ዶክተር ቴድሮስ እስራኤል በየመን ከፈጸመችው የአየር ጥቃት “በሕይወት ለመትረፌ እርግጠኛ አልነበርኩም” አሉ……. Leave a comment

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሐኖም ገብረ እየሱስ እስራኤል በየመኗ መዲና ሰንዓ ዓለም አቀፍ ማረፊያ ከፈጸመችው የአየር ጥቃት “በሕይወት ለመትረፌ እርግጠኛ አልነበርኩም” አሉ።

እስራኤል ሐሙስ፣ ታህሳስ 17/ 2017 የሰንዓ የዓለም አቀፍ ማረፊያ ላይ የአየር ጥቃት ስትፈጽም በስፍራው የነበሩት ዶክተር ቴድሮስ ወደ አውሮፕላኑ ሊሳፈሩ ነበር።

ከጥቃቱ ያመለጡት ዶክተር ቴድሮስ ከክስተቱ በኋላ “ህንጻውን ያናወጠው ፍንዳታ በጣም የከበደ ከመሆኑ የተነሳ ከአንድ ቀን በኋላም ጆሬዬ ላይ ያቃጭላል” በማለት በሰንዓ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ዶክተር ቴድሮስ ፍንዳታ በተሰማበት ወቅት አውሮፕላን ማረፊያው ጥቃት እየተፈጸመበት እንደሆነ በፍጥነት በመታወቁ፣ ከአራቱ ፍንዳታዎች በኋላ በርካቶች “በድንጋጤ መሯሯጥ” ጀመሩ ሲሉ ከሮይተርስ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አንደኛው ፍንዳታ እርሳቸው ተቀምጠው ከነበረበት በረራ ከሚነሳበት ማረፊያ “በሚያስደነግጥ ሁኔታ” ቅርብ ነበር ብለዋል።

“በእርግጥ በሕይወት እንደምተርፍ እርግጠኛ አልነበርኩም። ምክንያቱም በጣም ቅርብ ነበር፣ እኛ ከነበርንበት ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ” ሲሉ ለሮይተርስ የተናገሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ “ትንሽ አቅጣጫውን ቢቀይር ቀጥታ ሊመታን ይችል ነበር” ብለዋል።

“ከሁለት ሰዓታት በፊት፣ ከሰንዓ ለመብረር ወደ አውሮፕላኑ ልንሳፈር ስንል አየር ማረፊያው የአየር ጥቃት ተፈጸመበት” ብለዋል።

“ልንሳፈርበት የነበረው አውሮፕላን ሰራተኞች መካከል አንዱ ቆስሏል። ቢያንስ ሁለት ሰዎች በአውሮፕላን ማረፊያው መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።

“እኛ ካለንበት ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ የነበረ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማማ እንዲሁም የማረፊያ ስፍራ እና ማኮብኮቢያው [በጥቃቱ] ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ነው ዶክተር ቴድሮስ የገለጹት።

ዶክተር ቴድሮስ እሳቸውና ባልደረቦቻቸው ከጥቃቱ በኋላ በአውሮፕላን ማረፊያው ለሰዓት ያህል ተቀምጠው እንደነበር ለሮይተርስ ገልጸው በላያቸው ላይ ድሮኖች እያንዣበቡ የነበረ በመሆኑ እንደገና ጥቃት ይፈጸማል የሚል ስጋት ውስጥ “ገብቼ ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።

በስብርባሪዎች መካከል የሚሳኤል ቁርጥራጮች ማየታቸውንም ገልጸዋል።

“በፍጹም ምንም መጠለያ አልነበረም። ምንም የለም። በተጋለጠ ሁኔታ ነው የነበርነው። የትኛውም ሁኔታ እንደሚፈጠር እየጠበቅን ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

እስራኤል በየመን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ሁቲዎች በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ አጋርነት ለማሳየት ሲሉ በተደጋጋሚ በድሮኖች እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፋቸውን ተከትሎ ነው።

ከጥቃቱ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሁቲዎች ለፈጸሙት ጥቃቶች የሚሰጠው ምላሽ ገና መጀመሩ መሆኑን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

በጥቃቱ በአየር ማረፊያው ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም ሆዲዳህ በተሰኘው ግዛት ደግሞ የሶስት ሰዎች ሕይወት እንደተቀጠፈ በየመን ሁቲዎች የሚተዳደረው ሳባ የዜና ወኪል ዘግቧል።ከተገደሉት በተጨማሪ 40 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

ዶክተር ቴድሮስ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኛ ጋር አብረው አርብ ዕለት ወደ ዮርዳኖስ በርረዋል።

ከዮርዳኖስ ሆነው ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ እስራኤል በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ጥቃት ሊፈጸም እንደምትችል ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት (UNHAS) ሠራተኛ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ነው ዶክተሩ የተናገሩት።

ዶክተር ቴድሮስ ወደ የመን ያቀኑት በእስር ላይ ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች እንዲፈቱ ለመደራደር እና የአገሪቷን የጤና ሰብዓዊ ሁኔታ ለመገምገም ነበር።

በእስራኤል እና በሁቲዎች መካከል ከገቡበት ውጥረት አንጻር እሳቸውን ሆነ ባልደረቦቻቸው ጉዞው አደገኛ መሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች የሚፈቱበት የመስኮት እድል በመከፈቱ ወደዚያው ማቅናታቸውን ነው የገለጹት።

ከየመን ባለስልጣናት ጋር የተደረገው ውይይት በመልካም ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸው፣16ቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ሠራተኞች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች ከእስር የሚፈቱበትን ዕድል ማየታቸውን ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመሩት ዶክተር ቴድሮስ በጥቃቱ ማንም ላይ ጣት ለመጠቆም ፈቃደኛ ባይሆኑም የጉዞ መርሃ ግብራቸው በይፋ መጋራቱን እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ዒላማ መደረጋቸው እንዳስገረማቸው ተናግረዋል። “

እኔ ልኑርም አልኑርም የሲቪል አውሮፕላን ማረፊያ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። ከስራ ባልደረቦቼ አንዱ ለጥቂት ተረፍን አለ። እኔ አንድ ሰው ነኝ። በየቀኑ እንዲህ አይነት ተመሳሳይ ነገር ለሚገጥማቸው ተሰምቶኛል። ቢያንስ እነሱ የሚሰማቸውን ስሜት እንድሰማ አስችሎኛል”ብለዋል።

እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት አለም አቀፉን የሰንዓ አየር ማረፊያ፣ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን እና ወደቦችን መምታቷን አስታውቃለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው የሁቲ መሰረተ ልማቶችን ታወድማለች ሲሉ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረው ነበር።

ሁቲዎች ቅዳሜ በቴልአቪቭ የፈጸሙት ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ሚሳኤሎች ማስወንጨፋቸው ይታወሳል።

የሁቲ ቃል አቀባይ መሐመድ አብዱልሰላም ጥቃቱን “በየመን ሕዝብ ላይ የተፈጸመ የጽዮናዊ የሰብዓዊነት ወንጀል” ሲሉ መግለጻቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የሁቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ባለስልጣን በየመን የእስራኤል የአየር ጥቃት እየተባባሰ ቢመጣም ቡድኑ ከፍልስጤማውያን ጋር በመቆም እስራኤልን ላይ የከፈተውን ጥቃት ይቀጥላል ብለዋል።

መሐመድ አል ቡኻይቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል” እስካልቆመ ድረስ ሁቲዎች “በእስራኤል ወታደራዊ ዒላማ የምናደርሰውን ጥቃት አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ሐሙስ እለት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በቀይ ባህር ዳርቻ በሚገኙ ወደቦች እና ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቢያንስ አራት ሰዎችን ገድለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop