ሶፊ ለ12 ዓመታት ያህል የወር አበባዋ ሲመጣ ያማታል። የሰውነት ክብደቷ ይጨምራል። ድባቴ እና ድካም ይሰማታል።
ከአሥር ሴቶች አንዷ ላይ የሚታየው የሆርሞን ችግር (ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም ወይም ፒሲኦኤስ) እንዳለባት ተነግሯታል። ሆኖም ሕክምና ለማግኘት ተቸግራለች።
ጤናዋን ማስተካከል የምትቸው በራሷ መንገድ እንደሆነ ተሰማት። ኢንስታግራም ላይ ኮርኒ ሲማንግ የተባለች ሰው ተዋወቀች።
ህመሟን እንደምታስወግደው ቃል ገባችላት። ሳይንስ ለፒሲኦኤስ እስካሁን ሕክምና አላገኘም።
ኮርኒ ግን ለታካሚዎች በቤተ ሙከራ ምርመራ በማድረግ መመገብ ያለባቸውን ታዛለች። ለማማከር እና ተጨማሪ መድኃኒቶች ለመስጠት 3,600 ዶላር ታስከፍላለች።
ሶፊ የኮርኒን ምክር እና መድኃኒት ለማግኘት ገንዘብ መክፈል ጀመረች።
የማህፀን ሐኪም እና የሴቶች ጤና መምህርት ዶ/ር ጄን ገንተር እንደምትለው፣ ኮርኒ የምትሰጠውን ምርመራ ለማድረግ ሙያዊ ብቃት የሌላት ሲሆን፣ ሕክምናውም በስፋት ጥናት አልተደረገበትም።
ሶፊ ለአንድ ዓመት የኮርኒን ሕክምና ተከታትላ ውጤት ሳታገኝ ስትቀር ሕክምናውን አቋረጠች።
“ሕክምናውን ከመጀመሬ በፊት ከነበረው በባሰ ከሰውነቴ ጋር ተጣልቼ እና አመጋገቤ ተበላሽቶ ነው ሕክምናውን ያቋረጥኩት። የፒሲኦኤስ ህመሜም ለውጥ አላሳየም” ትላለች።
ኮርኒ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንድትሰጥ ብትጠየቅም ምላሽ አልሰጠችም።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው የሕክምና ምክር የሚሰጡ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እየተበራከቱ ነው።
ፒሲኦኤስ ሕክምና የሌለው በመሆኑ እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መፍትሄ ለመስጠት ቃል በመግባት በርካታ ገንዘብ ያገኛሉ።
ሐሰተኛ ምክር እና መድኃኒት ያቀርባሉ።
አንዳንዶቹ ራሳቸውን የአመጋገብ አማካሪ ብለው ሲጠሩ፣ የተቀሩት ደግሞ የሆርሞን ጉዳይ አማካሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
እነዚህን ሙያዎች በሳምንታት ውስጥ በበይነ መረብ መማር ይቻላል።
ቢቢሲ ፒሲኦኤስን በተመለከተ በቲክ ቶክ እና በኢንስታግራም በአራት ቋንቋዎች መረጃ የሚሰጡ ገጾችን ተከታትሏል።
ግማሾቹ ሐሰተኛ መረጃ እንደሚያሠራጩ ለማወቅ ተችሏል። በእንግሊዝኛ፣ ስዋሂሊ፣ ሂንዲ እና ፖርቹጊዝ ነው መረጃዎች የሚተላለፉት።
በእንግሊዝኛ የሚለቀቁት ይዘቶች በሕንድ፣ በናይጄሪያ፣ በኬንያ እና በብራዚል ተመልካች አላቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ 70 በመቶ ያህል ሴቶች ፒሲኦኤስ እንዳለባቸው አልተነገራቸውም።
ህመሙ እንዳለባቸው ካወቁ በኋላም ሕክምና ለማግኘት ይቸገራሉ።
“ያለውን ክፍተት በመጠቀም የሚነግዱበት አሉ” ስትል ዶ/ር ጄን ታስረዳለች።
ስለ ፒሲኦኤስ ከሚዘዋወሩ ሐሰተኛ መረጃዎች የተወሰኑትን እንመልከት፦
- ፒሲኦኤስ አመጋገብን በማስተካከል ይድናል
- ፒሲኦኤስን ለማዳን አነስተኛ ካርቦሃይድሬት እና አነስተኛ ስብ ያላቸው ምግቦች መመገብ ያስፈልጋል
- ፒሲኦኤስ የሚከሰተው በእርግዝና መከላከያ መድኃኒቶች አማካይነት ሲሆን፣ እነዚህ እንክብሎች ህመሙን ያባብሳሉ
- ፒሲኦኤስ በመደበኛ ሕክምና ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ አይጠፋም
-
ከምግብ ውስጥ ካሎሪ መቀነስ አወንታዊ ሚና እንዳለው የሚያሳይ ጥናት የለም። ኪቶ የተሰኘው የአመጋገብ ዓይነት ህመሙን ሊያባብስ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፒሲኦኤስ የሚከሰተው በእርግዝና መከላከያ መድኃኒቶች አይደለም። አንዳንድ ሴቶች እንዲያውም ህመማቸው እንዲቀንስ እንደሚረዳቸው ይናገራሉ።
የቲክ ቶክ ቃል አቀባይ በገጻቸው ላይ አሳሳች፣ ጎጂ ወይም ሐሰተኛ መረጃ እንዲሠራጭ እንደማይፈቅዱ ይናገራሉ።
የፌስቡክ ባለቤት ሜታ ቃል አቀባይም እንዳሉት፣ የሴቶችን ጤና በተመለከተ መረጃ በገጹ ላይ እንዲሠራጭ የሚፈቅዱ ሲሆን፣ ከሦስተኛ ወገን ጋር በመሆን ሐሰተኛ መረጃን ለማስወገድ ይሠራሉ።
ፒሲኦኤስ ምንድን ነው?
ፒሲኦኤስ የሆርሞች ችግር ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከ8 – 13 በመቶ የሚደርሱ ሴቶችን ይጎዳል።
ህመም የበዛበት እና የተዛባ የወር አበባ፣ ከፍተኛ የፀጉር ዕድገት እና የሰውነት ክብደት መጨመር ከምልክቶቹ መካከል ይገኙበታል።
መኻንነትን ከሚያስከትሉ መካከል አንዱ ፒሲኦኤስ ነው። ያለ ሕክምና እርዳታ ህመሙ እያለባቸው የሚወልዱ ሴቶች ግን አሉ።
ከእነዚህ አንዷ የሆነችው ቫሺናቪ በሕንድ፣ ባንግሎር ነው የምትኖረው።
አያና ሻርማ የተባለች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪን ትከተል ነበር።
ለህመሟ “ተፈጥሯዊ” ፈውስ እንደምትሰጣት ነግራት ነበር። ቫሺናቪ አመጋገቧን እንድታስተካከል ምክር ተሰጥቷታል።
አንያ ሻርማ እንደ ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የሰውነት ክብደት መቀነስ ላይ ያተኮረ ምክር ትለግሳለች።
ቫሺናቪ በቀን ከ1,000 እስከ 1,200 ካሎሪ እንድትመገብ ተነግሯታል።
በእርግጥ ጤናማ አመጋገብ የፒሲኦኤስ ምልክቶችን ይቀንሳል። ሆኖም ምግብ ላይ ያልተገባ ገደብ ማስቀመጥ ለአመጋገብ መዛባት ያጋልጣል።
ሴቶች በቀን ውስጥ በአማካይ 2,000 ካሎሪ እንዲመገቡ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ቫሺናቪ ምግብ በመቀነሷ ምክንያት የወር አበባዋ ለስድስት ወራት ተቋርጧል።
የሰውነት ክብደቷ በቆሎ ባለመቀነሱ ሃፍረት ይሰማት ነበር።
“ሌሎች አንያ የምታማክራቸው ሴቶች በፍጥነት ሰውነታቸው ቀነሰ። ለውጥ ማየት የምትለው ሰውነቴ ሲቀነስ ነው ብዬ ስላሰብኩ የሰውነቴ ክብደት ሳይቀንስ ሲቀር ተሸማቀቅኩ” ትላለች።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዋ አንያ እንደምትለው የፒሲኦኤስ ምልክቶችን መቀነስ ቢቻልም ህመሙን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አይቻልም።
ማኒሻ የተባለችው የባንግሎር ነዋሪ እንደ ቫሺናቪ ያለ ችግር ገጥሟታል።
ሰውነቷ ላይ የሚወጣው ፀጉር፣ የሰውነቷ ክብደት መጨመር እና ከፍተኛ የወር አበባ ህመም ሲበረታባት ልክ እንደ ቫሺናቪ እና ሶፊ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ፊቷን አዞረች።
“ፒሲኦኤስ ስላለባቸው መውለድ አይችሉም በሚል ትዳራቸው የፈረሰ ሴቶች አውቃለሁ። ስለዚህም ራሴን ለማዳን ቆርጬ ተነሳሁ” ትላለች።
በፆም፣ በኪቶ አመጋገብ ስልት እና በሌላም መንገድ ራሷን ለማዳን ሞክራለች።
ፍቱን የተባሉ መድኃኒቶችንም ሞክራለች።
ከሞከረቻቸው መድኃኒቶች አንዱ የሕንድ ባህላዊ መድኃኒት የሆነው አሽዋጋንዳ ነው።
የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የምዕራቡ ዓለም መድኃኒቶች ፒሲኦኤስን እንደሚያባብሱ ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ማኒሻ በባህላዊ መድኃኒት ሕመሟ አልጠፋም።
“ራሴን ለማጥፋት ያሰብኩበት ጊዜም ነበር። ሌላው ሰው እየተሻለው ለምን እኔን አይሻለኝም? ብዬ ተጨነቅኩ” ትላለች።
ማኒሻ በ29 ዓመቷ ስኳር እንዳለባት ተነገራት።
ፒሲኦኤስ ያለባቸው ሴቶች ስኳር ማብላላት ያስቸግራቸዋል። ለስኳር ተጋላጭ ናቸው። ቅድመ የስኳር መከላከያ መድኃኒቶች መውሰድ እና ለፒሲኦኤስ መድኃኒት መውሰድ ለጤናቸው ይመከራል።
ማኒሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ፒሲኦኤስ ለመታከም ወደ ሆስፒታል ስትሄድ እምብዛም ድጋፍ አላገኘችም።
ማርገዝ ስትፈልግ ወደ ሆስፒታሉ እንድትመለስ ተነገራት።
የማህፀን ሐኪም እና የሴቶች ጤና መምህርት ዶ/ር ጄን ገንተር እንደምትለው፣ የሕክምና እርዳታ ማጣት በህመሙ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራል።
ሐሰተኛ መረጃ ሴቶች አስፈላጊውን እርዳታ ሳያገኙ እንዲዘገዩ ምክንያት ነው። ለስኳር ህመም እስከ መጋለጥ ድረስ የሚያደርሰውም ሳይታከሙ መቆየት ነው።
ሜድሊን በናይጄሪያ የሕክምና ተማሪ ናት።
ስለ ፒሲኦኤስ ያለውን የተዛባ ምልከታ ለመቅረፍ ከሚሞክሩ አንዷ ናት።
ስለ ፒሲኦኤስ ያለውን የተዛባ ምልከታ ለመቅረፍ ከሚሞክሩ አንዷ ናት።
አመጋገብ በማስተካከል እና መድኃኒት በመውሰድ ውጤት ያላገኙ ሴቶች የሕክምና ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ ታበታታለች።
“ፒሲኦኤስ እንዳለብኝ ሲነገረኝ መገለል ደርሶብኛል። ራሴን ስላልተንከባከብኩ የመጣ ህመም አድርገው የወሰዱት አሉ። አትወልድም ተብሎ ስለሚታሰብ ማንም እኔን ማግባት አይፈልግም” ትላለች።
በጊዜ ሂደት ግን እውነታውን ተቀብላለች። ፀጉሯ ላይ ያለውን ለውጥና የሰውነቷን መጨመር በፀጋ ነው የተቀበለችው።
“ሁኔታውን መቀበሌ የተለየሁ ያደርገኛል” ትላለች።
በዩናይትድ ኪንግደም ፒሲኦኤስ ላይ የሚሠራው የበጎ ፈቃድ ተቋም ውስጥ የምትሠራው ሳሻ ኦቲ እንደምትለው፣ በሕክምና እገዛ ፒሲኦኤስ ያለባቸው ሴቶች መውለድ ይችላሉ።
ዶ/ር ጄንም የሕክምና ባለሙያዎች ማማከርን ታበረታታለች።
የማህፀን እና ፅንስ ባለሙያዎችን ሴቶች ማማከር እንዳለባቸው ሐኪሟ ታስረዳለች።
ማኒሻ ስኳር እንዳለባት ከተነገራት በኋላ ሜታፎርሚን መውሰድ ጀምራለች። በዚህም ለውጥ እያየች ነው።
ቫሺናቪ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለውጥ ለማግኘት እየሞከረች ትገኛለች።
ሶፊ ከአመጋገብ አማካሪ ጋር በመሆን ክትትል እያደረገች እንደሆነ ትናገራለች። ሰውነቷ እየቀነሰ እና ለውጥ እያየች ነው።
ሴቶቹ ለፒሲኦኤስ ዘላቂ እና ፍቱን መድኃኒት የሚገኝበትን ቀን ይጠባበቃሉ።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)