የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቻይና ውስጥ የተሠሩ ተሽከርካሪዎች፣ የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያዎች፣ ብረታ ብረቶችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እንዲጣል ወስነዋል።
ከቻይና የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች የሚጣልባቸው 100% የድንበር ቀረጥ አሜሪካውያን የሚያጡትን ሥራ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቻይና የቀረጥ ጭማሪውን ነቅፋለች። ተመጣጣኝ እርምጃ እንደምትወስድም አስታውቃለች።
ቀረጥ ለመጨመር ውሳኔ የተላለፈው በቀጣዩ ምርጫ የተሻለ ተወዳዳሪነት ለማግኘት እንደሆነ ተንታኞች ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኤሌክትሪክ መኪና የአሜሪካን ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ “ይገድላል” ማለታቸው ይታወሳል።
ባይደን በበኩላቸው ቻይና “ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ገበያውን እንድትቆጣጠር” እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።
“የኮቪድ ወረርሽኝ ያስተማረን አገራችን ውስጥ የምንፈልገው ነገር በብዛት ማግኘት እንዳለብን ነው” ብለዋል ባይደን።
ዋይት ሀውስ እንዳለው፣ አዲሱ የቀረጥ ጭማሪ 18 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወደ አሜሪካ የሚገባ ቁሳቁስን ይመለከታል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ቀረጥ ከ25% ወደ 100% ከፍ ያለ ሲሆን፣ የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያዎች ቀረጥ ከ25% ወደ 50% እንዲሁም የሌሎች ብረታ ብረቶች ቀረጥ በ25% ተጨምሯል።
የቻይና የንግድ ሚኒስትር ውሳኔው “የጋራ ትብብር መንፈስን” የሚያውክ ነው ሲል ተቃውሟል።
የምጣኔ ሀብት ጉዳይን የፖለቲካ ማድረግ እንደማይገባም አክሏል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ “ጥቅማችንንና መብታችንን ለማስከበር ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም የቀረጥ ጭማሪ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ በባይደን አስተዳደር ውሳኔው በድጋሚ እንዲጤን ትዕዛዝ ተላልፏል።
አሜሪካውያን ሸቀጥ የሚገዙበት ዋጋ እየጨመረ ስለሄደ የዋጋ ቅናሽ እንዲደረግ የጠየቁ ነበሩ።
የባይደን ውሳኔ ቀረጡ ባለበት ሆኖ አዳዲስ ዘርፎችም እንዲካተቱ ያደርጋል።
የኑሮ ውድነት ባይደን ያላቸው ተቀባይነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
የቀድሞ የአሜሪካ ንግድ ባለሥልጣን የነበሩት ዌንዲ ከልተር እንዳሉት፣ አሜሪካውያን ለተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ቢጠየቁም የአገሪቱ ዜጎችን ሥራና ተቋማትን የሚጠብቅ ሕግ ከሆነ እምብዛም ተቃውሞ ላይኖራቸው ይችላል።
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ውሳኔ በፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያዎችና ሌሎች ብረታ ብረቶች ላይ መተላለፉን አስታውሰው፣ አሁን የተለወጠው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ የተደረገው ማሻሻያ መሆኑን አስረድተዋል።
“አሁን ላይ መኪና ውድ ሊሆን ይችላል። በጊዜ ሂደት ግን ፉክክር ያለበት ኢንዱስትሪ ይሆናል” ብለዋል።
ቻይና አሜሪካን የሚጎዳ እርምጃ መውሰዷ ለውሳኔው መነሻ መሆኑንም አክለዋል።
ባይደን “ገበያውን ተቆጣጥረውታል። ውድድር ሳይሆን መሸነፍ ነው” ብለዋል።
ራሳቸውን ‘የቀረጥ አባት’ የሚሉት ትራምፕ የአሜሪካን ተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ ለመጠበቅ የቀረጥ ጭማሪ እንደሚያስፈልግ ይከራከሩ ነበር።
በታክስ ፋውንዴሽን ውስጥ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ኤሪካ ዮርክ ሁለቱም የፕሬዝዳንት እጩዎች “በተመሳሳይ መንገድ እየሄዱ ነው” ብለዋል።
ቀረጥ መጨመር ከፖለቲካ አንጻር ለባይደን እንደሚጠቅምና ዘርፉን ፉክክር የሞላበት ለማድረግ ነው የሚለው ከሽፋን የዘለለ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
“በምጣኔ ሀብት ትርጉም የሚሰጠው ምንድን ነው የሚለው ሳይሆን ትኩረት የተደረገበት ፖለቲካዊ ምጣኔ ሀብቱ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የተሽከርካሪዎች ምርት ዘርፍ በአንድ አገር ቁጥጥር ሥር ብቻ ያለ እንዳይሆን ውሳኔው እንደሚያግዝ ዋይት ሀውስ አስታውቋል።
የኢንቨስትመንት ማኔጅመንት ባለሙያ ናታሻ ኤቢታጅ እንደሚሉት፣ በአውሮፓም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።
“የቻይና ባለ ሃብቶችና ኢንዱስትሪዎች ብዙም በውሳኔው የሚገረሙ አይመስለኝም” ብለዋል።
ከአሜሪካ በላይ ተሽከርካሪዎች በሚገባበት አውሮፓ ውሳኔው ሲተላለፍ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እንደሚታይም አክለዋል።
ከአውሮፓውያኑ 2018 አንስቶ አሜሪካ እና ቻይና የንግድ ጦርነት ውስጥ ይገኛሉ።
ከቻይና የሚገቡ ቁሳቁሶች መካከል ሁለት ሦስተኛው ላይ ወደ 360 ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ቀረጥ አንዲጣል ትራምፕ መወሰናቸው ይታወሳል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )