በአማራ ክልል አንድ የረድዔት ሠራተኛ ባገቱዋቸው ታጣቂዎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ…… Leave a comment

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ ውስጥ ለገንዘብ የታገቱ ያሬድ መለሰ የተባሉ የረድዔት ሠራተኛ መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

በማኅበራዊ ልማት እና በከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ላተኮረ አገር በቀል የሆነ የረድዔት ድርጅት ሠራተኛ የነበሩት ያሬድ መለሰ ባልታወቀ ወንጀለኛ ታጣቂ ቡድን መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ነሐሴ 8/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ያሬድ፣ አክሽን ፎር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ፕሮቴክሽን በተባለው ድርጅት የሥነ ምግብ (ኒውትሪሽን) ባለሙያ እንደነበሩ ያስታወቀው ተመድ የረድዔት ሠራተኛውን ግድያ አውግዟል።

“በሰብዓዊ ተግባር ተሰማርቶ እያለ በወንጀለኞች ለገንዘብ ከታገተ በኋላ መገደሉን በጥብቅ እናወግዛለን። ያሬድ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ያሉ ነዋሪዎችን ለመርዳትን ዝግጁ እና ቁርጠኛ የሰብዓዊ ሠራተኛ ነበር። ማንኛውም ጥቃት ዛቻ፣ ዘረፋ ወይም እገታ የሥነ ምግባር ሕጋችንን የጣሰ ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ ገልጸዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪው በረድዔት ሠራተኛው ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ገልጸው ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

በአሁኑ ወቅት የተፈጸመውን ግድያ ጨምሮ በኢትዮጵያ ከጥር ወር ጀምሮ ስምንት የረድዔት ሰራተኞች የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ስድስቱ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ኃይል እየተዋጉ ባለበት የአማራ ክልል ነው።

ከተገደሉት በተጨማሪ ቢያንስ 14 የረድዔት ሠራተኞች ለገንዘብ ሲባል የታገቱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ የተከሰቱት በማዕከላዊ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች መሆኑን ተመድ በዚህ መግለጫው ጠቅሷል።

“የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ኢላማ ሲደረጉ በተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ የማድረስ አቅማችንን በእጅጉ ይጎዳል። የአሁኑን ክስተት አፋጣኝ ምርመራን ጨምሮ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ግድያዎችን የፈጸሙ ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ በተመለከተ ከመንግሥት ተቋማት ጋር ተነጋግረናል” ሲሉ አስተባባሪው አክለዋል።

የእርዳታ ሠራተኞች ደኅንነታቸው ተረጋግጦ ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የስነ ምግባር ህጉን እንዲያከብሩ የጠየቁት አስተባባሪው “የረድዔት ሰራተኞች ኢላማ አይደሉም” ብለዋል።

በተመሳሳይ ግጭት እየተካሄደባቸው ባሉ የአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች አካባቢዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ደህንንት እንዲጠበቅ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጠይቋል።

ግጭት ባለባቸው በነዚህ አካባቢዎች በሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ ያነጣጠሩ እንደ ግድያ፣ አፈና ያሉ ጥቃቶች መበራከቱን ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፖርቶች እንደደረሱት ነሐሴ 8/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ከነዚህም በተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን መንጠቅ፣ በመጋዘን የሚገኙ የዕርዳታ አቅርቦቶች ዝርፊያዎች እየደረሱ እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ እነዚህ ክስተቶችየእርዳታ አገልግሎቶችን እና ሰብአዊ እንቅስቃሴዎችን እያደናቀፉ እንደሚገኙም ገልጿል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ሲስተዋሉ የነበሩ እነዚህ ጥቃቶች በተለይም በአማራ ክልል ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልተው እየታዩ መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል።

የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ የእርዳታ ሰራተኞች ስራቸውን ለአደጋ ተጋላጭና አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች በሚያከናውኑበት ወቅት ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እና በማንኛውም ሁኔታ የጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ በግልጽ እንደሚደነግግ በጠቀሰበት በዚህ መግለጫው እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን አውግዟል።

ምክር ቤቱ እነዚህን ጥቃቶችን የሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቦ “በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአካባቢው የመንግሥት አደረጃጀቶች፣ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች እና ማህበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች፤ የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ደህንነት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ” ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want