በስፔን ላ ሊጋ ግራናዳ ከአትሌቲክ ቢልባዎ የሚያደርጉት ጨዋታ የአንድ ተመልካች ሕይወት በማለፉ ምክንያት ተቋርጧል። በኑዌቮ ሎስ ካርሜኔስ ስታድየም የነበረው የላ ሊጋ ጨዋታ ሰኞ ዕለት ከተቋረጠበት እንደሚቀጥል ተሰምቷል። እሑድ ዕለት የነበረው ጨዋታ ከ17 ደቂቃ በኋላ የተቋረጠው አንድ ተመልካች የልብ ሕመም አጋጥሞት ከወደቀ በኋላ ነው። የጤና ባለሙያዎች ግለሰቡን ለማዳን ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጨዋታው ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ተቋርጦ ተመልካቾች ወደቤታቸው እንዲመለሱ ተነግሯቸዋል።
ቢልባዎ 1-0 እየመራ ሳለ የተቋረጠው ጨዋታ ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ከ17ኛው ደቂቃ ጀምሮ በተመሳሳይ ውጤት እንደሚቀጥል ላ ሊጋ ጠቁሟል። የሰንበቱን ጨዋታ ለማየት ቲኬት የቆረጡ ተመልካቾች ወደ ስታድየም መግባት ይችላሉ። ግራናዳ እግር ኳስ ክለብ ለሟች “ቤተሰቦችና ወዳጆች እንዲሁም ለመላው የግራናዳ ቤተሰብ መፅናናትን እንመኛለን” ብለዋል።
የአትሌቲክ ቢልባዎ ግብ ጠባቂ ኡናይ ሲሞን ደጋፊው እርዳታ እንደሚሻ በመጠቆሙ በግራናዳ ደጋፊዎች አድናቆት ተችሮታል። የሁለቱ ክለቦች ተጨዋቾች ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ 20 ደቂቃ ያክል ጠብቀው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ተደርገዋል። በሌላ የላ ሊጋ ጨዋታ የዘንድሮው ክስተት ጂሮና ወደ ባርሴሎና አቅንቶ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል።
ጂሮና ወደ ካምፕ ኑ ሄዱ ባርሴሎናን በሜዳው 4-2 በመርታት የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ላ ሊጋውን ጂሮና በ41 ነጥብ ሲመራ፤ ሪያል ማድሪድ በ39 ሁለተኛ፣ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አትሌቲካ ማድሪድ በ34 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ባርሴሎና በጎል ድርሻ ተበልጦ በተመሳሳይ 34 ነጥብ ከአትሌቲኮ ዝቅ ብሎ አራተኛ ደረጃን ይዟል። አትሌቲክ ቢልባዎ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ግራናዳ አስራ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጣና ይገኛል።