የጋዛ ሰርጥን የሚቆጣጠረው ሐማስ፤ እስራኤል እየፈጸመች ያለውን “ጥቃቷን ካላቆመች” በቀር ታጋቾችን እንደማይለቅ አስታውቋል።
እስራኤል እንደምትለው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተገባው የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነት ከተጣሰ በኋላ 2 ሺህ ያህል የሐማስ ወታደሮችን ገድላለች። በተኩስ አቁም ፋታው100 ያክል ታጋቾችን መለቀቃቸው ይታወሳል።
መስከረም መጨረሻ በሐማስ ታግተው ከተወሰዱ ሰዎች መካከል 120 ያህሉ አሁንም በሐማስ ቁጥጥር እንዳሉ ይገመታል።
የተባበሩት መንግሥታት ጦርነቱ እንዲቆም የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለ ነው።
አሜሪካ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያረቀቀው የመፍትሔ ሐሳብ እንዳሳሰባት ትገልጻለች።
ለአንድ ሳምንት ያህል የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ የምግብ እርዳ የገባ ሲሆን፤ እስራኤል እና ሐማስ የሚያደርጉት ጦርነት ከቀጠለ የጋዛ ሕዝብ ለከፋ ረሃብ እንደሚጋለጥ የተባበሩት መንግሥታት እያሳሰበ ይገኛል።
አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ድርድር እየተደረገ ሲሆን ረቡዕ የነበረው ስብሰባ ያለስኬት ተጠናቋል።
ሐማስ ባወጣው መግለጫ “ሙሉ በሙሉ ጥቃቱ እስካልቆመ ድረስ ስለ እስረኞችም ሆነ ስለ ታጋቾች ልውውጥ ንግግረእ አይኖርም የሚለው የፍልስጤም ብሔራዊ ውሳኔ ነው” ብሏል።
መግለጫው ሌላ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድንን ያማከለ ይሁን አይሁን ግልፅ አይደለም። ኢስላሚክ ጂሃድ የተሰኘው አነስ ያለ ቡድን ከሐማስ በተጨማሪ እስራኤላዊያንን አግተው ከያዙ መካከል ነው።
የሐማስ መግለጫ የእስራኤል መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነው።
እስራኤል እንደምትለው ከሐማስ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ብቸኛው አማራጭ ወታደራዊ እርምጃና የነብስ አድን ሥራ ነው።
ነገር ግን ይህን እርምጃ እስካሁን ድረስ ብዙም ውጤታማ አይደለም።
እሰራኤል እስካሁን ኦሪ ሜጊዲሽ የተባለ አንድ ታጋች ብቻ ነው እስካሁን ማስለቀቅ የቻለችው።
የእስራኤል መንግሥት ታግተው ከተወሰዱ እስራኤላዊያን ቤተሰቦች ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ሲሆን አንዳንዶች ኃይል መጠቀም አማራጭ አይደለም ይላሉ።
ነገር ግን እስራኤል ጦርነቱን ብታቆም ሐማስ ሙሉ በሙሉ ወታራዊ እንቅስቃሴዎቹን ያቆማል ወይ የሚለው ሌላኛው ጥያቄ ነው።
የእስራኤል መንግሥት ደግሞ የሐማስን አቅም ክፉኛ ካላደቀቀ በቀር ጦርነቱን ለማቆም ዝግጁ አይደለም።
ይህ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ ላሉት የጋዛ ነዋሪዎች መልካም ዜና አይደለም።
እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት 20 ሺህ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ ከሚመራው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል። ከእነዚህም መካከል 8 ሺህ ሕፃናት እና 6200 ሴቶች ሲሆኑ ከ50 ሺህ በላይም ቆስለዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዝዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazonnnn