አየር መንገዶች በ737 ማክስ አውሮፕላን የበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓት ውስጥ ሊላላ የሚችል ብሎን ላይ ፍተሻ እንዲያደርጉ በቦይንግ ማሳሰቢያ ተሰጠ።
የአሜሪካው ግዙፍ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየውን አውሮፕላኑን የተመለከተ ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው በበረራ መቆጣጠሪያ ስርዓት ውስጥ አንድ ብሎን ያለማቀፊያ ከተገኘ በኋላ ነው።
ቦይንግ የሚላላ ብሎን ተገኝቶበታል ያለው አውሮፕላን 737 ማክስ አውሮፕላን ከአምስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ባጋጠመ አደጋ ምክንያት ከበረራ የታገደው አውሮፕላን ነው።
ኩባንያው ለጥንቃቄ ሲባል 737 ማክስ አውሮፕላን ባለቤት የሆኑ አየር መንገዶች በአውሮፕላኑ ላይ ፍተሻ አድርገው ውጤቱን እንዲያሳውቁኝ እፈልጋለሁ ብሏል።
ቦይንግ ሰራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ልል ብሎን በተመለከተ በቅርበት ክትትል እያደረጉ ነው ብሏል።
ቦይንግ በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ሊላላ ይችላል የተባለውን ብሎን በተመለከተ ሁለት ሰዓታት ሊፈጅ በሚችለው ፍተሻ በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንዲካሄድ ለአየር መንገዶች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።
ቦይንግ ከእያንዳንዱ በረራ በፊት ባለሙያዎች በሚያደርጉት የተለመደ ፍተሻ ይህን ችግር ሊለዩ ይችላሉ ብሏል።
የበረራ ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት አንቶኒ ብሪክሃውስ ኩባንያው ለዚህ ክስተት ትልቅ ትኩረት መስጠት አለበት ካሉ በኋላ እንደ ለአጠቃላይ የአየር ጉዞ ተጠቃሚዎች ግን ይህ ክስተት የደኅንነት ስጋት መፍጠር የለበትም ብለዋል።
ቦይንግ ብዙ ባነጋገረው የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሰርዓት ላይ የብሎን መላለት ችግር ሪፖርት መደረጉን ይፋ እንዳደረግ የገበያ ድርሻው በ1 በመቶ ቀንሷል።
ቦይንግ 737 ማክስ ከሁለቱ አደጋዎች በኋላ ለ20 ወራት ታግዶ ቆይቶ እአአ 2020 ላይ በአሜሪካ መንግሥት ዳግም ወደ በረራ እንዲመለስ ተፈቅዶለታል።
በአውሮፕላኑ ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ከተነሳ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ለመግዛት ከአምራቹ ጋር ስምምነት ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
በቅርቡ በዱባይ ኤየር ሾው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 20 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ጨምሮ 31 አውሮፕላኖች ለመግዛት ከአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ጋር ከስምምነት መድረሱ ይታወሳል።