በአሜሪካዋ ግዛት ካሊፎርኒያ ውስጥ ተከስቶ ሳምንት ባለፈው ሰደድ እሳት ምክንያት እስካሁን 24 ሰዎች ሞተዋል።
ከሟቾቹ መካል 16ቱ ኢተን የተሰኘው እሳት በተከሰተበት አካባቢ የተገኙ ሲሆን፣ ስምንቱ ደግሞ በፓሊሳዴስ አካባቢ መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።
በተጨማሪም ቢያንስ 16 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት እንደማይታወቅ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በሎስ አንጀለስ በሰደድ እሳቱ ምክንያት ወደ 180 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንዲለቁ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል። ወደ 200 ሺህ ነዋሪዎች ደግሞ ለመልቀቅ ተዘጋጁ የሚል ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል።
በሎስ አንጀለስ የምትኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት በላይ ፈረደ በዚህ ሰደድ እሳት የተነሳ ለተጎዱ ነዋሪዎችን ድጋፍ ከሚሰጡ መካከል አንዷ ናት።
በራሷ ተነሳሽነት ከሁለት ልጆቿ ጋር ድጋፍ አድርጋለች። “ውሃ፣ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት፣ የሕጻናት ዳይፐር፣ ትንሽ የመድኃኒት እርዳታ ሰጥቻለሁ” ትላለች።
መኖሪያ ቤቶችን እና ተቋትን እያወደመ ባለው ሰደድ እሳት እምብዛም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ እንዳልተጎዳ ትዕግስት ተናግራለች።
“የእሳት ቃጠሎው የተነሳው በብዛት ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አካባቢ አይደለም” ስትልም አስረድታለች።
በሎስ አንጀለስ ታሪክ እጅግ አስከፊ በሆነው የፓሲፊክ ፓሊሳዴስ እሳት 5300 ያህል ቤቶች ወድመዋል።
አምስት ሺህ ሕንፃዎች ደግሞ ከከተማዋ ወጣ ብላ በምትገኝ አካባቢ በኤተን እሳት ወድመዋል።
አደጋው በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ወጪን ካስወጡ የሰደድ እሳቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ ቃጠሎው ውድ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ በመከሰቱ ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንሹራንስ ኪሳራ ይጠበቃል።
እስካሁን በተቀመጠው ግምት ሰደድ እሳቱ ከ250 እስከ 275 ቢሊዮን ዶላር ማውደሙን የግል ትንበያ ተቋሙ አኩዌዘር አስታውቋል።
ትዕግስት የምትኖርበት አካባቢ ከሰደድ እሳቱ ራቅ ያለ ቢሆንም የንግድ ቦታዋ አካባቢ ለሰደድ እሳቱ ቅርብ እንደነበር ገልጻለች።
“እሳቱ ወደዚያ እያመራ ነበር። ወደ አካባቢ ሲደርስ አስቁመውታል” ብላ የንግድ ቦታዋ በእሳት አደጋ ሠራተኞች ጥረት እንደተረፈ ገልጻለች።
“እሳቱ የተነሳው የሐበሻ ገና ቀን ነበር። ከቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ነው የጀመረው። ጓደኞቼም ነበሩ። በጣም የሃብታም ሰፈር ከሆነው ማሊቡ ነው የጀመረው። እዚህ ይደርሳል ብለን አላሰብንም” ስትል ከሳምንት በፊት ሰደድ እሳቱ ሲነሳ የነበረውን ሁኔታ ታስታውሳለች።
“ቀኑን ሙሉ፣ ሌሎቱን ሙሉ እሳቱ ቀጠለ። ከዚያም ተቃራኒ ወደ ሆነው ወደ ፓሳዲና ተሻገረ። በነጋታው ወደ ሆሊዉድ ሂል ከዚያ ደግሞ ወደ ስቱዲዮ ሂል ተሻገረ። በጣም ሊታመን የማይችል ነገር ነበር” ስትል ትገልጻለች።
በዚህ ሰደድ እሳት የንግድ ቦታቸው ላይ ጉዳት የገጠማቸው ውስን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም እሷ እስከምታውቀው ድረስ የሞቱ አለመኖራቸውን ትዕግስት ትናገራለች።
“በእሳት አደጋው ሕይወቱን ያጣ ወይም የተጎዳ ሐበሻ አላውቅም። ምናልባት የታመሙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አውቃለሁ። የተወሰኑት ቤታቸው ሲጎዳባቸው፣ ጥቂቶች ንግዳቸው ተጎድቷል” ብላለች።
በሎስ አንጀለስ ታሪክ አውዳሚ በሆነው በዚህ ሰደድ እሳት ከ137 ሺህ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል።
“ፊልም የማይ እንጂ የእውነት አልመስል ነው ያለኝ” ስትል ነው ኢትዮጵያዊት-አሜሪካዊቷ ትዕግስት የገለጸችው።
በካሊፎርኒያ ያሉ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያዎች በሎስ አንጀለስ ዙሪያ ያለው የእሳት ቃጠሎ እንዲነሳ ምክንያት የሆነው ኃይለኛ ንፋስ በዚህ ሳምንት እንደሚቀጥልም አስጠንቅቀዋል።
የእሳት አደጋ የመከላከያ ሠራተኞች በበኩላቸው በሦስት አካባቢዎች የተነሱ እሳቶችን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ያሳለፍነው ቅዳሜ እና እሑድ በአንፃራዊነት የተረጋጋ ንፋስ የነበረ ቢሆንም ሳንታ አና የተሰኘው ኃይለኛው ንፋስ ከእሑድ ምሽት እስከ ረቡዕ ድረስ እንደገና እንደሚነሳ እና በሰአት 60 ኪሎ ሜትር እንደሚጓዝ ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።
ከንፋሱ መነሳት በፊት በከተማው ዳርቻ እየተቃጠሉ ያሉትን የፓሊሳድስ እና ኢተን እሳቶች በመቆጣጠር ረገድ የተወሰነ ለውጥ ታይቷል።
“የእሳት አደጋ ተከላካዮች የሰዎችን ሕይወት ለማዳት ሲሞክሩ ነበር። ባልታሰበ ሰዓት ስለተነሳ ብዙዎች ዕቃ ይቅር እና ሰነዶች ይዞ ለመውጣት አልቻሉም” ትላለች ትዕግስት።
“በጣም አስደንጋጭ ነው። ባየኋቸው ብዙ ቦታዎች በርካቶች ያለ ምንም ነገር ነው የቀሩት” ስትልም ያለውን አስከፊ ሁኔታ ገልጻለች።
በሎስ አንጀለስ ዙሪያ ሦስት አካባቢዎች መቃጠላቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ ትዕግስት ከልጆቿ ጋር በመሆን በእሳት አደጋው ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ መስጠቷን ትናገራለች።
“የተጎዱ ኢትዮጵያውያን አላገኘሁም። እዚህ ላሉ አሜሪካውያን ነው ድጋፍ የሰጠነው” ብላለች።
ትዕግስት ከዚህ ቀደም በደብረ ብርሃን እና በሌሎችም አካባቢዎች እርዳታ በመስጠት ትታወቃለች። አሁንም በወሎ አካባቢ ረሃብ ለተጎዱ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት ድርጅት መሥርታለች።
“ሰው ስለሚረባረብ የምግብ እና መድኃኒት እጥረት የለም። እንዲያውም ውሃ በዝቶ ማስቀመጫ ቦታ ስላልነበረ መለስኩት። የሕጻናት ምግብ እና የንጽሕና መጠበቂያ ያስፈልግ ስለነበር እነሱን ሰጥቻለሁ” ትላለች ትዕግስት።
“ለመርዳት ተሰልፈን ነው የነበረው። ብዙ ሰው ነው ለመርዳት የወጣው። ለመረዳት ሳይሆን ለመርዳት ነው ሰው የወጣው። የደብረ ብርሃን ሁኔታን አስታውሼ የሁለቱ ተቃራኒ መሆን ስሜታዊ አደረገኝ” ስትልም ስሜቷን ገልጻለች።
ኃይለኛ ንፋስ እና የዝናብ አለመኖር ሰደድ እሳቱን እንዳባባሰው ተገልጿል። የአየር ንብረት ለውጥ ከሰደድ እሳቱ ጀርባ እንዳለም ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ትዕግስት “ልጆቼ ተወልደው ያደጉባት እና እኔም የምኖርባት አገር ስለሆነች የአቅሜን ማድረግ አለብኝ” ትላለች።
ልጆቿ በእርዳታው እንዲሳተፉ ያደረገችበትን ምክንያትም “ልጆቼ ከልጅነታቸው ጀምሮ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊ ነው ስረዳ የሚያውቁኝ። እነሱም ያግዙኛል። በተወለዱበት አሜሪካ ችግር ሲገጥም መርዳት እንዳለብን እንዲያውቁ ነው። ወገናዊነቴ እና ሰብአዊነቴ ለሁሉም ሰዎች እኩል መሆኑን እንዲያውቁ ነው” ስትል ገልጻለች።
ኢትዮጵያዊት-አሜሪካዊቷ ትዕግስት ፈረደ ቀድሞ የፋሽን ዲዛይነር የነበረች ሲሆን፣ አሁን በሎስ አንጀለስ የራሷ ንግድ አላት።
“ሁሉም ሰብአዊ ሰው ችግር ሲደርስ መረባረብ አለበት። ዛሬ ቢኖረኝ ነገ እንደማጣ አስባለሁ” የምትለው ትዕግስት፤ አብዛኞቹ በሰደድ እሳቱ የተጎዱ ሰዎች በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ “በአንድ ቀን ቤት አልባ ሆነዋል” ትላለች።
በእርስ በእርስ ጦርነት እንዲሁም በረሃብም የሚሞቱ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍም ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡም ታሳስባለች።
የካሊፎርኒያ የእሳት አደጋ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ቢያንስ በአምስት አካባቢዎች እሳቱ ተከስቷል። እነዚህም፦
ፓሊሳዴስ: የመጀመሪያው እሳት ማክሰኞ የተነሳበት ትልቁ እሳት ሲሆን፣ በግዛቲቱ ታሪክ በጣም አውዳሚው እሳት ሊሆን ይችላል። ከፍተኛውን የፓሲፊክ ፓሊሳዴስ ሰፈርን ጨምሮ ወደ ከስምንት ሺህ ሔክታር በላይ የሚጠጋ አካባቢን አውድሟል።
ኢተን፡ ይህኛው እሳት የሎስ አንጀለስን ሰሜናዊ ክፍል አጥቅቷል። እንደ አልታዴና ያሉ ከተሞችን በእሳቱ እየወደሙ ነው። ወደ 5665 ሔክታር የሚጠጋ አካባቢን የሚያቃጥለው እሳት በአካባቢው ሁለተኛው ትልቁ እሳት ነው።
ኸረስት፡ ከሳን ፈርናንዶ በስተሰሜን የሚገኘው አካባቢ ማክሰኞ ምሽት መቃጠል ጀመረ። ወደ 271 ሔክታር የተስፋፋ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ለመቆጣጠር ሥራ ጀምረዋል።
ሊዲያ፡ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ ከሎስ አንጀለስ በስተሰሜን በምተገኘው ተራራማው አክቶን አካባቢ እሳቱ ተከሰተ። ወደ 141 ሔክታር የሚጠጋ አካባቢን አዳርሷል። 60 በመቶው እሳት በቁጥጥር ስር መዋሉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ኬኔት፡ ይህ አዲስ እሳት ሐሙስ ዕለት በሎስ አንጀለስ እና በቬንቹራ አውራጃዎች ድንበር ላይ ተቀሰቀሰ። እስካሁን ወደ 404 ሔክታር አካባቢን አዳርሷል።
ቀደም ሲል የሰንሴት፣ ዉድሊ እና ኦሊቫስ እሳቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)