ስትጠይቃቸው “የአሜሪካን ፉትቦል መጫወት ከፈለግሽ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ሴቶች ሰብስበሽ ቡድን መመሥረት አለብሽ” የሚል ምክረ ሐሳብ ይሰጧታል።
ኬነሳ ከችግር ተነስቶ ወደ መፍትሔ ፍለጋ ማምራት የመጀመሪያ ሥራዋ ስላስተማራት ይሄኛውንም አጋጣሚ ወደ መልካም ነገር ለመቀየር ወሰነች።
ወዲያውኑ ፍላጎት ያላቸው ሴቶችን ለመሰብሰብ በማኅበራዊ ሚዲያ ማስታወቂያ አጋራች።
ውጤቱ ከጠበቀችው በላይ ሆነ።
በአንዴ በኔዘርላንድስ ትልልቅ ከተሞች የሚኖሩ ከ200 በላይ ሴቶች ፍላጎታቸውን ገለጹላት። ኬነሳ ጊዜ አላባከነችም።
በፍጥነት አሰልጣኝ ቀጥራ፣ ቡድኖቹን አዋቅራ፣ ትጥቅ አሟልታ፣ የመጫዋቻ ሜዳ አዘጋጅታ ጨዋታውን በተለያዩ ከተሞች ማካሄድ ጀመረች።
የኬነሳ ፍላጎት የነበረው ጨዋታውን ለአጭር ጊዜ አከናውኖ ማቆም ነበር።
ነገር ግን የሰበሰበቻቸው ሴቶች ጨዋታው እንዲቀጥል ፈለጉ።
በዚህም ጨዋታው ወደ ሊግ ማደግ እንዳለበት አመነች።
እናም በተለያዩ ከተሞች ቡድን መሥርታ መደበኛ ጨዋታ እያካሄዱ አንድ የመዝናኛ ስፖርት እንዲሆን አስቻለች።
ጨዋታው በሊግ ደረጃ ተመሰረተ፣ ባለቤትነቱንም መስራቿ ከኔሳ ጠቀለለች።
በሁሉም ከተሞች ተመዝግበው የሚጫወቱ አባላት የአባልነት ክፍያ ይከፍላሉ፤ የመጫዎቻ ግብዓቶችንና አልባሳትን የሚገዙትም ከኬነሳ ነው።
ዳጎስ ያለ ገቢ ማስገኘት ጀመረ። በአጭር ጊዜ ወደ ትልቅ ድርጅት አደገላት። ትልልቅ በሚባሉት የኔዘርላንድስ ከተሞች የሚኖሩ ሴቶችም ስፖርቱን ወደዱት።
“ጨዋታውን ለተወሰነ ጊዜ ተጫውተን ያልቃል የሚል እሳቤ ነበረኝ፤ ነገር ግን ከጠበቅኩት በላይ አድጎ ትልቅ ድርጅት ሆነ” በማለት የድርጅቷን እድገት ታስታውሳለች።
ኬነሳ የአዲሱ ድርጅቷ ተጠቃሚዎች በየጊዜው ቢጨምርም ድርጅቱን በባለቤትነት ይዛ ለረጅም ጊዜ መቆየት አልፈለገችም። “አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ስለምፈልግ አንድ ነገር ላይ ብዙ ጊዜዬን ማጥፋት አልፈለግኩም” ትላለች።
በመሆኑም በኔዘርላንድስ ያቋቋመችውን የሴቶች የአሜሪካ ፉትቦል ድርጅት እንደመጀመሪያው ድርጅቷ ሁሉ ይህንንም ሸጠችው።
የህይወቷን አጋጣሚዎች ለስራ መፍጠሪያነት የምትጠቀመው ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ኬነሳ በተለይም ሁለተኛ ልጇን ስትወልድ ክብደቷ መጨመሩ ሌላ መነሻ ሆናት።
ክብደት ለመቀነስ ስፖርት ብትሰራም በአንድ ጊዜ ሰውነቷ ስላልቀነሰ ሰፋ ያሉ ልብሶችን መልበስ ነበረባት።
ሆኖም ገበያ ስትወጣ ግን ከፍላጎቷ ጋር የሚጣጣም ሰፋፊ ልብሶች [ፕላስ ሳይዝ] ማግኘት አልቻለችም።
ይህ ገጠመኝ ታዲያ ለኬነሳ ችግር አልሆነም።
እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ይህንን ችግርም “መፍትሔ ልፈልግለት” የሚል ሃሳብ አመነጨች። በዚህ አጋጣሚ ነበር የዛሬው “ሙሉ የፋሽን ብራንድ” የተጀመረው።
በእኔ ላይ የደረሰው ትልልቅ ልብሶች እጥረት በሌሎች ሰዎች ላይም ይደርሳል የሚል እሳቤ አደረባት።
በመሆኑም ይህን የብዙ ሰዎችን ችግር መፍትሔ ለማበጀት አዲስ የልብስ ሥራ መጀመር እንዳለባት ወሰነች።
በዚህም ምክንያት “ሙሉ ብራንድ” የተሰኘውን ድርጅቷን መሰረተች።
መጠናቸው ሰፋ ያሉ ልብሶችን የሚያመርተው የኬነሳ ድርጅት፣ ስያሜውን ያገኘው ከአባቷ ሙሉነህ ስም መሆኑን ትናገራለች።
በመሆኑም የልብሱ መጠን ሙሉ [ፉል ሳይዝ] መሆኑንም አባቷንም ለማስታወስ ‘ሙሉ ብራንድ’ በሚል ተደራራቢ ትርጉሞች ባሉት መልኩ መሰየሟን ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት ኬነሳ ፓኪስታን ውስጥ የልብስ ፋብሪካ አላት።
ፋብሪካው ከሙሉ ብራንድ በተጨማሪ ለሌሎች የልብስ ፋሽን ኩባንያች ጭምር ልብስ ያመርታል።
ለዚሁ ሥራ ሲባል ኑሮዋን ከኔዘርላንድስ ወደ ዱባይ ቀይራለች።
ዱባይ የንግድ ሥራዋን ለማሳለጥ ጥሩ ዕድል እንደፈጠረላት ትገልጻለች። ምርቶቿን በእስያ፣ አፍሪካ እና አውሮፓ ገበያዎች ለማሰራጨት አማካይ ቦታ እንደሆነላት ትናገራለች።
ከዚህም በተጨማሪ በሁለት ማንነት እና ማኅበረሰብ ውስጥ ማደጓ [ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ] ገበያዋን በስፋት ለማዳረስ እንዳገዛት ገልጻለች።
በአፍሪካ ጋና እና ናይጄሪያ በብዛት የፋሽን ልብሶቿን የምትሸጥባቸው አገራት ሲሆን ኢትዮጵያ በቅርቡ መጀመሯን ተናግራለች።
በቀጣይም ወደ ሕንድ እና ፓኪስታን የማስፋት እቅድ አላት። አውሮፓ እና አሜሪካ ከመጀመሪያው ጀምሮ የገበያ አማራጮቿ ናቸው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ተቀጥረው የሚሠሩ ከ50 በላይ ሠራተኞች አሏት።
የእርሷ መደበኛ ሥራ ችግሮችን መመርመርና መፍትሔያቸውን መፈለግ ነው። በኦንላይን የምትሠራው ሥራም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው።
ኬነሳ አሁን በጀመረቻቸው ሥራዎች ሁሉ ውጤታማ እና ስኬታማ ሆናለች።
ከጠንካራ ሠራተኝነት በተጨማሪ ማኅበራዊ ሚዲያ ለስኬቶቿ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ትገልጻለች።
ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ሁለት ተዋንያን አሉ የምትለው ኬነሳ፣ “አንደኛው ተጠቃሚ [ከምርቱ ወይም አገልግሎቱ ጥቅም የሚያገኝ] ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ተጠቃሚ [ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ግን ደግሞ ምንም ትርፍ የማያገኝ] ናቸው ትላለች።
እናም እርሷ የመጀመሪያዋ አይነት ተጠቃሚ ነች። ማኅበራዊ ሚዲያ ምርቶቿን እና አገልግሎቶቿን ለተጠቃሚዎች የምትሸጥበት ዋነኛ መድረክ ነው።
ከንግድ ሥራዋ በተጨማሪ አስተማሪ ነኝ ትላለች። የምታስተምረው ዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ውስጥ ተቀጥራ አይደለም።
በኦንላየን ተማሪዎችን መዝግባ የሕይወት ጉዞዋን እና የቢዝነስ ፈጠራን በተመለከተ ትምህርት ትሰጣለች። ብዙ ተማሪዎቿም አዳዲስ ቢዝነስ ጀምረው ለውጥ እያመጡ መሆኑን ተናግራለች።
ኬነሳ ከሥራ ፈጠራ ክኅሎቷ እና የአስተማሪነት ሥራዋ በተጨማሪም የኦንላየን ይዘት ፈጠራ ላይ ትሠራለች። በቅርቡ ‘አድዋ’ የተሰኘ የኢንተርኔት ጨዋታ [ጌም] ይፋ አድርጋለች።
ጨዋታው ታሪካዊውን የኢትዮጵያ የአድዋ ድል የሚዘክር ነው።
በጨዋታው የወከለቻቸው ገጸ ባህሪያት እና አጠቃላይ የጨዋታው ሂደትም በጦርነቱ ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን ሚና የሚያስታውስ፣ አልበገር ባይነታቸውን፣ ጀብደኝነታቸውን የሚዘክር ነው።
ስራ ፈጣሪዋ ኬነሳ ድርጅት ፈጥሮ መሸጥ ዋነኛ መገለጫዋ ነው።
ከዚህ በኋላም ክፍተቶችን የሚሞላ ግኝት በማምጣት ሥራዋቿን እንደምትቀጥል ገልጻለች።
ሀኖም እንደከዚህ ቀደሙ ግን “ድርጅት በመፍጠር እና በመሸጥ ብዙም የምሳተፍ አይመስለኝም” ብላለች።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡- (ቢቢሲ )