በእስራኤል ጥቃት ከተገደለች ፍልስጤማዊት እናት ማህጸን ልጇን ማትረፍ ተቻለ!!!!! Leave a comment

ፍልስጤማዊቷ ሳብሪን ለወራት ያህል የተሸከመቻትን ህጻን አይኗን ሳታይ እና ሳታቅፍ ተገደለች።

የሰባት ወር ተኩል ነፍሰ ጡር ነበረች።

በጋዛ በሚፈጸመው የማያባራ ጥቃት በቤተሰቡ ከፍተኛ ሰቀቀን እና ስጋት ውስጥ ቢሆኑም ሳብሪን ልጇን በሰላም እንደምትገላገል ተስፋ አድርጋ ነበር።

ከቀናት በፊት እኩለ ሌሊት ገደማ ከፍተኛ ፍንዳታ እና ጩከት አካባቢያቸውን አናወጠው።

ሳብሪን ከባለቤቷ እና ከሦስት ዓመት ልጃቸው ማላክ የሚኖሩበት እና በራፋህ በሚገኘው የአል-ሳካኒ ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ተኝተው ነበር። ቤቱ በእስራኤል ቦምብ ተመታ።

ሳብሪን ከፍተኛ ጉዳት አስተናገደች። ማላክ እና ባለቤቷ ተገደሉ። ነፍስ አድን ሠራተኞች ሲደርሱ በሳብሪን ማህጸን ያለችው ልጅ በሕይወት ነበረች።

በፍጥነት ሳብሪንን ወደ ሆስፒታል በመውሰድ ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ልጇ እንድትወለድ አደረጉ።

ሳብሪን ግን በህይወት ልትተርፍ አልቻለችም። የልጇን ሕይወት ለማቆየት ግን ሐኪሞች ያደረጉት ሙከራ ተሳካላቸው።

“ከባድ የመተንፈስ ችግር ይዛ ነው የተወለደችው” ሲሉ በራፋህ የሚገኘው የኤሚራቲ ሆስፒታል የኒዮ-ናታል ድንገኛ ክፍል ኃላፊው ዶ/ር ሞሐመድ ሳላማ ገልጸዋል።

ስትወለድ 1.4 ኪሎ ብቻ የምትመዝነው ህጻንም ፈተናዎቿን ማለፍ ጀመረች።

ሐኪሙም “የሰማዕቷ ሳብሪን አል-ሳካኒ ልጅ” የሚል ጽሑፍ ፕላስተር ላይ አስፍረው ህጻኗ ላይ በመለጠፍ ያለጊዜዋ የተወለደችውን ህጻን በጨቅላ ማሞቂያ ክፍል (ኢንኩቤተር) ውስጥ አስገቧት።

“ጤንነቷ እየተሻሻለ ነው” ብለዋል ዶ/ር ሳላማ።

“አሁንም ግን ስጋቱ ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈም። መጀመሪያ ላይ የነበረው የመተንፈስ ችግሯ ያለጊዜ በመወለድ የመጣ ነው። ይህቺ ህጻን በዚህ ሰዓት እናቷ ማህጸን ውስጥ መሆን ሲገባት ይህንን መብቷን አጥታለች።”

ህጻኗ ለአንድ ወር ያህል በሆስፒታል እንደምትቆይ ሐኪሙ ይገምታሉ።

“ከዛ በኋላ ስለ ስለመውጣቷ እንወስናለን… ይህ ነው ትልቁ አሳዛኝ ነገር። ይህች ልጅ በህይወት ብትተርፍም ወላጅ አልባ ሆና ነው የተወለደች” ብለዋል ዶክተር ሳላማ።

ለህጻኗ ስም የሚያወጡላት ወላጆች የሉም። የሞተችው እህቷ ማላክ ሩህ እንድትባል ፈልጋ ነበር። በአረብኛ ሩህ ማለት ነፍስ ወይም መንፈስ ማለት ነው። ለእናቷ መታሰቢያ ትሆን ዘንድ ግን ሳብሪን ተብላለች።

በሕይወት የተረፉት የቤተሰቡ አባላት በሆስፒታሉ ተሰባስበዋል። ህጻኗ ሳብሪን አዲስ ቤተሰባዊ ሕይወት ለመፍጠር በሐዘናቸው እና በንዴታቸው መካከል ሆነው ተገኝተዋል።

የህጻኗ አያት ሚርቫት አል-ሳካኒ “ከምንም ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው” ሰዎች ላይ “ግፍ እና ስም ማጥፋት” ደርሷል ብለዋል።

“ልጄ ነፍሰጡር ነበረች። በማህጸኗ ፅንስ ተሸክማለች። ልጇም ከእሷ ጋር ነበረች። ልጄም ከእነርሱ ጋር ነበር።” ይላሉ

“ልጄ የአካል ክፍሎቹ በመቆራረጡ እስካሁን አላገኙትም። ሊለዩትም አልቻሉም. . . ለምንድነው ዒላማ ያደረጓቸው? ለምን እና እንዴት እንደሆነ አናውቅም። ዒላማ የሚያደርጉት ሴቶችን እና ህጻናትን ብቻ ነው” ብለዋል።

የህጻኗ አጎት ራሚ አል-ሼክ በበኩሉ ከአባቷ ጋር በፀጉር አስተካካይነት አብረው ይሠሩ እንደነበር ተናግሯል።

“ጥፋታቸው ምንድን ነው? አንድ ቤተሰብ ከመዝገብ ላይ ተፍቋል። ብቸኛዋ የተረፈችው ህጻን ልጅ ነች?” ሲል ይጠይቃል።

“እነዚህ ተራ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው።” ይላል።

የሳብሪን አያት አሃላም አል-ኩርዲ ህጻኗን እንደምታሳድግ ቃል ገብታለች። ” ፍቅሬ እና ነፍሴ ናት። የአባቷ መታሰቢያ ናት። እኔ እንከባክባታለሁ” ብለዋል።

መስከረም 26 ጦርነቱ በጋዛ ከተጀመረ ወዲህ 34 ሺህ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከልም አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስራኤል ጥቃት የጀመረችው ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ቤተ እስራኤላውያን እና የውጭ ዜጎች ከተገደሉ በኋላ 253 የሚሆኑት ታግተው ወደ ጋዛ ከተወሰዱ በኋላ ነው።

የእስራኤል ጦር በሠላማዊ ሰዎች ላይ አለማነጣጠሩን ገልጾ ሐማስን ህዝቡን እንደ ጋሻ ይጠቀማል ሲል ይከሳል።

ሳብሪን በተገደለችበት ምሽት እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት 15 የአል-አል ቤተሰብ አባልት ተገድለዋል።

አብዲ አል-አል እንዳለው ከሆነ ሁሉም ልጆቹ እና ባለቤቱ በመገደላቸው ማንነቱ እንደተፋቀ ተናግሯል።

“ከነሱ መካከል አንድ ደረሰ ሰው አሳዩኝ። ሁሉም ህጻናትና ሴቶች ናቸው” ብሏል።

ከጥቃቱ በኋላ ለቢቢሲ የተላከው የእስራኤል ወታደራዊ መግለጫ “ጦሩ በጋዛ ውስጥ የአሸባሪ ድርጅቶችን በርካታ ወታደራዊ ዒላማዎችን፣ የመተኮሻ ቦታዎችን እና የታጠቁ አሸባሪዎችን ኢላማ አድርጓል” ብሏል።

በጦርነቱ እንደተጀመረ ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲወጡ በእስራኤል ጦር የተገደዱ 1.4 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ራፋህን አጨናንቀዋል።

የእስራኤል ጦር ከሐማስ ጋር የሚደረገውን ውጊያ ለመቀጠል በቅርቡ ወደ ራፋህ ይገባል የሚለው ግምት እየጨመረ ይገኛል።

እስራኤል በራፋህ ላይ ሙሉ ወረራ ከማድረግ ይልቅ የተወሰኑ ዒላማዎች ላይ በማነጣጠር እንድታጠቃ አሜሪካ ጠይቃለች። ካልሆነ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

 በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ ፡-(@tikvahethiopia)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop