ፈረስ ለጭነት መጠቀም 60 ሺህ ብር የሚያስቀጣባት የኦሮሚያ ከተማ Leave a comment

የፊቼ ከተማ አስተዳደር ፈረስን ለጭነት አገልግሎት ማዋል በገንዘብ የሚያስቀጣ ተግባር ይሆናል ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ከአራት ወራት በኋላ ተፈጻሚ የሚሆነውን መመሪያ በመጣስ ፈረስን ለጋሪ አገልግሎት ተጠቅሞ የተገኘ በ60 ሺህ ብር ይቀጣል ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ውሳኔ የደረሰው ፈረስ በኦሮሞ ባሕል ያለውን ክብር እና ቦታ ዝቅ በማድረግ ለስቃይ እየተዳረገ በመሆኑ ነው ይላል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የፊቼ ከተማ የባሕል ና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ደጀኔ “ፈረስ፤ ጋሪ መጎተት የለበትም። ፈረስ ክብር አለው፣ በኦሮሞ ባሕል ትልቅ ቦታ አለው። በማይገባው ቦታ መገኘት የለበትም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አበራ ጨምረው ሲናገሩ፤ “ኦሮሞ ፈረስን ልክ እንደ ልጁ፤ እንደ የዓይን ብሌኑ በመመልከት እየተንከባከበ ሲጠቀም ነው የኖረው። አሁን ላይ ግን እንደምናስተውለው ለማይገባው ተግባር እየዋለ የተለያዩ ጉዳቶች እየደረሱበት ነው” ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ ፈረሰ ጋሪ መጎተት የለበትም የሚለው ሕግ የወጣው የዞኑ የባሕል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ከአባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲቄዎች እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው።

ይህን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ከአራት ወራት በኋላ ይህን መመሪያ ተፈጻሚ ማድረግ ይጀምራል። በዚህ መሠረት ፈረሰ ላይ ጋሪ ጭኖ የሚገኝ ሰው 60 ሺህ ብር ይቀጣል።

አቶ አበራ ፈረሰ ላይ ጭነት በመጫን ሕይወታቸውን እየገፉ ያሉ ሰዎች ለእንስሳው የሚያደርጉት እንክብካቤ “እጅግ በጣም የወረደ ነው” ይላሉ።

“ተጠቅመውበት ሲያረጅ እና ጉልበት ሲያጣ አውጥተው ይጥሉታል። ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ለፈረስ ያለውን ክብር እና ስርዓት የሚያሳጣ ነው” ብለዋል።

የፈረስ ባለ ጋሪዎች ዕጣ ምን ይሆናል?

ከከተማ አስተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በፊቼ ከተማ 234 ገደማ በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎች አሉ።

ፈረስን ለጋሪ አገልግሎት መጠቀም ስለሚከለክለው መመሪያ የከተማ አስተዳደሩ ከፈረስ ጋሪ አገልግሎት ሰጪ ሰዎች ጋር ንግግር ስለማድረጉ አቶ አበራ ይናገራሉ።

“በፈረስ የጋሪ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን ለአንድ ቀን ሰብስበን የማንቃት ስራ ሰርተናል። በጉዳዩ ላይም ተግባብተናል” ይላሉ።

በፈረስ ጋሪ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ባሉት አራት ወራት ውስጥ “የሥራ ዘርፋቸውን መቀየር ይችላሉ” ይላሉ አቶ አበራ።

“አንደኛው ያላቸው አማራጭ በፈረስ የሚጎተት ጋሪን በአህያ ወደሚጎተት ጋሪ መቀየር ነው” የሚሉት ኃላፊው፤ ከዚህ በተጨማሪም ባለ ጋሪዎችን በማደራጀት እና የገንዘብ አቅርቦት በማመቻቸት ወደዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪነት የሚሸጋገሩበት መፍጠር ሌላ አማራጭ ነው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop