ጦርነት እንዲቆም በሚጠይቅ አጭር ፊልም ታዋቂ ሽልማትን ያገኘው ወጣት ኢትዮጵያዊ Leave a comment

አንዲት ወጣት መምህርት ወደ ማስተማሪያ ክፍል ስትገባ ፊልሙ ይጀምራል።እንደምን አደራችሁ ተማሪዎች?” በማለት መምህርቷ ለተማሪዎቿ ሰላምታ ታቀርባለች። ዘለግ ያለውደህና እግዚአብሔር ይመስገን!” የሚለው የተለመደ የተማሪዎች ምላሽ ግን እዚህ ክፍል ውስጥ አይሰማም።

ከዚያም መምህርቷ ቁጭ ብላ የተማሪዎቿን ስም መጥራት ትጀምራለች። ሄለን ተስፋዬ፣ ጋዲሳ ፍራኦል፣ ዊንታና ሐጎስ. . . እያለች ጥሪው ይቀጥላል፤ ምላሽ ግን የለም።

ክፍሉ ውስጥ ያሉት ተማሪዎቿ ሳይሆኑ ቀድመው ይቀመጡበት በነበረው ወንበር ላይ የተለጠፈ ፎቷቸው ነው። ከእያንዳንዱ ፎቶ ስር ሕጻናቱ ሰለባ የሆኑበት ጦርነት እና የደረሰባቸው ጉዳት ተጽፏል።

የተወሰኑት ሞተዋል፣ ቀሪዎቹ ተሰደዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የገቡበት አይታወቅም። ሕጻናቱ የሌሉበት መዋዕለ ሕጻናት፤ ጦርነት የበላቸውን ተማሪዎች ፎቶ የያዘ ትምህር ቤት

የአንድ ደቂቃው ፊልም እዚህ ላይ ያበቃል። አጭር ፊልም ነውና ዝርዝር ማብራሪያ ውስጥ አይገባም።ስቶፕ ዋር” (ጦርነት ይቁም) የተሰኘው ይህ አጭር ፊልም ዓለም አቀፉ የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ሽልማት አዘጋጅኤሚከሌላ ተቋም ጋር በጋራ ያዘጋጀውን የአጭር ፊልም ውድድር ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ አሸንፏል። የፊልሙ አዘጋጅ ደግሞ 27 ዓመቱ ወጣት ሀብታሙ ሰፊው መኮንን ነው።

 ሁሌም ዝግጁ ነበርኩ…”

ሀብታሙ፤ ጀማሪ ፊልም ሠሪ ነው። ከሠራው ይልቅ በተስፋ የሰነቀው ይበልጣል። ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ መኖሪያውን በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ አድርጎ አሁን ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል።

የአስራ አንድ ወራት የናይሮቢ ቆይታውን ያሳለፈው ከተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከመጡ ወጣት ፊልም ሠሪዎች ጋር በመልቲ ቾይስ ታለንት ፋክትሪ የፊልም ሥራን ሲሠለጥን ነው። በዚህ የሥልጠና ስፍራ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ የፊልም ስቱዲዮዎች፣ መሳሪያዎች እና ባለሙያዎች ይገኛሉ።

በናይሮቢ ቆይታው የተለያዩ አጫጭር ፊልሞች እና የሙዚቃ ቪድዮዎች ላይ በተለያየ መልኩ ተሳትፏል። ከወዳጆቹ ጋር ለመመረቂያነት በሠሩት “FULL TIME HUSBAND” የተሰኘ ረጅም ፊልም ላይ ደግሞ በአዘጋጅነት እና በፊልም ጽሁፍ ተሳትፏል። ይህ ፊልም በእንግሊዝኛ እና በስዋሂሊ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው።

ወጣቱ ፊልም ሠሪ ከዚህም በፊት ቢሆን ግን ለፊልም ሥራ አዲስ አይደለም። 2010 .. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቲያትር እና ሥነ ጥበባት ተመራቂ ተማሪ እያለተፈጣሪበተሰኘ ልብ አንጠልጣይ ፊልም ላይ በፕሮዳክሽን ማናጀርነት ተሳትፏል። ኋላ ደግሞ አሜሪካውያን ፊልም ሠሪዎች “A FIRE WITHIN” ወይም በአማርኛ ስሙፍትህየተባለ ፊልም ወደ ኢትዮጵያ ይዘው ሲመጡ በአገር ውስጥ ለነበረው ቀረጻ ረዳት አዘጋጅ ነበር።

እነዚህ ፕሮዳክሽኖች ላይ ከተሳተፍኩ በኋላ ራሴን ስፈትሸው የፊልም ሥራን ለመቀላቀል ብቁ አልነበርኩም። ስለዚህ አሁን የፊልም ሥራው ላይ አልገባም ብዬ ወሰንኩ። በደንብ ልማር፣ ክህሎቴን ላሳድግ እና ያኔ [ኢንዱስትሪውን] እቀላቀላለሁ አልኩይላል ከዩኒቨርስቲ ሲወጣ ለምን ፊልም መሥራት እንዳልጀመረ ሲያስረዳ።

ይህ ውሳኔው ታዲያ ከአዲስ አበባ አርቆ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ወሰደው። በዩኒቨርስቲው የቲያትር እና ፊልም መምህር ሆኖ ለአንድ ዓመት ሠራ። ቀጥሎም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመልሶ ሁለተኛ ዲግሪውን በፊልም መማር ጀመረ። ወደ ኬንያ የወሰደውን ዕድል ያገኘው የማስተርስ ትምህርቱን ለመጨረስ አንድ ሴሚስተር ሲቀረው ነበር።

እንዴት ለዚህ ሥልጠና ለመመረጥ በቃህ?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ መልሱይህ ይመጣል ብዬ ባይሆንም ሁሌም ዝግጁ ነበርኩየሚል ነው።በተቻለ መጠን ራሴን በእውቀት እና በክህሎት ለማሳደግ እጥር ነበር። ስለዚህ ዕድሉ ሲመጣ ለሚጠየቁት ጥያቄዎች፤ ለነበሩት ፈተናዎች መልስ ነበረኝሲል ይመልሳል።

 አሸናፊነቴንለቤተሰቦቼ መናገር አልቻልኩም

ስለ የፊልም ኢንዱስትሪ ሲነሳአለን እንዴ?” ከሚባልበት ኢትዮጵያ ለመጣ ሰው የመልቲ ቾይስ ታለንት ፋክትሪን ሥልጠና መቀላቀል ቀላል ነገር አይደለም። የናይሮቢ ቆይታው ስለ ፊልምአዲስ ዕይታያገኘበት እንደሆነ ያነሳል። በተለያዩ የፌልም ፌስቲቫሎች እና ውድድሮች ላይ መሳተፍ አንደኛው የዚህ አይነቱ ሥልጠና ትሩፋት ነው።

ሀብታሙ የተወዳደረበት (JCS international young creatives’ awards) የተሰኘው የአጭር ፊልም ሽልማት ወጣት ባለተስጥዖዎችን ለማግኘት፣ ዕውቅ ለመስጠት እና ለማሳደግ ሲባል የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ውድድር ነው። ውድድሩ የሚካሄደው ሰላምን በተመለከተ በተሠሩ ባለ አንድ ደቂቃ አጫጭር ፊልሞች መካከል ነው።

ወጣቱ ፊልም ሠሪ፤ግጭት የሚበላው ወጣቱን ነው። ከዚያ ደግሞ ቀጣዩን ትውልድ። [ሕጻናት]ግጭት ሲመጣ መሠረተ ልማቶች ይወድማሉ፣ ቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ራሳቸውን መርዳት አይችሉምይላል። ይህንን ሀሳቡን ለማንጸባረቅ በፊልሙ ላይ ጦርነት የመጀመሪያው ገፋት ቀማሽ የሆኑትን ሕጻናት መምረጡን ይናገራል። በፊልሙጦርነትን በሕጻናት ጫማ ውስጥ ሆነን እንየውለማለት።

የፊልም ውድድሩ ዳኞችም ይህንን ሀሳብ ወደውለታል። የውድድሩ አንደኛው መመዘኛ በነበረው የሕዝብ ድምጽም ጥሩ ድምጽ ማግኘቱም ከሦስት አሸናፊ ወጣት ፊልም ሠሪዎች መካከል ቀዳሚው አድርጎታል።

ፊልሙ የተቀረጸው፣ ኤዲት የተደረገው እና የተላከው በውድድር ማስገቢያው የመጨረሻ ቀን እንደነበር የሚያስታውሰው ሀብታሙ፤በዚህ ዓመት ከተሳተፉኩ ይበቃል። በሚቀጥለው ዓመት ድጋሚ እወዳደራለሁማለቱን ይናገራል። ውድድሩን ማሸነፉ ኤሚ ኢንተርናሽናልዌብሳይት ላይ ተገልጾ ቢያይም ይፋዊ ኢሜል እስከሚደርሰው ድረስ አላመነም ነበር።

ማሸነፌን የሚገልጽ ኢሜይል ሲደርሰኝ ለጓደኞቼ ነገርኩኝ፣ ለትምህርት ቤቴ ኃላፊዎች ተናገርኩኝ። መጨረሻ ላይ ለቤተሰቦቼ ደወልኩኝ። ግን እንደአለመታደል ሆኖ በግጭት ምክንያት የሁሉም ስልክ አይሰራም። ወንድሜ ጋር፣ እህቴ ጋር፣ እናቴ ጋር ደወልኩኝ። ግን የአንዳቸውም ስልክ አይሰራምሲል በወቅቱ በአማራ ክልል ለሚገኙት ቤተሰቦቹን ደስታውን ማጋራት አለመቻሉን ይናገራል።

በአማራ ክልል በሚገኙ ታጣቂዎች እና በመንግሥት መካከል የሚደረገውን ውጊያ ተከትሎ በጊዜው በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ የኢንተርኔት አገልግሎት አሁንም ድረስ እንደተቋረጠ ነው።

ፊልሙን የሠራሁት ግጭት እንዲቆም ነው። ስለ ግጭት ነው ያወራሁት። በዚህ ፊልም ማሸነፌን ግን በጊዜው ለቤተሰቦቼ ማጋራት አልቻልኩምበማለት ስላቅ የሆነበትን አጋጣሚ ያነሳል።

የሀብታሙ እና የጦርነት አጋጣሚ ይህ ብቻ አይደለም። ከውድድሩ ሽልማቶች ውስጥ አንዱ በኒው ዮርክ የተካሄደውን 50ኛው የኢንተርናሽንል ኤሚ ዝግጅትን መሳተፍ ነበር። የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት በመቀስቀሱ ምክንያት ግን የዚህ ዓመት አሸናፊዎች ጉዞ ወደሚቀጥለው ዓመት ተዘዋውሯል። እንደ ሀብታሙ ገለጻ ይህ የሆነው አንዱ የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው ..ኤስ ኢንተርናሽናልየእስራኤል ኩባንያበመሆኑ ነው።

 የኢትዮጵያን ፊልም ኤክስፖርት ማድረግ እፈልጋለሁ

ከአምስት ዓመት በፊት ከዩኒቨርስቲ ሲመረቅ የፊልም ሥራን ለመቀላቀል ብቁ አይደለሁም ብሎ የነበረው ሀብታሙ፤አሁን አቅም አለኝየሚል እምነት ላይ መድረሱን ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ ሦስት የተለያዩ የፊልም ጽሁፎች እያዘጋጀ መሆኑንም ያክላል። የትኛው ፊልም ቀድሞ ለዕይታ ይቀርባል የሚለውን የሚወስነው ግንየትኛው ጽሁፍ ቀድሞ ፈንድ ያገኛልየሚለው እንደሆነም ይገልጻል።

ዕቅዴ የኢትዮጵያን ታሪክ መናገር ነው። የመጣሁት ከኢትዮጵያ ነው፤ የማውቀውም የኢትዮጵያን ታሪክ ነው። ስለማላውቀው ነገር ፊልም አልሰራምይላል። እንደ ዘመን ተጋሪዎቹ የፊልም ባለሙያዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ፊልም ለአለም ገበያ የማቅረብ እቅድም አለው።

እንደ አገር ክፍተት አለብን ብዬ የማምነው፤ ታሪካችንን ኤክስፖርት ማድረግ ላይ ነው። ታሪካችንን አውጥተን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ ችግር አለብን። እንደ ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ብዙ የኢትዮጵያ ፊልምን አማዞን እና ኔትፍሊክስ ላይ አይገኙም። [እነዚህ ማሰራጫዎች ላይ ያሉት] የኢትዮጵያ ፊልሞች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው። ይሄንን መስበር እፈልጋለሁይላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop