ኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያን አሊያም “ስቶክ ማርኬት” በአዲስ መልክ ጀምራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ታሪካዊ” ሲሉ በጠሩት ዕለት አርብ ጥር 2/2017 ዓ.ም. በደወል የኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት ለገበያ ክፍት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ በሶሻሊስቱ ደርግ አስተዳደር ወቅት ነበር እንዲዘጋ የተደረገው።
የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ – ኢኤስኤክስ) ተጨማሪ የውጭ ካፒታል በማስገባት የልማት ድርጅቶችን የግል የማድረግ ሥራውን እንደሚያፋጥነው ይጠበቃል።
በአፍሪካ አምስተኛ ትልቁ ምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ለውጭ ገበያ ክፍት ማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አንዱ ዕቅድ ነው። ከዚህ ቀደም በነበረው አስተዳደር የሀገሪቱ ገበያ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበር።
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ጥላሁን ካሳሁን “መንግሥት ባሳየው ፍላጎት መሠረት ከሀገር ውስጥ አማራጮች የብድር ካፒታሉን ማሳደግ ነው ዋና ዓላማው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ባለፈው ሐምሌ ኢትዮጵያ የብር ዋጋን ዝቅ በማድረግ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ 10.7 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘቷ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር የውጭ ምንዛሪ ገበያው መንግሥት ባስቀመጠው ተመን መሠረት የሚተዳደር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በገበያው እንዲወሰን ክፍት እንዲሆን ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ደግሞ የውጭ ሀገራት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ እና የውጭ ሀገራት ዜጎች የባንክ አክሲዮን መግዛት እንዲችሉ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል።
ምንም እንኳ ሕጉ ባይፀድቅም የኬንያ፣ የሞሮኮ እና የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የስቶክ ማርኬት መጀመር ትልቅ እርምጃ እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ያስረዳሉ።
ኢኤስኤክስ እንዴት ይሠራል?
የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) 25 በመቶ ድርሻው በመንግሥት የተያዘ ሲሆን፣ የተቀረው 75 በመቶ ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ተመድቧል።
38 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ የሚያንቀሳቅሰው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መንግሥትን ወክሎ በኢኤስኤክስ ይንቀሳቀሳል።
ኢኤስኤክስ ባለፈው ዓመት ኅዳር ካፒታል ማሰባሰብ ሲጀምር ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ባለሀብቶች 631 ሚሊዮን ብር ለማስገባት አቅዶ ነበር።
ሚያዚያ 2016 ዓ.ም. የካፒታል ማሰባሰብ ሥራውን ሲያገባድድ ካሰበው በላይ እጥፍ ማለትም 1.51 ቢሊዮን ብር አሊያም 26.6 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል።
“እንደኛ ያለ ትልቅ ገበያ ዋነኛ ማነቃቂያው እምቅ ምጣኔ ሀብት እና ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ኢንቨስተሮች የሚታይ ተሳትፎ ነው” ይላሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ።
ኢኤስኤክስ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ነው የሚተዳደረው። ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ለሟሟላት በሚል በገበያ መር የዋጋ አወጣጥ ሥራውን ያከናውናል።
መንግሥት የልማት ድርጅቶችን የግል ለማድረግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ መሠረት ግዙፉ ኢትዮ ቴሌኮም በኢኤስኤክስ የሚመዘገብ የመጀመሪያው ድርጅት ይሆናል።
“የ130 ዓመት ዕድሜ ያለው ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻውን ለገበያ ያቀርባል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት ግብይት መንገድ የሚጠርግ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤክስ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢኤስኤክስ ከመከፈቱ በፊት ኢትየ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻውን ለሕዝብ ክፍት አድርጓል።
“ሰዎች በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ካለው ሀብት የራሳቸውን ድርሻ መግዛት መቻላቸው ደስተኛ አድርጓቸዋል” ሲሉ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ፌርፋክስ አፍሪካ ግሎባል ፈንድ ኃላፊ የሆኑት ዘመዴነህ ንጋቱ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“የኢትዮጵያ ዕድገት የሚያፋጥነው የሀገር ውስጥ የግል ዘርፍ ነው” ሲሉም ያክላሉ።
ዶ/ር ጥላሁን እንደሚሉት ወደፊት ሌሎች የልማት ድርጅቶችን በኢኤስኤክስ የማስመዝገብ ሥራውን ተጠናክሮ ይቀጥላል።
“ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ 10 የሚሆን ድርጅቶች ገበያውን ለመቀላቀል የዝግጅት ሥራ እያከናወኑ ነው” ይላሉ።
ኢኤስኤክስ ለኢትዮጵያዊያን ያለው ጥቅም ምንድነው?
ኢኤስኤክስ በኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ ድርሻ ላላቸው አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ይገመታል።
አብዛኛዎቹ አነስተኛ እና መካከለኛ ‘ቢዝነሶች’ ብድር ለማግኘት ሲቸገሩ ቆይተዋል። ኢንተርፕራይዞቹ በባሕላዊ መንገድ ከባንክ አሊያም ከትስስር በሚደረግ የብድር ሥርዓት ነበር ካፒታል የሚያገኙት።
የስቶክ ማርኬት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ግን ድርሻቸውን በመሸጥ ካፒታል በማሰባሰብ ሥራቸውን ማስፋት እና ሥራ መፍጠር እንደሚችሉ ሙያተኞች ይተነትናሉ።
“በርካታ በቤተሰብ የተያዙ ቢዝነሶች አሉ። አዳዲስ ፈጠራዎችን ይዘው የመጡ ሰዎች አሉ። አሁን ትልቅ የካፒታል ገበያ ያገኛሉ ማለት ነው” ይላሉ ዘመዴነህ።
የኢኤስኤክስ መከፈት ለኢትዮጵያውያን ያለው ሌላኛው ጥቅም ድርሻ በመግዛት ትውልድ የሚሻገር ሀብት መግዛት ነው።
ዘመዴነህ እንደሚሉት “ስቶክ ኤክስቼንጅ (የመዋዕለ ንዋይ ገበያ) ምን ማለት እንደሆነ ለሕዝቡ የማሳወቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።”
የምጣኔ ሀብት ለውጡ እንዴት ይታያል?
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምጣኔ ሀብት ክለሳ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ዓለም የተለያዩ አስተያየቶች እያስተናገደ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2021 የቴሌኮም ገበያውን በ850 ሚሊዮን ዶላር ለኬንያው ሳፋሪኮም ስትሸጥ እርምጃው አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ ነበር።
70 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም የኔትዎርክ ገበያውን ለዓመታት ተቆጣጥሮት ቆይቷል።
ሳፋሪኮም በ2023 የገንዘብ መለዋወጫ የሆነውን ኤምፔሳ ለገበያ በማስተዋወቅ በወራት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራት ችሏል።
ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት በርካታ ኢትዮጵያውያን የምጣኔ ሀብት ክለሳውን በተመለከተ ያላቸው አስተያየት አሉታዊ ነው።
ለምሳሌ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅደው ረቂቅ ሕግ የሀገር ውስጥ ባንኮችን ስጋት ላይ የጣለ እርምጃ ነው።
ረቂቅ አዋጁ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች እስከ 40 በመቶ ቀጥተኛ ድርሻ እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ሲሆን፣ ድርሻው በውጭ ምንዛሪ እንዲሆን ያስገድዳል።
የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የመንግሥት ንብረት በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይነት ሥር ያለ ሲሆን፣ የተቀሩት ሌሎች 32 ባንኮች የሀገር ውስጥ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚለው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት በሚል ለአምስት የውጭ ሀገር ባንኮች ፈቃድ ይሰጣል።
ሌላኛው ሕዝቡን ስጋት ላይ የጣለው ጉዳይ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዋጋው 50 በመቶ እንዲወርድ የመደረጉ ነገር ነው። ይህ እርምጃ እያሻቀበ ያለውን የኑሮ ውድነት ያባብሰዋል በሚል አንዳንድ ሰዎች ዶላር ማከማቸትን መርጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ስጋት ለማቅለል በሚል ለመንግሥት ሠራተኞች የ300 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የወደፊት ዕጣ ፈንታ
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የወደፊት ዕታ ፈንታ የሚወሰነው ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን የዋጋ ግሽበት፣ ዕዳ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዴት ትወጣዋለች በሚለው ጥያቄ መልስ ላይ ነው።
“ፈተና ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በእኔ ዕይታ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ወደ ቀጣዩ ደረጃ እንዲሻገር የፖሊሲ ክለሳው አስፈላጊ ነው” ይላሉ ዘመዴነህ።
ኢትዮጵያ ከአበዳሪዎቿ ጋር የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ውይይቶች በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ሀገሪቱ ያለችበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮችን ለመጋበዝ አንዱ ደንቃራ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት የውጭ ኢንቨስትመንቱን የጎዳው ሲሆን፣ አይኤምኤፍ በአሁኑ ወቅት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ያሉ ግጭቶችን “አሳሳቢ ናቸው” ሲል መግለፁ ይታወቃል።
ነገር ግን ባለሙያዎች ሀገሪቱ ትክክለኛውን ድጋፍ ካገኘች የምጣኔ ሀብት ክለሳው ውስብስብ ለሆነው ችግር መፍትሔ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
“የሚመጡት አምስት እና አስር ዓመታት የውጭ ኢንቨስትመንት በሰፊው እንደምንስብ አስባለሁ። በትክክለኛው መንገድ ከሄድን ቢሊዮን ዶላሮች ልናስገባ እንችላለን” ይላል ዶ/ር ጥላሁን።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)