1 ታህሳስ 2023
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (ኢኤሲ) አዳዲስ አባላትን በመቀበል በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶማሊያ በቅርቡ የኢኤሲ አባል ሆናለች። በማስከተልም በአካባቢው ብዙ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያም የማኅበሩ አባል እንደምትሆነ የተዘገበ ሲሆን፣ ጂቡቲም አባል የመሆኗ ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው እየተባለ ነው። የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ማኅበር የሆነው ይህ ስብስብ በአገራት መካከል ነጻ እንቅስቃሴ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።ታጣቂው እስላማዊ ቡድን ስጋት የሆነባት እና በአካባቢው ረጅም የባሕር ዳርቻ ያላት ሶማሊያም ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገቷን ለማጠናከር በማሰብ ማኅበረሰቡን መቀላቀሏ ተገልጿል።
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ማን ነው?
በሦስት አገራት ፊርማ እአአ በ1999 የሆነው ማኅበረሰቡ በቀዳሚነት ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የመሠረቱት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን የያዙ አገራት በአባላቱ ናቸው።የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ማኅበር የሆነው ኢኤሲ መቀመጫውን አሩሻ ታንዛኒያ ላይ ነው። በሦስት አገራት የጀመረው ስብስብ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲን አካቶ እየጎለበተ በመሄድ አሁን አባላቱ ስምንት ደርሰዋል። ኢኤሲ አዲስ የተቀላቀለችው ሶማሊያን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ቡሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያን አካቶ እያደገ ነው።ማኅበሩ ራዕይ ብሎ የተነሳው የበለፀገ፣ ተወዳዳሪ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የተረጋጋ እና በፖለቲካዊ አንድነት ያለው ምሥራቅ አፍሪካን መመሥረት መሆኑን በድረ ገጹ አስፍሯል። ከምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ባሻገር በቀጠናው በርካታ አገራትን አቅፎ የሚገኘው አካባቢያዊው ስብስብ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ተቋም–ኢጋድ ይገኛል።
ኢጋድ እና ኢኤሲ ምንና ምን ናቸው?
ሁለቱንም በግርድፉ ከተመለከትን ዓላማቸው ተመሳሳይ ነው ይላሉ መቀመጫቸውን ኔዘርላንድስ ያደረጉት የአፍሪካን ኦሪንታል ጥናት ዘርፍ ተመራማሪው አቶ ነአምን አሸናፊ። ትኩረታቸው ደግሞ የዜጎችን ደኅነነት ማስጠበቅ እና በተለይም ልማትን ማስረጽ ላይ ነው። ሁለቱም ዓላማቸው አንድ ይምሰል እንጂ የሚያተኩሩት በተለያየ ጉዳይ ላይ ነው። በተለይም ኢጋድ እንደ አዲስ ከተመሠረተ በኋላ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ኢኤሲ ግን በዋነኝነት የኢኮኖሚ እና የንግድ ትስስርን በማሳለጥ የአካባቢውን አገሮች ተጠቃሚ ማድረግን መርጧል።“ኢኤሲ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት በማድረግ ማኅበረሰቡን ወደ ማስተሳሰር፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ወደ ማስፋት፣ ታሪፎችን ወደ ማሻሻል፣ የጋራ የሆኑ የጉምሩክ ማዕከላትን በመፍጠር ተደራራቢ ታክሶችን በማስቀረት እና ወጥ የሆነ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ላይ አተኩሯል” ይላሉ አቶ ነአምን። በተቃራኒው ደግሞ ኢጋድ ለማተኮር የሚፈልገው በአካባቢው አገራት ሠላም እና ደኅንነት እንዲሰፍን ነው። በደቡብ ሱዳን፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የነበረው ድርሻ እዚህ ላይ በምሳሌነት ይነሳል። አሁንም በሱዳን ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚያድርገውን ጥረት በመጥቀስ “በአጠቃላይ በፖለቲካ ላይ በማተኮር ሠላም እና ደኅንነት ላይ ይሠራል።” ይህ አንዳንድ ጊዜ የሚና መደራረብን ሊፈጥር ይችላል። አብዛኛዎቹ አገራት ግብርና ላይ ተመሠረተ ምጣኔ ሃብት ያላቸው በመሆኑ በአባል አገራት መካከል ፉክክር ሊኖር ይችላል። “በሁለት አገራት መካከል ያለን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተመለከተ ግጭትን ከማረቅ አንጻር፤ በአካባቢው ላይ ካለው ሽብርተኝነትን፣ ግጭትን ወዘተ በጋራ መሥራት ላይ የመተላለፈ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” ይላሉ አቶ ነአምን። አሁን ባለው ሁኔታ የኢኤሲ አባል ሆነው የኢጋድ አባል የሆኑ እንዳሉ ሁሉ፣ የኢኤሲ አባል ሆነው የኢጋድ አባል ያልሆኑ አገራት አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በሁሉቱም ማኅበራት ውስጥ አባል ናቸው። በሌላ መልኩ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ያሉት የኢጋድ አባል አገራት፣ እስካሁን የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዋነኛው የምጣኔ ሃብት ትስስርን (ኢኤሲ) አልተቀላቀሉም። ከዚህ አንጻር በአገራቱ መካከል የራስን ጥቅም በሌላኛው አገር ከማስጠበቅ አንጻር መደራረቦች አልፎ አልፎም የመጠላለፈ ነገሮች እንዳሉ አቶ ነአምን አሸናፊ ይናገራሉ። የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ መቀመጫ የሆነችው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ (ከግራ)፣ አዲሷ የማኅበሩ አባል ሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ (ከመሃል) እና የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ፒተር ማቱኪ (ከግራ)
አዲሷ አባል አገር ሶማሊያ
ሶማሊያ ለቀጠናው አገራት የስጋት ምንጭ ናት። አልሸባብ ከአገሪቱ በመነሳት በኬንያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያም ጥቃት ይፈጽማል። ይህም አገሪቱን ወደ የትኛውም የአገራት ስብስብ ማስገባት ስጋትን ይፈጥራል።“[ሶማሊያ] አባል ስትሆን ነጻ የሰዎች ዝውውር ትጀመራለች። የሶማሊያ ዜጋ ያለምንም ችግር ወደ እነዚህ አገራት ሊገባ ይችላል። በዚህም አሸባሪዎች ሌላ አገር ገብተው ጥቃት ሊያደርሱ ይችላል የሚል ትልቅ ስጋት ነበረ። እሱም ሶማሊያ ኢኤሲን እንዳትቀላቀል ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል” ብለዋል አቶ ነአምን። ሆኖም ሶማሊያ የሽብር ቡድንኑን ለመዋጋት የምትሞክረው በእነዚህ አባል አገራት እና በአሚሶም ጥምር ጦር ድጋፍ ነው። አብዛኛው በሶማሊያ ያለው የሠላም አስከባሪ ኃይል የተዋቀረውም ከኢጋድ እና ከኢኤስ አባል አገራት ነው። ስጋቱን በተመለከተም “እርዳታችሁ ያሻኛል፤ ስጋቱን በጋራ የምናስወግደው ይሆናል። ጠላትነቱ የእኔ ብቻ አይደለም…በጋራ ልንዋጋው የሚገባ ስለሆነ አግዙኝ ብላለች” በማለት ወደ ስብስቡ ለመግባት መቻሏን ጠቁመዋል። ሶማሊያ ጥቅም ላይ ያልዋለ እምቅ ሐብትም አላት። አፍሪካ ውስጥ ረዥሙ የባሕር ዳርቻ ያላት አገር ሶማሊያ ናት። በዚህ የባሕር ዳርቻ ላይ ፈቃድ ያለው፣ በአገራት ይሁኝታ የተመሠረተ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሊገነባ ይችላል። ይህ ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅሙን ሰፊ ያደርገዋል። የሶማሊያ ዓሳ ሃብት እጅግ ከፍተኛ ነው። እስካሁንም ጥቅም ላይ አልዋለም። በተጨማሪም ሶማሊያ በሙዝ ምርትም ትታወቅ ነበር። ይህን ዕድል ተጠቅማ ያላትን ሃብት ልትጠቀምበት ትችላለች። “ሶማሊያ ለአካባቢው አገራት ከፍተኛ የዓሳ ምርት ማቅረብ ትችላለች። ይህ ለአገሪቱ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ ተጠቃሚነትን የሚፈጥር ነው” ይላሉ አቶ ነአምን። ስለዚህም የማኅበሩ አባል አገራት ቁጥር ሲጨምር በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሰማት አቅማቸውም ይጨምራል። ሶማሊያም ከዚያ ትጠቀማለች። ብቻዋን ከመቅረብ ይልቅ በጋራ መምጣቷ ተጠቃሚ ያደርጋታል እንደሚያደርጋት በማመን ነው ኢኤሲን የተቀላቀለችው። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አገራቸው የማኅበሩ አባል መሆኗ ለአገራቸው ብልጽግና “የተስፋ ብርሃንን የሚፈነጥቅ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ኢኤሲ
የኢትዮጵያ እና የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ስም በተደጋጋሚ አብሮ እየተነሳ ነው። ኢትዮጵያ ማኅበረሰቡን እንድትቀላቀል ጥሪ እንደቀረበላት ተደጋግሞ ተዘግቧል። ኢትዮጵያ የዚህ ስብስብ አባል መሆኗ እንደሚጠቅማት ነአምን ይገልጻሉ “ምሥራቅ አፍሪካን ስትይዝ ስለትልቁ አፍሪካ ማውራት ይቻላል። ኢትዮጵያ የምታተርፈው በጋራ መሰማትን ነው። ብሪክስ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት አለ። ሰብሰብ ብሎ ከአካባቢው አገራት ጋር መምጣት ይቻላል።” ኢትዮጵያ ማኅበረሰቡን ብትቀላቀል የኢኤሲ አባል አገራት የሕዝብ ብዛቱ ወደ 500 ሚሊዮን ይደርሳል። ማኅበረሰቡ ይህንን ሁሉ ሰው ይወክላል ማለት ጥንካሬውን በማጉላት የትስስሩን ስፋት ያጎለብተዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ የማኅበረሰቡ አባል መሆኗ ለእራሷ እና ለዜጎቿ ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጥንካሬን በመጨመር እንዲጎለብት ያደርገዋል። አቶ ነአምንም “ኢትዮጵያ ማኅበሩን ስትቀላቀል እነዚህ ዘጠኝ አገራት የሚያወሩት ስለዚህ ሁሉ ሕዝብ ስለሚሆን የመሰማት ዕድላቸው ይጨምራል። ኢትዮጵያም ተጠቃሚ ትሆናለች” ብለዋል። ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ይዛ ባሕር በር አልባ የሆነችው የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የባሕር በር ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ መያዙን ይፋ አድርጓል። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለውጪ እና ገቢ እቃዎች በዋናነት የጂቡቲን ወደብ እየተጠቀመች ያለችው ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገራት ጋር በመነጋገር እና ሰጥቶ በመቀበል መርኅ የባሕር መተላለፊያ ለማግኘት ፍላጎት አላት። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን በአባልነት ብትቀላቀል የወደብ አማራጮችን ጨምሮ ሌሎች የምታኔ ሃብት ዕድሎችን እና ጠቀሜታን ታገኛለች። “ለምሳሌ ሶማሊያ የማኅበረሰቡ አባል ሆናለች። የሶማሊያን ወደብ እየተጠቀመች አይደለም። ኢትዮጵያ ማኅበረሰቡን ብትቀላለቅ ባለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረት ሳይሆን፣ የጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ ስላለው በዚያ መንገድ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የባሕር በር ወይንም ወደብ አገኘች ማለት ነው” ሲሉ አቶ ነአምን አስረድተዋል። አክለውም ይህ አማራጭ በሰላማዊ መንገድ ግጭቶች ሳይኖሩ መካረሮች እና የቃላት ውርወራ ሳይኖር ኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ የወደብ ዕድል እንድታገኝ ከማድረጉ ባሻገር ወደ 120 ሚሊዮን ለሚጠጋው ሕዝቧ ሰፊ የሥራ ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ይህ ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከሚፈጥረው አውንታዊ ዕድሎች በተጨማሪ የሚፈጠሩ ስጋቶች አሉ። ምሳሌ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በግብርና ላይ ተመሠረተ ምጣኔ ሃብት አላት። ሁለቱም ጋር ከፍተኛ የቀንድ ከብት እና የቡና ምርት አለ። ይህ በሁለቱ አገራት መካከል ከፍተኛ የገበያ ፉክክር ሊፈጥር ይችላል። ሌላው ስጋት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን ብትቀላቀል ኢትዮጵያውያ በቀላሉ ወደ ማኅበረሰቡ አገራት ያለችግር ሊዘዋወሩ ስለሚችሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሊጨምር ይችላል።“ይህ ስጋት ሊቀለበስ የሚችለው [ኢትዮጵያ] በጋራ በምትመሠርተው የኢኮኖሚ እና የገበያ መረጋጋት እና ለዜጎቿ የሥራ ዕድል በመፍጠር ነው። …የሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም በጋራ መሥራትን እንደመፍትሄ ልታቀርብ ትችላለች” ይላሉ አቶ ነአምን አሸናፊ።