በሊቢያ እገታ ሥር ያለችው ኢትዮጵያዊት ሁኔታ እና የሱዳን ስደተኛ ሴቶች ስቃይ…… Leave a comment

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ታሪክ አንዳንዶችን ሊረብሽ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።

ኢትዮጵያዊቷ ነሒማ ጀማል ስትሰደድ ሕልሟ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ማቅናት ነበር። ነገር ግን ይህ ያሰበችው ሳይሳካ ቀርቶ በሊቢያ ታጣቂዎች እጅ ላይ ወድቃለች።

በቅርቡ ነሒማ እና ሌሎች ስደተኞች እጅና እግራቸው ተጠፍሮ፤ አፋቸው በጨርቅ ተጠቅጥቆ ስቃይ ሲደርስባቸው የሚያሳይ ፎቶ ተለቋል።

ፎቶዎቹን እና ቪድዮውን ለሕዝብ ይፋ ያደረገው ሬፊውጂስ ኢን ሊቢያ የተባለው ድረ-ገፅ ነው።

ነሒማን ያገቷት ታጣቂዎች 6 ሺህ ዶላር እንዲከፈላቸው ሻሸመኔ ለሚገኙት ቤተሰቦቿ መልዕክት መላካቸውን እህቷ ኢፍቱ ጀማል ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።

ታጣቂዎቹ የማስለቀቂያ ገንዘብ ከጠየቁ ጥቂት ሳምንታት ቢቆጠሩም አሁንም ነሒማ በቁቁጥራቸው ሥር ናት።

ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ቤተሰቡ እስካሁን ማሰባሰብ የቻለው 300 ሺህ ብር ሲሆን ታጣቂዎቹ ደግሞ የሚፈልጉት 750 ሺህ ብር ነው። በአሁኑ ወቅት ቤተሰቡ ያሰባሰበውን ብር ለታጣቂዎቹ መላኩን ቢቢሲ አረጋግጧል።

የነሒማ ቤተሰቦችም አጋቾቿ ልባቸው ራርቶ ልጃችንን ይለቁልናል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

ነሒማ ከስምንት ወራት በፊት ነበር የ11ኛ ክልፍ ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሊቢያ የተሰደደችው።

ሊቢያ በተለይ ለጥቁር አፍሪካዊያን ስደተኞች ‘ሲኦል’ ሆናለች። ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ በርካታ ሱዳናዊያንም ሀገራቸው ውስጥ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በመሸሽ ወደ ሊቢያ ያቀናሉ።

ባለፈው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ለደኅንነታቸው ሲሉ ከባለቤቷ እና ከስድስት ልጆቿ ጋር ከሱዳን ተሰዳ ሊቢያ የምትገኘው ለይላ፤ ማንም እንዳይሰማት ድምጿን ቀንሳ በስልክ ስትናገር ያለችበትን ሁኔታ “በሽብር ውስጥ ነው የምንኖረው” ስትል ትገልጸዋልቸ።

እሷን ጨምሮ ወደ ሊቢያ በሕገወጥ መንገድ የተሻገሩ ሱዳናውያንን ቢቢሲ ያናገረ ሲሆን፣ ለደኅንታቸው ሲልም ስማቸው ተቀይሯል።

በአውሮፓውያኑ 2023 በተቀሰቀሰው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በኦምዱርማን የሚገኘው ቤቷ እንዴት እንደተወረረ በተንቀጠቀጠ ድምጽ ታስረዳለች።

ቤተሰቡ በመጀመሪያ ወደ ግብፅ አቀና። ለሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች 350 ዶላር ከፍለው ወደ ሊቢያ ተሻገሩ። በሊቢያ የተሻለ ሕይወት እንደሚገጥማቸው፤ በጽዳት እና በመስተንግዶ ሥራ መሠራማት እንደሚችሉ ተነገራቸው።

ልክ ድንበሩን እንደተሻገሩ ግን ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እንዳገቷቸው፣ እንደደበድቧቸው እና ተጨማሪ ገንዘብ እንደጠየቋቸው ለይላ ተናግራለች።

“ልጄ ፊቱ ላይ ደጋግሞ ከተመታ በኋላ የህክምና እርዳታ አስፈልጎት ነበር” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

ምክንያቱን ሳይነግሯቸው አዘዋዋሪዎቹ ከሦስት ቀናት በኋላ ለቀቋቸው። ቤተሰቡ ወደ ምዕራብ ሊቢያ ከተጓዘ እና ቤት ከተከራዩ በኋላ ሕይወታቸው መሻሻል እንደሚጀምር ላይላ ጠብቃ ነበር።

አንድ ቀን ግን ባለቤቷ ሥራ ፍለጋ ወጥቶ ሳይመለስ ቀረ።። ከዚያም የ19 ዓመቷ ልጇ ቤተሰቡ በሚያውቀው ሰው ተደፈረች።

“ልጄ የደረሰባትን ነገር ከተናገረች ታናሽ እህቷን እንደሚደፍሯት ነግሯታል” ትላለች።

ቤት አከራያቸው ስለዛቻው ከሰሙ ቤተሰቡ ይባረራል በሚል ፍራቻ ድምጿን ቀንሳ ትናገራለች።

አሁን በሊቢያ ተይዘው እንደሚገኙ ለይላ ተናግራለች። ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚከፍሉት ምንም ገንዘብ የላቸውም። በጦርነት ወደምታመሰው ሱዳንም መመለስ አይችሉም።

ምንም ዓይነት ምግብ የለንም” ከማለት ባለፈ ልጆቿ ትምህርት ቤት እንዳልገቡ ተናግራለች “ሌሎች ልጆች ብዙ ጊዜ ስለሚደበድቡት እና ጥቁር ብለው ስለሚሰድቡት ልጄ ከቤት መውጣትን ይፈራል።”

ስደተኛ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

በ2023 በሱዳን ጦር ኃይል እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከጀመረ በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሱዳንን ለቀው ተሰደዋል። ሁለቱ ወገኖች በ2021 በጋራ መፈንቅለ መንግስት ቢያካሂዱም በአዛዦቻቸው መካከል በተነሳው የሥልጣን ሽኩቻ አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ አድርገዋታል።

ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ረሃብ ወደ አምስት አካባቢዎች ተዛምቷል። ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሽ የሚሆነው ማለትም 24.6 ሚሊዮን የሚጠጋው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ከ210 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች በሊቢያ ይገኛሉ ብሏል።

ቢቢሲ በመጀመሪያ ወደ ግብፅ የሄዱ አምስት ሱዳናውያን ቤተሰቦችን አነጋግሯል። ሁሉም ዘረኝነት እና ጥቃት እንደደረሰባቸው በመግለጽ የተሻለ የሥራ ዕድል ለማግኘት በሚል ተስፋ ወደ ሊቢያ ያነቀኑ ናቸው። በስደት እና ጥገኝነት ጠያቂ ጉዳዮች ተመራማሪ በኩል ነበር ቢቢሲ ያገኛቸው።

ሳልማ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ግብፅ ካይሮ ውስጥ ከባለቤቷ እና ከሦስት ልጆቿ ጋር ትኖር እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች። በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ግብፅ በመግባታቸው ምክንያት በዚያ ለሚኖሩ ስደተኞች ሁኔታው እየተባባሰ ሄደ።

ወደ ሊቢያ ለመዛወር ቢወስኑም ግን እዚያ የሚጠብቃቸው ነገር “ሲኦል” ነበር ስትል ሳልማ ተናግራለች።

ድንበሩን እንዳቋረጡ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ቁጥጥር ስር በሚገኝ መጋዘን ውስጥ እንዲኖሩ መደረጉን ትገልጻለች። ሰዎቹ በግብፅ ድንበር ላይ ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በቅድሚያ የሚከፈል ገንዘብ ቢፈልጉም በጊዜ ማግኝት አልተቻለም።

ቤተሰቧ በመጋዘኑ ውስጥ ለሁለት ወራት ያህል አሳልፏል። በአንድ ወቅት ደግሞ ሳልማ ከባለቤቷ ተለይታ ወደ ሴቶች እና ህጻናት ክፍል ተወሰደች። በክፍሉ ውስጥ እሷ እና ሁለቱ ታላላቅ ልጆቿ ገንዘቡን እንዲከፍሉ የተለያዩ ጥቃቶች ይደርስባቸው እንደነበር ትናገራለች።

“ግርፊያቸው በሰውነታችን ላይ ጠባሳ ትቶ ነበር። ሴት ልጄን ይደበድቡ እና እያየሁኝ የወንድ ልጄን እጆች ምድጃ ውስጥ ይከቱ ነበር።”

“አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም አብረን እንድንሞት እመኝ ነበር። ሌላ መውጫ መንገድ አላስብም ነበር።”

ልጆቿ ባጋጠማቸው ነገር ተጎድተው እንደነበር ሳልማ ተናግራ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በራስ የመተማመን ስሜት አጥተዋል ስትል ድምጿን ዝቅ አድርጋ ቀጠለች።

“ወደ የተለየ ክፍል ይወስዱኝ ነበር። ‘ወደ መደፈሪያ ክፍል’ በመውሰድ በየጊዜው የተለያዩ ወንዶች ጋር ይወስዱኝ ነበር። ከእነርሱ የአንዱን ልጅ አረገዝኩኝ” ብላለች።

በግብፅ ከምትገኝ ጓደኛዋ በኩል የተወሰነ ገንዘብ በማሰባሰቧ አዘዋዋሪዎች ቤተሰቡን ለቀቁ።

ጽንሱን ለማቋረጥ በጣም እንደረፈደ ሐኪም ነገራት። ባለቤቷ ማርገዟን ሲያውቅ እሷን እና ልጆቹን ጥሎ ጠፋ። ይህም መተኛ ቦታ እንዲያጡ፤ ከቆሻሻ መጣያ የተረፈውን እንዲበሉ እና መንገድ ላይ እየለመኑ ለመኖር አስገደዳቸው።

በሊቢያ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኝ እርሻ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ መቆየት ቢችሉም ቀኑን ሙሉ በትንሽ ምግብ ለማሳለፍ ተገደዱ። በአቅራቢያው ካለ ጉድጓድ የተበከለ ውሃ በመጠጣት ጥማቸውን ለመቁረጥ ቻሉ።

“(ታላቁ) ልጄ ቃል በቃል በረሃብ ልሞት ነው ሲል መስማቴ ልቤን ሰብሮታል” ሰትል ሳልማ ገለጸች።

“በጣም ርቦታል። እኔ ግን ምንም የለኝም። እሱን ለመመገብ ጡቶቼ እንኳ በቂ ወተት የላቸውም።”

በሱዳን ጦርነት የወደመ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,በሱዳን ጦርነት የወደመ አካባቢ

በ40ዎቹ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ሱዳናዊቷ ጀሚላም በሊቢያ የተሻለ ሕይወት እንደሚጠብቃቸው በሱዳን ማኅበረሰብ ዘንድ የሚወራውን ነበር የምትጠብቀው።

በአውሮፓውያኑ 2014 በሱዳን ምዕራባዊ ዳርፉር አካባቢ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ሸሽታ በግብፅ ለዓመታትን ካሳለፈች በኋላ በ2023 ወደ ሊቢያ አቀናች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሴት ልጆቿ በተደጋጋሚ ተደፍረዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የተደፈሩት በ19 እና 20 ዓመታቸው ነበር።

“በታመምኩበት ወቅት ለጽዳት ሥራ ላኳቸው። ማታ በአፈር እና በደም ተሸፍነው ይመለሱ ነበር። ራሳቸው እስኪስቱ ድረስ አራት ሰዎች ደፈሯቸው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ጀሚላም ከእሷ በጣም በሚያንስ እና ቤቱን እንድታጸዳለት በጠየቃት ሰው ተደፍራ ለሳምንታት ታስራ እንደነበር ተናግራለች።

“አስጸያፊ ጥቁር” ይለኝ ነበር። ደፈሮኝ “ሴቶች የተፈጠሩት ለዚህ ነው” እንዳላት ታስታውሳለች።

“እዚህ ያሉ ልጆች እንኳን ለእኛ ክፉ ናቸው። እንደ አውሬ አድርገው ይቆጥሩናል። ጥቁር እና አፍሪካዊ በመሆናችን ይሰድቡናል። እነሱ ራሳቸው አፍሪካውያን አይደሉምን?” ጀሚላ ትጠይቃለች።

ሴት ልጆቿ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደፈሩ ጀሚላ ሆስፒታል ወስዳቸው ጉዳዩንም ለፖሊስ አሳወቃለች። የፖሊስ መኮንኑ ስደተኛ መሆናቸውን ሲያውቅ ግን ጀሚላ ክሱን እንድተተው ካልሆነ ግን ልትታሰር እንደምትችል አስጠንቅቋቋታል። ይህ የሆነው በምዕራብ ሊቢያ ነበር።

ሊቢያ የ1951 የስደተኞች ስምምነትን ወይም የ1967 የስደተኞች ፕሮቶኮል አልፈረመችም። ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችንም “ሕገወጥ ስደተኞች” አድርጋ ትቆጥራለች።

አገሪቱ ለሁለት የተከፈለች ሲሆን፣ ሁለቱም ክፍል በተለያየ መንግሥት ይመራሉ። በምሥራቅ ያሉ ስደተኞች ሳይታሰሩ ቅሬታዎችን ማቅረብ እና የጤና አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት ስለሚችሉ ሁኔታው ቀለለ ያለ ነው ሲል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሊቢያ ክራይምስ ዎች ገልጿል።

በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በሚተዳደሩ መደበኛ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት የተለመደ ቢሆንም፤ በሊቢያ በተለይም በምዕራብ በሚገኙ መንግሥታዊ የማቆያ ማዕከላትም ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አለ።

ስደተኞች በሊቢያ

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

የምስሉ መግለጫ,ስደተኞች በሊቢያ

ልጆቿን ለመመገብ ፕላስቲክ ከቆሻሻ መጣያ የምትሰበስበው ሱዳናዊቷ ሃና በምዕራብ ሊቢያ ታፍና ወደ ጫካ ከተወሰደች በኋላ መሳሪያ በታጠቁ ወንዶች እንደተደፈረች ተናግራለች።

በማግስቱ በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግለት ስታቢሊቲ ሰፖርት (ኤስኤስኤ) ወደ ተባለ ተቋም ወሰዷት። ለምን እንደታሰረች ግን ለሃናን የገለጸላት የለም።

“ወጣቶች እና ወንዶች እያየሁ ተደብድበው ልብሳቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያወልቁ ተገድደዋል” ስትል ሃናን ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ለቀናት እዚያ ነበርኩ። ባዶው ወለል ላይ ተኝቻለሁ። ጭንቅላቴን የማሳርፈው በፕላስቲክ ስሊፐርቼ ላይ ነበር። ከሰዓታት ልመና በኋላ ወደ መጸዳጃ ቤት እንድሄድ ፈቀዱልኝ። ጭንቅላቴ ላይ በተደጋጋሚ ተደብድቤያለሁ።”

የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ስደተኞች በሊቢያ በደል እንደሚደርስባቸው ከዚህ ቀደም በርካታ ሪፖርቶች ቀርበዋል። ቢቢሲ ካነጋገራቸው ሴቶች አንዳቸውም ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ባያቅዱም ሊቢያ ወደዚያ ለመሻገር ቁልፍ መንገድ ናት።

በ2022 አምነስቲ ኢንተርናሽናል “በዓለም አቀፍ ሕግ ሕገወጥ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ ጣልቃ ገብነት እና በስደተኞች የዘፈቀደ እስር፣ ማሰቃየት፣ የግዳጅ ሥራ እና ሌሎች አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም ወንጀሎች” ኤስኤስኤ በተባለው ቡድን ላይ ክስ አቅርቧል።

በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ የሚገኘው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ለአምነስቲ በሰጡት ምላሽ ሚኒስቴሩ በኤስኤስኤ ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር እንደሌለው አስታውቋል። ተቋሙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ ዲቤህ ሲሆን፣ ጽህፈት ቤቱ ለቢቢሲ ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም።

የሊቢያ ክራይምስ ዎች ለቢቢሲ እንደተናገረው ከሆነ በስደተኞች ላይ ስልታዊ የሆነ የፆታ ጥቃት በትሪፖሊ የሚገኘውን አቡ ሳሊም እስር ቤትን ጨምሮ በኦፊሴላዊ የስደተኞች ማቆያ ማዕከላት ጭምር ይፈጸማል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በ2023 ባወጣው ሪፖርት በአቡ ሳሊም ውስጥ “የወሲብ እና አካላዊ ጥቃት ሪፖርቶች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህም ስልታዊ በሆነ መንገድ ማራቆትን እና የሰውነት አካልን ፍተሻን እንዲሁም መደፈርን ይጨምራል” ብሏል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና በትሪፖሊ የሚገኘው ሕገወጥ ስደትን ለመዋጋት የተቋቋመው መምሪያ ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ሳልማ አሁን እርሻውን ለቃ በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ሌላ ቤተሰብ ጋር ብትሄድም እሷ እና ቤተሰቧ አሁንም የመፈናቀል እና እንግልት ዛቻ ይደርስባቸዋል።

በደረሰባት ነገር ወደ ቤቷ መመለስ እንደማትችል ትናገራለች።

“ቤተሰቡን አሳፍሬአለሁ ይላሉ። አስከሬኔን እንኳ ስለመቀበላቸው እርግጠኛ አይደለሁም” ስትል ገልጻለች።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop