25 ህዳር 2023
እስር ቤት ነው ብሎ ማን ያምናል? ያውም በላቲን አሜሪካ እና በቬንዙዌላ የተስፋፋው እና እጅግ አስፈሪው ትሬን ዲ አራጓ የወንበዴ ቡድን እስር ቤት። በቶኮሮን ከተማ የሚገኘው ይህ እስር ቤት የተገነባው እንደ አውሮፓውያኑ 1982 ነው። ከተማው ከቬንዙዌላ መዲና ካራካስ 140 ኪሎ ሜትር ይርቃል።2.25 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 750 እስረኞችን የመያዝ አቅም አለው። ይሁን እንጂ ትሬን ዲ አራጓ የሚባለው የወንበዴ ቡድን በተስፋፋበት ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከ7 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች መኖሪያ ሆኖ ነበር። አሁን ላይ በቬንዙዌላ እና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ አደገኛ ወንበዴዎች ተወሮ የነበረው ይህ እስር ቤት በኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት ትዕዛዝ እንዳልነበር ሆኗል። የማዱሮ መንግሥት በወንበዴዎቹ ቁጥጥር ሥር የነበረውን እስር ቤት ከ11 ሺህ በላይ ወታደሮችን በማሰማራት መልሶ በእጁ ያስገባው በቅርቡ ነበር። ከዚህ በኋላ ለታሰሩ ዘመዶቻቸው ምግብ እና ልብስ ለማድረስ በአካባቢው የሚመላለሱ በርካታ ሴቶች አይታዩም። ወደ እስር ቤቱ መዋኛ ሥፍራ ለመሄድ እናቶቻቸውን የሚያጣድፉ ሕጻናትንም እንዲሁ። በአራጓ ግዛት ቶኮሮን ከተማ የሚገኙ ቢራ መሸጫዎች እና ሌሎች የንግድ ተቋማትም ተዘግተዋል። ጎብኚዎች ስልካቸውን ለማስቀመጥ አንድ ዶላር የሚከፍሉባቸው ከእስር ቤቱ ፊት ለፊት ያሉ ሱቆችም አገልግሎት አይሰጡም። በእስር ቤቱ ውስጥ ያለውን ሕንጻ የማፍረሱ ሂደት ግን ቀጥሏል። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የምርመራ ጋዜጠኛዋ እና የቢቢሲ ልዩ ዘጋቢ ሮና ሪስኪዩዝ ይህንን ቅንጡ እስር ቤት የመጎብኘት ዕድል ነበራት። ጋዜጠኛ ሪስኪዩዝ እስር ቤቱን የጎበኘችው በአህጉሪቱ ስለተስፋፋው እና ስለተደራጀው የወንጀል ቡድን እየጻፈች የነበረውን መጽሐፍ ለማጠናቀቅ በአካባቢው እጅግ አደገኛ የሆኑት የትሬን ዲ አራጓ ወንበዴዎች ምሽግ ሆኖ የሚያገለግለው እስር ቤት ምን እንደሚመስል ለማየት ነበር። “መንግሥት የቶኮሮን እስር ቤት መልሶ መቆጣጠሩን ሲያስታውቅ ማመን አልቻልኩም ነበር” ብላለች ሪስኪዩዝ። ሪስኪዩዝ የወንበዴ ቡድኑ መሪ የሆነው እና አሁን ላይ በላቲን አሜሪካ በጥብቅ የሚፈለገውን ኤል ኒኖ ጉሬሮን ግዛት በጎበኘችበት ወቅት ያየችው ሁሉ እንዳስደመማት ተናግራለች።
ቶኮሮን እስር ቤት
ቶኮሮን እንደማንኛውም እስር ቤት አልነበረም። ቅንጡ የመዝናኛ መንደር እንጂ። መዋኛ ገንዳዎች፣ መካነ እንስሳት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ ምግብ ቤቶች፣ የቤዝቦል ስታዲየም፣ የእፅ መሸጫ ሱቆች፣ ሞተርሳይክሎች እና የጦር መሣሪያዎች አለ። የቶኮሮን እንዲሁም ትሬን ዲ አራጓ የሚባለው የወንበዴ ቡድን መሪ ይህንን እስር ቤት ወደ ቶኮሮን ከተማ ሳይቀይር እረፍት እንደማይኖረው ይናገር እንደነበር እስረኛው አስጎብኚዋ ጁሊዮ ለሪስኪዩዝ ነግሯታል። ጁሊዮ ይህ ሲነግራት ጎብኚዎች አረፍ የሚሉበት ከእንጨት የተሰሩ ውብ ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች እንዲሁም ቴሌቪዥን በሚገኝበት አካባቢ ሆነው ነበር። ቶኮሮን ይህ ቀረው የሚባል ነገር የለውም። መካከለኛ ገቢ ያላቸውና ቱጃሮች የሚኖሩበት ትንሽ ከተማ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። እስር ቤቱ በቬንዙዌላ የተለመደው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሲቋረጥ ኃይል የሚያገኝበት የራሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ነበረው። የቴክኒክ ሥራውን የሚሠራም ቡድን ነበረው። እነዚህ ባለሙያዎች የራሳቸው የደንብ ልብስ የነበራቸው ናቸው። ጂንስ ሱሪ እና ቀለም ያለው ቲ ሸርት ነበር የሚለብሱት። በእስር ቤቱ ያለውን የኤሌክትሪክ ሥርዓት የመጠገን እና አቅርቦቱን የመከታተል ኃላፊነት ነበረባቸው። በአቅራቢያ ያሉ ከተሞች ነዋሪዎችም የኃይል መቋረጥ ሲያጋጥማቸው እንዲሰሩላቸው ይወስዷቸው ነበር። የቶሮኮን እስር ቤት 750 እስረኞችን የመያዝ አቅም የነበረው ሲሆን፣ከ7 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ ሆኖ ነበር።
ቁማርተኞቹ
የቡድኑ መሪ ጉሬሮ፣ ቶኮሮን እስር ቤትን ለመለወጥ ለነበረው ጥልቅ ፍላጎት በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ሕንጻዎች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሁም በእስር ቤቱ ያለው ሥርዓት እና ፀጥታ ይመሰክራሉ። የእስር ቤቱ ሁሉም አካባቢዎች ኤአር-15 ወይም ኤኬ -103 መሣሪያ፣ ጠመንጃ እና ሽጉጦችን በታጠቁ ሰዎች ይጠበቃል። እነዚህ ጠባቂዎች ራሳቸው እስረኞች ናቸው። ጠባቂዎቹን ‘ጋሪቴሮስ’ እያሉ ነበር በእስር ቤቱ ቋንቋ የሚጠሯቸው። ቁማርተኞቹ እንደ ማለት ነው። በርካታ እፅዋት በሚገኙበት ትልቅ ተራራ ሥር የሚገኘው መካነ እንስሳትም ሁለት ጠባቂዎች እና ተንከባካቢዎች ነበሩት። ጉሬሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እባብ ከጠፋ በኋላ ያ ክስተት እንዳይደገም ይፈልግ ስለነበር ነው ተንከባካቢዎች ያሰማራው። አዕዋፍት፣ ጦጣዎች፣ ሰጎኖች፣ ዶሮዎች፣ ድመቶች፣ ፈረሶች፣ አሳማዎች፣ የቀንድ ከብቶች፣ ተለይተው በየራሳቸው ዝርያ ምቹ ቦታ ነበር የተቀመጡት። ይህ ብቻም አይደለም። የእያንዳንዳቸውን ባህርይ የሚገልጽ ትንሽ ካርድም ነበራቸው። በዚያው ቦታ እስረኞች በ‘ኩክፋይት’ ጨዋታ የሚወራረዱበት በኮንክሪት የተሠራ አስገራሚ ሜዳ አለ። ኩክፋይት በታጠረ ቦታ ሁለት አውራ ዶሮዎች እንዲጋጠሙ በማድረግ የሚካሄድ የውርርድ ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ በአንዳንድ አገራት ክልክል ነው። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በቡድኑ መሪ ዲዛይን የተደረገ በሰው ሰራሽ ሳር የተሰራ የቤዝቦል ስታዲየም ይታያል። በመካነ እንስሳቱ ውስጥ ሁሉም እንስሳት እንደ ዝርያቸው ተለይቶ የተዘጋጀ ምቹ መኖሪያ አላቸው።
የቶኮሮን የመጨረሻው መጀመሪያ
እስር ቤቱ በእስረኞቹ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለታል። ሪስኪዩዝ በጉብኝቷ ወቅት ጠመንጃ እና ሽጉጥ የታጠቁ ሁለት ሰዎች እንቅስቃሴዋን በሦስት ሜትር ርቀት በቅርበት ይከታተሉ እንደነበር አስተውላለች። በከባድ ሞተር ሳይክሎች ከሚያልፉት በተጨማሪ በእያንዳንዱ 100 ሜትር በታጠቁ ሰዎች አጠገብ ነበር የምታልፈው። ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ስትሄድ በርካታ መሠረተ ልማቶችን እና የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትንም ተመልክታለች። በፈረስ ግልቢያ ውድድሮች የሚካሄዱ ውርርዶችን አይታለች። በጣም ያስገረማት ግን እፅ ለመሸጥ ብቻ ተለይተው የተዘጋጁት ሱቆች ነበሩ። ከማሪዋና እስከ ኮኬይን ከዚያም እስከ ሰው ሰራሽ እፆች ይሸጥበታል። በእያንዳንዱ እርምጃዋ የምታየው ሁሉ ከ2016 ጀምሮ ሾልከው ወጡ በተባሉ ፎቶች እና ቪዲዮዎች ላይ ያየቻቸውን ቦታዎች ያስታውሷታል። ከምታስታውሰው አንደኛው ቶኪዮ የምሽት ክለብ ነው። በዚህ ክለብ በጣም ዝነኛ የሆኑ የቶኮሮን ፓርቲዎች ይዘጋጁበት ነበር። ይሁን እንጂ በ2022 አጋማሽ የወንበዴ ቡድኑ መሪዎች የምሽት ክለቡን ለሕዝብ ክፍት እንዳያደርጉ ከመንግሥት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው እንደነበር የቀድሞው የቡድኑ አባል ለሪስኪዩዝ ነግሯታል። ከማንና ከየት እንደሆነ ግን አልገለጸላትም። ሆኖም ጉዳዩ የሕዝብ ትኩረት ስቧል የሚል ስለነበር በእስር ቤቱ ውስጥ የሚካሄዱ ፓርቲዎች ቀጥለው ነበር። ይህ ትዕዛዝ ምን አልባት የቶኮሮን መጨረሻ መጀመሪያ መሆኑን አመላካች ሊሆን ይችላል። በዚሁ ወቅት የቡድኑ መሪ ጉሬሮም አጋሮቹ በተለያዩ እስር ቤቶች በፌስቡክ የገበያ ገጽ የሚካሄዱ የተሸከርካሪ ሽያጭ ማጭበርበሮችን እንዲያግዱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። በርካታ የማኅበረሰብ አባላት የአጭበርባሪዎቹ ሰለባ ሆነው የነበረ ሲሆን ወንጀሉ በርካታ ባለሥልጣናትንም የነካ ነበር። ቶኮሮን ውድ የሆኑ ምርቶችን የሚያስተዋውቁ ምግብ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ነበሩት።
“የሚሊየነሮቹ ብቻ እስር ቤት”
ጋዜጠኛ ሪስኪዩዝ ለእስረኛው አስጎብኝዋ ጁሊዮ የወሰደችለትን ዳቦ አብረው እየቀማመሱ እያወሩ ነው። ጁሊዮ ዳቦ ወይም ኃይል የሚሰጡ መጠጦችን ለማግኘት ብዙም ዕድል አልነበረውም። ጎብኚዎችን የሚቀበለውም አልፎ አልፎ ነው። ሆኖም ከእርሱ በባሰ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እስረኞች እንዳሉ ለሪስኪዩዝ አጫውቷታል። ከእነዚህ እስረኞች መካከል አንዳንዶቹ “ በግ” እየተባሉ ነበር የሚጠሩት። በእስር ቤቱ ውስጥ ባለው የማኅበራዊ ደረጃ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ነበሩ። እነዚህ እስረኞች ቤተሰብ የሌላቸው አሊያም በመሪው የተደነገገውን የእስር ቤቱን ሕግ የጣሱ ናቸው። በተወሰነ ቦታ ተገድበው ነበር የሚቀመጡት። በዚህም ምክንያት የመዋኛ ገንዳውን፣ ምግብ ቤቶቹን ወይም የምሽት ክለቦቹን የመጠቀም ዕድልም አልነበራቸውም። እነርሱን ለመለየትም ረጅም እጅጌ ያለው ሸሚዝ አሊያም መስመር ያለው ልብስ እንዲለብሱ እንዲሁም ከረቫት እንዲያደርጉ ይደረጋሉ። አብዛኞቹ እነዚህ እስረኞች የተራቡ እንደሆኑ ያስታውቃሉ። “እየተራመዱ ሲታዩ ‘ሙታን’ ነበር የሚመስሉት” ትላለች ሪስኪዩዝ። ይህ እስር ቤት የሚሊየነሮች እንደሆነ እና ሁሉም ነገር ገንዘብ መሆኑን ጁሊዮ ነግሯታል። ሁሉም እስረኛ በየሳምንቱ ለመሪው 15 ዶላር መክፈል አለበት። ይህ ክፍያ እስረኞች ምንም ዓይነት ጥቃት ሳይደርስባቸው በእስር ቤቱ ለመቆየት የሚከፍሉት ነው። ለሌሎች አገልግሎቶችም ክፍያ አለ።የክፍያ መጠኑ ግን እንደ አገልግሎቱ ይለያያል። ሁለት በሁለት የሆነች የመኝታ ቦታ ለማግኘት 20 ዶላር ኪራይ ይከፈላል። ቅዳሜ እና እሁድ ከጓደኛ ጋር አብሮ ለማሳለፍ ደግሞ 30 ዶላር መክፈል ግድ ነው። በእስር ቤቱ ውስጥ የሚታዩት የባሌንሺያጋ፣ ጉሲ፣ ናይክ የንግድ ማስታወቂያዎችም በእስር ቤቱ ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ እንዳለም ፍንጭ ይሰጣሉ። ሪስኪዩዝ በእስር ቤቱ ቆይታዋ ያላየችው የመሪዎቹን መኖሪያ ቤት ብቻ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ የሚኖሩት ከትሬን ዲ አራጓ መሪዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንዲገቡ በተፈቀደበት አካባቢ ስለሆነ ነው። እዚያ ለመሪዎቹ ብቻ የተገነቡ የመዋኛ ገንዳዎች እና ምግብ የሚሰራበት ቦታ ነበር። አሁን ይህ ዓለም ተረት ሆኗል። መንግሥት 11 ሺህ የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራት የወንበዴ ቡድኑን ይዞታ በታትኖታል። እስር ቤቱን ለመቆጣጠር የተሰማሩትን ወታደሮች የመሩት የቬንዙዌላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ግንኙነት ሚኒስትር አድሚራል ሬሚጊዮ ሴባሎስ፣ “ለዚህ ዓይነት አገልግሎት የማይመጥኑ በጣም ሰፊ ቦታዎችን አግኝተናል” ብለዋል።
አሁን ላይ እንደ ቶኮሮን በርካታ እስረኞች እንዲሁም ጠፍቶ እየታደነ እንዳለው የቡድኑ መሪ ኤል ኒኖ ጉሬሮ ሁሉ የጁሊዮ ዕጣ ፈንታም አልታወቀም። የእስር ቤቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል ለወንጀል ቡድኑ ከባድ ጉዳት ነው። ነገር ግን ይህ የወንጀል ተግባራቱ ከቬንዙዌላ እስር ቤት ወደ ኮሎምቢያ፣ ብራዚል፣ ፔሩ፣ ኢኳዶር፣ ቦሊቪያ፣ ቺሊ ምን አልባትም ወደ አሜሪካ የተስፋፋው የዚህ አደገኛ ወንበዴ ቡድን መጨረሻ ይሁን አይሁን ግልጽ አይደለም።