በሩስያ ና ዩክሬን የተከሰተው የበረዶው ሽንፍር 2 ሚሊዮን ሰዎችን ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ውጪ አደረገ Leave a comment

28 ህዳር 2023

ሃሪኬን በተሰኘው አውሎ ንፋስ እና ከባድ ጎርፍ ሳቢያ በደቡባዊ ሩስያ 1. 9 ሚሊዮን ህዝብ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ውጪ እንዳደረገ ሩስያ አስታውቃለች።።  ሞስኮ በህገ ወጥ መንገድ ጠቅልላቸዋለች ተብለው የሚጠቀሱት የዩክሬን ግዛቶችም ከአቅርቦት ውጭ ከሆኑት መካከል ናቸው ተብሏል። የሩስያ የኢነርጂ ሚኒስቴር ዳጋስታን፣ ክራሳንዶር እንዲሁም በዩክሬኖቹ ዶንቴስክ፣ ሉአንሳክ፣ ኬርሶን፣ ዛፖርስያና ክሪሚያ ግዛቶች የከፋውን ችግር እያስተናገዱ ነው ብሏል። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቢያንስ አራት ሰዎች ከበረዶ ውሽንፍር ጋር በተገናኘ መሞታቸው ዘግበዋል። የዩክሬን በበኩሏ 2 ሺህ 19 መንደሮችና አነስተኛ ከተሞች በበረዶ ውሽንፍር ሳቢያ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ጋር መቆራረጣቸውን ገልጻለች።

ይህ የበረዶ ውሽንፍር በሞልዶቫ፣ ጆርጂያና ቡልጋሪያም ተከስቷል። በሩስያ የጥቁር ባህር ወደብ በሆነችው ሶቺ የተቀሰቀሰው ከባድ ማዕበል ለባህሩ ቅርብ የሆኑ አካባቢዎችን ክፉኛ ጎድቷቸዋል። በዚህም ሳቢያ ባለ ሶስት ወለል ህንጻ ሲደረመስ የሚያሳይ ቪዲዮም ተለቋል።  በሞስኮ ከከባድ ውሽንፍር በኋላ ልዩ መስሪያዎች የከተማዋን ጎዳናዎች ሲያጸዱ ታይተዋል። ሩስያ በአውሮፓውያኑ 2014 በጠቀለለቻት የዩክሬን ግዛት በሆነችው የክሪሚያ ባህረ ገብ መሬት በሞስኮ የተቀመጡ ሹማምንት በባህር ዳርቻዎች አከባቢ ጎርፍ መከሰቱን ገልጸዋል። በበርካታ ከተሞች ላይ ዛፎችና ሌሎች ቁሶች ወድቀው ይታያሉ። በዚህ የተፈጥሮ ክስተት ሳቢያ ሴቫስቶፖል በተሰኘው የወደብ ከተማ የሚገኘው ታሪካዊ ሙዝየም ውስጥ የነበረው የአሳ ማቆያ ወድሞ ወደ 800 የሚጠጉ ከሌላ ስፍራ የተሰባሰቡ አሳዎች መሞታቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዘኃን የሙዝየሙን ኃላፊ ጠቅሰው ዘግበዋል። በክሪሚያ በርካታ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።

የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ አማካሪ ከውቅያኖስ በተነሳው ጎርፍ ምክንያት ሩስያ በጠቀለለችው ክሪሚያ የተገነቡ ምሽጎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ብለዋል። ሩስያ በዚህ ጉዳይ አስተያየት አልሰጠችም። በሌላ በኩል ዩክሬን በግዛቷ በበረዶ ውሽንፍርና በከባድ ንፍስ ምክንያት 16 አካባቢዎች እንደተጎዱ ገልጻለች። ክስተቱ በከፋበት ደቡብ ምዕራባዊ ግዛት ኦዴሳ መውጫ ያጡ ህጻናትን ጨምሮ 48 ሰዎች ከአደጋ መታደግ መቻሉን ጨምራ ገልጻለች። ወደ 840 የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች እስከ ሁለት ሜትር በሚዘልቅ በረዶ በመዋጣቸው ተጎትተው እንደወጡ የዩክሬን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ገልጿል። ቢያንስ 1 ሺህ 370 የጭነት ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉም ተዘግቧል። ቢያንስ 6 ሰዎች በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት በሚመጣው አይፖተርሚያ በተባለ በሽታ መጋለጣቸውም ተነግሯል። 14 ዋና ዋና መንገዶች ዝግ ሆነዋል።

የዩክሬን ደቡባዊ ግዛት የሆነችው ማይኮሊቪያም ክፉኛ ተጎድታለች። ከተሞች እና መንደሮችን ለማጽዳት ወደ 1 ሺህ 500 የሚጠጉ የነፍስ አድን ሰራተኞች በመላው ዩክሬን ተሰማርተዋል። የንፍስ አድን ሰራተኞቹ በፖሊስ፣ በድንበርና በብሄራዊ ዘብ አባላት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በኪየቭ 90 ሜትር ከፍታ ላይ የሚውለበለበው የሀገሪቱ ትልቁ ሰንደቅ ዓላማ በከባድ ንፍስ ምክንያት ከጥቅም ውጪ ሆኖ መስቀያው ባዶ ሆኖ ታይቷል። በዩክሬን በርካታ መንገደኞች ሲጓዙበት የነበረ ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ በነፍስ አደን ሰራተኞች ታግዘዋል

የከተማው ሹማምንት ሰንደቅ ዓላማው በድጋሚ እንደሚሰቀል ገልጸዋል። ይህ ከባድ የአየር ሁኔታ ሩስያ የኤሌክትሪክ ማከፋያያዎን እና ሌሎች ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ በማድረግ ለተጨማሪ ከባድ የሮኬትና የድሮን ጥቃት እየተዘጋጀች ባለችብት ወቅት የተከሰተ ነው ተብሏል። ባለፈው ዓመት ሩስያ በተመሳሳይ ሁኔታ በፈጸመችው ጥቃት ሚሊዮኖች ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቆራርጠዋል። ባለፈው ቅዳሜ ሩስያ 2022 ወረራ በኋላ ከባድ የተባለውን የድሮን ጥቃት ኪዬቭ ላይ ማድረሷን ባለስልጣናት ገልጸዋል። ባለስልጣናቱ፣ ከተላኩት 75 ድሮኖች ውስጥ 74 ተመትተው መጣላቸውን ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop