በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ምክንያት “አገር አልባ ለመሆን ተቃርቤያለሁ” ሲሉ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ተናገሩ። ባለፈው ሳምንት ሰኞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ የተከለከሉት አቶ ልደቱ “ይህ እገዳ ከበኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሚበሩ ሌሎች አየር መንገዶች ላይም ጭምር መሆኑን ደርሼበታለሁ” ብለዋል።
አቶ ልደቱ ይህን ያሉት ባለፈው ሳምንት ሰኞ የካቲት 3/ 2017 ዓ.ም ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ ለዓለም አቀፍ ተቋማት እና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በጻፉት ደብዳቤ ነው።
እሁድ የካቲት 9/ 2017 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ “ወደ አገሬ የመመለስ ሕገ መንግስታዊ መብቴን የነፈገ ነው” ብለዋል።
የመዘዋወር ነጻነትን የሚደነግገው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው” ይላል።
“በዚህ ውሳኔ ምክንያት አገር አልባ ለመሆን ተቃርቤያለሁ” ያሉት አቶ ልደቱ ” ይህ የዘፈቀደ እርምጃ እንዲቀለበስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላይ የዓለም አቀፍ ጫና እንዲፈጠር” ጠይቀዋል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሳፈር ሲሞክሩ “በይፋ የጉዞ እገዳ ስለተጣለባቸው” መጓዝ አንደማይችሉ በአየር መንገዱ ኃላፊዎች እንደተነገራቸው አመልክተዋል።
በኋላም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው መንግስት የጉዞ ክልከላውን መጣሉን እንዳረጋገጡ አቶ ልደቱ ገልጸዋል።
የጉዞ እገዳው “በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ በሚበሩ አየር መንገዶች ላይም ጭምር መሆኑን” እንደደረሱበት አቶ ልደቱ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ ፈራሚ የሆነችበት የዓለም የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ከስምንት ዓመታት በፊት ያወጣው መመሪያ መመሪያ አገራት የመንገደኛ ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ምዝገባ ሥርዓት እንዲዘረጉ ያስገድዳል።
የመንገደኞች ቅድመ ጉዞ መረጃ የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ዘዴ ሲሆን፣ በረራው ከመነሳቱ በፊት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ተሰብስበው ወደ ድንበር ቁጥጥር ኤጀንሲዎች እንደሚተላለፉ መመሪያው ያትታል።
የተጓዦችን መረጃ ቀድሞ አለመላክ የአውሮፕላን ጉዞ እንዲዘገይ ወይም በመዳረሻ አገራት ለቅጣት ሊዳርግ እንደሚችል መመሪያው ላይ ሰፍሯል።
አቶ ልደቱ “ለዚህ ህገወጥ እርምጃ የተዳረኩት በፖለቲካዊ አመለካከቴ፤ በተለይም እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶች በአፋጣኝ እንዲቆሙ እና አጠቃላይ ሀገራዊ የሽግግር ሂደት እንዲተገበር በማሳየቴ ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ወደ አሜሪካን አገር ከመሄዳቸው በፊት ” በህገወጥ መንገድ በኢትዮጵያ መንግስት ለአምስት ወራት” ታስረው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ልደቱ፤ በሶስት የተለያዩ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች እንዲፈቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም “የሕግ አስከባሪ አካላት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በሕገወጥ መንገድ አስረውኛል” ብለዋል።
ይህ “የተራዘመ እና ፍትሃዊ ያልሆነ እስር” ከባድ የግል ጭንቀት እንዳስከተለባቸውም አቶ ልደቱ አክለዋል።
በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድጋፍና በሌላ የፍርድ ቤት ውሳኔ ለሕክምና ወደ አሜሪካ አገር ካቀኑ በኋላ ብዙም ሳይቆይ “የኢትዮጵያ መንግሥት “በአሸባሪነት እንደወነጀላቸው እና “የስም ማጥፋት ዘመቻ” እንደከፈተባቸው ጠቁመዋል።
አቶ ልደቱ ጤንነታቸው መሻሻሉን ተከትሎ “አሁን ያለው አገዛዝ አፋኝ ቢሆንም” ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ልደቱ አክለውም “ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘በምንም መልኩ ወደ ሀገሬ እንድመለስ እንደማይፈቀድልኝ’ በይፋ መግለጻቸውን ለማወቅ ችያለሁ’ ብለዋል።
“ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ተቃዋሚዎች ለማፈን ቆርጦ መነሳቱን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አቶ ልደቱ አክለዋል።
አቶ ልደቱ “በህይወቴ በሙሉ በትጋት ያገኘሁትን ንብረቴን መንግሥት ለመውረስ እየተዘጋጀ እንደሆነ ደርሼበታለሁ” ብለዋል።
“እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች የሚፈጸሙት ያለ ምንም ህጋዊ መሰረት ነው” ያሉት አቶ ልደቱ፤ “መፍትሄ ካልተበጀለት በሌሎች በርካታ ንፁሀን ኢትዮጵያውያን ላይ ሊወሰድ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው “በፈጠራ ክስ ስድስት ጊዜ ብታሰርም በ32 አመት የፖለቲካ ህይወቴ በምንም አይነት ወንጀል ተፈርዶብኝ አያውቅም” ብለዋል።
አቶ ልደቱ “እኔ እንደማምነው የመንግሥት እርምጃዎች ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው እኔ እና ሌሎች ሰላማዊ ትግል እንዳንቀጥል እና በመጪው ሀገራዊ ምርጫ እንዳንሳተፍ ለማድረግ ነው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
አቶ ልደቱ አያሌው በ1997 ዓ.ም. ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ በመሆኑ ግዙፍ እንቅስቃሴን ፈጥሮ የነበረው የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ጥምረት መሥራች ፓርቲዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የነበረው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር ሆነው ለረጅም ጊዜ መርተውታል።
አቶ ልደቱ አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ለአንድ የሥልጣን ዘመን የቆዩ ሲሆን፣ ከዚያም በኋላ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ጎልተው የሚታዩ ወጣት ፖለቲከኛ ሆነው ቆይተዋል።
ከአራት ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ የተፈጸመውን የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ግጭት እና ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ለእስር ከተዳረጉ ፖለቲከኞች መካከል አቶ ልደቱ አንዱ ነበሩ። የቀረበባቸው ክስም በምሥራቃዊቷ ቢሾፍቱ ከተማ አመጽን በማበረታታት እና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ በመያዝ ነበር።
ለወራት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ልደቱ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለሕክምና ወደ አሜሪካ ቆይተው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ ነው እገዳ እደተጣለባቸው እንደተነገራቸው የገለጹት።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)