በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በድርቅ እና በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት 107 ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች መጎዳታቸውን እና በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንሚገኙ ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገለፁ።
የዞኑ ጤና መምሪያ ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ በአራት ወረዳዎች በርካታ ነዋሪዎችን ለችግር ያጋለጠ “ከፍተኛ የምግብ እጥረት” መከሰቱን አመለክቷል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ድርቅ የተከሰተ ሲሆን፤ ባለፈው የክረምት ወቅት ደግሞ ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የመሬት እጥበት፣ ጎርፍ፣ በረዶ እና የመሬት መንሸራተት በሰብሎች ላይ ጉዳት ማደረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተለይም ደጋማ በሆኑ እና ከፍተኛ ምርት በሚጠበቅባቸው ወረዳዎች ከፍተኛ ዝናብ ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል ሰብል ማውደሙን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በአካባቢው የዳሰሳ ጥናት ያካሄደው ወልዲያ ዩኒቨርስቲ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና ባቄላ ያሉ ዋና ዋና ሰብሎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቶ፤ አርሶ አደሮችን በቂ የምግብ አቅርቦት አሳጥቷል ብሏል።
አንድ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የደረሰውን ጉዳት በአካባቢው አጠራር “የውሃ እሳት” (በአገውኛ “አሆሌ”) ሲሉ ገልፀውታል።
“ውሃው [ዝናብ] ምርቱን ይውጥና ደቃቃ [ይሆናል]፤ የሚዘራው ማሽላ እና ገብስ ምርት የማይሰጥ ሆኖ ይቀራል። ሁለተኛ በከባድ በረዶ እና ጎርፍ ደግሞ በጣም በርካታ መሬት ተገለባብጧል። አርሶ አደሩ ያረሰው መሬት በሙሉ በጎርፍ ተወስዷል፤ በበረዶ ተመቷል” ብለዋል።
ሌላ ነዋሪም በዞኑ የደረሰውን የሰብል ጉዳት “የምርት መጥፋት” በሚል የገለፁት ሲሆን፤ ሰብላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች መፈናቀላቸውንም ተናግረዋል።
“ዝናቡ እና በረዶው በመብዛቱ፤ መሬቱ ታጥቦ በመሄዱ፤ የቀረውም እህል ውሃ በመብዛቱ ምርት ሊሰጥ ባለመቻሉ” በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ወደ አጎራባቸው አካባቢዎች ሥራ ፍለጋ መፍለሳቸውን ገልፀዋል።
ከፍተኛ የሰብል ውድመት እና የምግብ እጥረት በደረሰበት ደሃና ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አላይ ስመኝ አገሩን “ማዕበል መታው” ሲሉ የገጠማቸውን ችግር ተናግረዋል።
ምግብ ለማግኘት ስምንት ቤተሰባቸውን ይዘው አጎራባች በሆነው እና በተመሳሳይ የምግብ እጥረት ወደ ተከሰተበት ቡግና ወረዳ ቢሰደዱም እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አምስት ልጆቻቸው እንደታመሙ የተናገሩት ወ/ሮ አላይ የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ልጃቸው ጤና ጣቢያ ህክምና ላይ ስትሆን “ተዳክማለች” ሲሉ ያለችበትን ሁኔታ ገልፀዋል።
“እንኳን ሌላ የምትመጠምተውም [ጡት] ነገር የለም። ጡቴም ደረቀ። እከኩም ሲይዛት አዳከማት። . . .[ሐኪሞቹ] ለበሽታ የዳረጋቸው የምግብ እጥረት ነው ይላሉ” ብለዋል።
የዳሃና ወረዳ ቀበሌ 18 ነዋሪ፣ ባቄላ እና ገብስ ያመርቱ እንደነበር የተናገሩት አቶ አወቀ ካሳ “የተዘራው አዝርዕትም ምንም ዋጋ የለው፤ ከጥቅም ውጪ [ነው ሆነው]። ባዶ ክረምት ሆኖ ነው የቀረው” ሲሉ ሰብላቸው እንደወደመ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ አወቀ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ አላማጣ ሥራ ፍለጋ ቢሄዱም እንዳላተሳካቸው እና የአራት ዓመት ልጃቸው ወባ፣ የአንድ ዓመት ከአምስት ወር ልጃቸው ደግሞ በምግብ እጥረት ታመውባቸዋል።
የአንድ ዓመት ከአምስት ወር ልጃቸው ለህክምና ጥር 12/2017 ዓ.ም. በደሃና ወረዳ በሚገኘው አዚላ ጤና ጣቢያ እንደወሰዷት የተናገሩት አቶ አወቀ፤ “እኛ ምንም ነገር የለንም። ንፁህ ደሃ ነን” ሲሉ ቤተሰባቸውን መመገብ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
በደሃና ወረዳ በተደረገ ልየታ 11 ሺህ 200 የሚሆኑ ህፃናት እና እናቶች “በከፍተኛ እና መካከለኛ ምግብ እጥረት” እንደተጎዱ የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላክ ፍሰሐ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዋግ ኽምራ ዞን የሚታወቅ የምግብ እጥረት ያለበት እና በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም የሚደገፍ መሆኑን የጠቆሙት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ፤ ባለፉት የክረምት ወራት በደረሱ የመሬት እጥበት እና መንሸራትቶች ምርት አለመመረቱን ገልፀዋል።
“የተወሰነውን መንግሥት እያገዘ፤ አጋር ድርጅቶች እያገዙ፤ ማኅበረሰቡም ቢያንስ በራሱ ለአራት ወር፤ ለስድስት ወር የተወሰነ ምርት ያገኝ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ይህ አልሆነም” ሲሉ ሕዝቡ በተደራራቢ ችግር “አስቸጋሪ” ሁኔታ ውስጥ መገባቱን አመልክተዋል።
አንድ ነዋሪ በዞኑ የደረሰው ጉዳት በተለይም በህፃናት እና እናቶች ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ ሲናገሩ “ልጆች ቆዳቸው ተሸብሽቦ፣ እናቶችም ጡት ማጥባት አቅቷቸው” ብለዋል።
ሌላ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪም “ለማየት የሚሰቀጥጥ” ሲሉ የገለጹት ጉዳት ህጻናት ላይ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች ከጥቅምት 2017 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ “በጣም የተወሳሰበ [ኬዝ]፣ በጣም የከሱ፣ የተጎዱ ህፃናትን” ማግኘት መጀመራቸውን አቶ አሰፋ ገልፀዋል።
የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን ጨምሮ ጋዝጊብላ፣ ደሃና፣ አበርገሌ እና ፃግብጅ ወረዳዎች ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎች መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
የወልዲያ ዩኒቨርስቲ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው በአራት ወረዳዎች ከ106 ሺህ 600 ነዋሪዎች (35 በመቶ የዞኑ ሕዝብ) በድርቅ እና በምግብ እጥረት ተጎድቷል።
በዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት ልኬት (ልየታ ከተደገላቸው) 41 በመቶ የዋግ ኽምራ ህፃናት “በአጣዳፊ እና መካከለኛ የምግብ እጥረት” መጎዳታቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“100 ህፃናት ብንለይ፤ ከምንለያቸው ህፃናት ሦስት በመቶዎቹ በጣም ከፍተኛ የሆነ የተወሳሰበ የምግብ እጥረት ችግር ያለባቸው እና ሆስፒታል ገብተው መታከም ያለባቸው ናቸው። ወደ 27 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አልሚ ምግብ የሚያስፈልጋቸው እና የነፍስ አድን ምግብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው” ብለዋል።
በዞኑ 68 በመቶ እናቶችም “በአጣዳፊ እና መካከለኛ የምግብ እጥረት መጎዳታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።
በወልዲያ ዩኒቨርስቲ መረጃ መሠረት ዳሰሳ በተደረገባቸው አራት ወረዳዎች 26 ሺህ 600 ህፃናት እና ነፍሰ ጡር እንዲሁም አጥቢ እናቶች “በአጣዳፊ እና መካከለኛ የምግብ እጥረት” የተጎዱ ናቸው።
ዩኒቨርስቲው በዳሰሳ ጥናቱ በዞኑ የምግብ እጥረት የ18 ህፃናት ሕይወት እንዳለፈ የጠቀሰ ሲሆን፤ የጤና መምሪያ ኃላፊው ሞቶች እንዳሉ አረጋግጠው፤ ትክክለኛ የሞቱን ምክንያት ለማወቅ ግን እየተጠና ነው ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ህፃናት እና እናቶች “ፕሮግራም” ውስጥ ገብተው መታከም እንዳለባቸው የሚያሰምሩት ኃላፊው፤ ሆኖም በተለምዶ አጠራር እንደ ፋፋ ያሉ አልሚ (ማሟያ) ምግቦች እጥረት እና የተደራሽነት ችግር እንዳለ አስታውቀዋል።
“እስካሁን በተሟላ መንገድ ምላሽ አልተሰጠም” የሚሉት ኃላፊው፤ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ “የመንግሥት መኪኖች ተንቀሳቅሰው ሎጀስቲክስ አድርሰው ምላሽ እየሰጡ አይደለም” ሲሉ ችግሩ “እየተባባሰ” ነው ብለዋል።
በዋግ ኽምራ ዞን እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች የተቀሰቀሱ ሲሆን፤ ውሃ ወለድ የሆኑ እንደ ተቅማጥ እና ትራኮማ ያሉ በሽታዎችም መከሰታቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
የረድኤት ድርጅቶችን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ተቋማት ስለተከሰተው የምግብ እጥረት ከአንድ ወር በፊት ማሳወቃቸውን የገለፁት አቶ አሰፋ፤ “እስካሁን ብዙም ምላሽ አልተገኘም” ብለዋል።
የደሃና ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መላክ እንደ መድኃኒት እና አልሚ ምግብ ያሉ እጥረት ያለባቸው ግብዓቶች ካልተገኙ “ከዚህ በላይ የከፋ ችግር” ይከሰታል የሚል ስጋት አላቸው።
“አሁን ባለው መከላከል እና መቆጣጠር እንችላለን። ግን ወደ ፊት እየከፋ ከሄደ ግን ከዚህም በላይ የሰው ሕይወት ልናጣበት እንችላለን። ከፍተኛ የሆነ ረሃብም [ሊከሰት ይችላል]፤ ትውልድም ሊጎዳ ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
አፋጣኝ የነፍስ አድን የምግብ ድጋፍ እና መድኃኒት እንደሚያስፈልግ የሚወተውቱት የዋግ ክምራ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊም፤ ይህ ካልሆነ ግን ከዚህ በፊት ያጋጠመ አሳዛኝ ታሪክ ይደገማል የሚል ስጋት አላቸው።
“አፋጣን ምላሽ ካልተሰጠ በተለይ ህፃናትን ማከም እና ማዳን አዳጋች ይሆናል” ሲሉ ስጋታቸውን የሚናገሩት አቶ አሰፋ፤ “የ77ቱ አይነትአደጋ” ይፈጠራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጉዳት ለደረሰባቸው የዋግ ኽምራ ዞን ነዋሪዎች ድጋፍ ለማቅረብ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በሚመለከት ቢቢሲ የዞኑን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊን ለማናገር ለቀናት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)