8 ታህሳስ 2023
በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን በበጎ ከሚያስነሱ ጉዳዮች አንዱ ስፖርት ነው። በተለይም አትሌቲክስ። ከአትሌቲክስም ረዥም ርቀት ለአገሪቱ ስም ለአትሌቶቹ ደግሞ ክብር እና ጥሩ ገቢ የሚያገኙበት ነው። ይህ መልካም ስም ግን አልፎ አልፎ ጥቁር ነጥቦች እያጋጠሙት ነው። በቅርቡ ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ ስምነት አትሌቶች ቅጣት ተላለፎባቸዋል። ሁለቱ ደግሞ ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ ጊዜያዊ እገዳ ተጥሎባቸው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታውቋል።
አበረታች ቅመም ምንድን ነው?
“ስፖርተኞች ተፈጥሯዊ ከሆነ መንገድ እና ሥልጠና ውጪ ብቃታቸውን ለማሳደግ ጥቅም ሊያገኙባቸው የሚችሉ እና የሚወስዷቸው የተከለከሉ ንጥረ ነገሮች ብለን ልንወስድ እንችላለን” ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በየዓመቱ የተከለከሉ ቅመሞችን ዝርዝር ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ አበረታች የሚባሉትም እነዚህ በኤጀንሲው የተከለከሉ ቅመሞች ናቸው። እነዚህ ቅመሞች በመርፌ እና በክኒን መልክ ሊገኙ ይችላሉ። በምግብ መልክም ሊወሰዱ የሚችሉ ይገኙባቸዋል። አንዳንድ አበረታች ቅመሞች ደግሞ ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶች ናቸው።
ኢትዯጵያ ውስጥ ሁሉንም አበረታች ቅመሞች የመጠቀም ዕድል መኖሩን የሚጠቁሙት አቶ መኮንን “በዋናነት ለመድኃኒትነት የሚውሉት ይዘወተራሉ። ባለፉት ዓመታት ባደረግነው የምርመራ ውጤት ወይም ጥናትም ያረጋገጥነው ይህንኑ ነው” ብለዋል። ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉት አበረታች ቅመሞች በሕክምና ተቋማት ይገኛሉ። ፋርማሲዎች እና መድኃኒት አቅራቢዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ያስገቧቸዋል። እነዚህ በሕጋዊ መንገድ ሰዎች ለታመሙ ሰዎች ሕክምና የሚውሉ ናቸው። “ስፖተርኞቹ ከታመሙም መድኃኒቶቹን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለመጠቀም ግን ልዩ ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል። ስፖርተኞች ሲታመሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በሚሰጠው ፈቃድ መጠቀም ይችላሉ” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። በሕጋዊ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡትን መድኃኒቶች እንደ አበረታች ቅመም ያለፈቃድ መጠቀም ግን ቅጣት ያስከትላል። ሌሎቹ አበረታች ቅመሞች ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ ናቸው።
አበረታች ቅመሞች የአትሌቲክስ ፈተና?
አብዛኛው ሰው አበረታች ቅመሞችን ሲያስብ ከተወሰኑ የስፖርት ዓይነቶች ጋር ብቻ ይያያዛል። ነገር ግን የትኛው የስፖርት ዘርፍ ለአበረታች ቅመሞች ተጋላጭ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአበረታች ቅመሞች ቀዳሚው ተጋላጭ ስፖርት አትሌቲክስ ነው። አቶ መኮንን ለዚህ ምክንያቶች ያሉትን ዘርዝረዋል።“አንደኛ ተወዳጅ ስፖርት ነው። ሁለተኛ፣ በበዓለም አቀፍ ደረጃም ውጤት ያለው ስፖርት ነው። ሦስተኛው ደግሞ የገቢ ምንጭም ያገለግላል” ሲሉ አስረድተዋል። አትሌቲክስ ኢንዱራንስ (ጽናት እና ጥንካሬ) የሚፈልግ ስፖርት ነው። 10 ሺህ፣ ግማሽ ማራቶን እና ማራቶን እያለ ሲሄድ ደግሞ በራሱ የሚፈልገው ተጨማሪ ኃይል እና ጉልበት አለ። ይህ ደግሞ ስፖርተኞች ተጨማሪ ጉልበት እና ኃይል ወደሚያገኙበት አቋራጭ እንዲያማትሩ ያደርጋቸዋል።“ሁለተኛው ተጋላጭ ስፖርት እግር ኳስ ነው። እግር ኳሱም ተወዳጅ እና የገቢ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ብስክሌትም የኢንዱራንስ ስፖርት በመሆኑ ተጋላጭ ነው። ቦክስ እና ሌሎችም የግለሰብ ስፖርቶች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው። አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ ብስክሌት. . .ሁሉንም ስፖርቶች የሚመለከት ነው” ብለዋል።
አበረታች ቅመሞች አጠቃቀም እና ቅጣት
እንደ ባለሥልጣኑ ከሆነ በአውሮፓውያኑ 2023 በተካሄዱ ምርመራዎች 10 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም ተጠርጥረው ጉዳያቸው ሲጣራ ቆይቷል።“ወደ ስምንት የሚሆኑ አትሌቶች በእኛ እና በዓለም አትሌቲክስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። እነዚህ አበራታች ቅመሞችን ተጠቅመዋል ተብለው የተረጋገጠባቸው ናቸው” በማለት የሁለቱ ጉዳይ በመጣራት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። በዚሁ መሠረት ስምንት አትሌቶች የሕግ ጥሰት መፈፀማቸው በመረጋገጡ በአማካኝ ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ 4 ዓመት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዳይሳተፉ አስተዳደራዊ ቅጣት ተጥሎባቸዋል። እንዲሁም የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን በመሸጥ ብሎም ሙያቸውን ተገን በማድረግ ለአትሌቶች በመስጠት የሕግ ጥሰት በፈፀሙ መድኃኒት ቤቶች ላይም እርምጃ ተወስዷል።
“መያዝ የማይፈቀድላቸውን መድኃኒት የያዙ ፋርማሲዎች ነበሩ።. . . ለምሳሌ ኢፒኦን (ይህ የቀይ የደም ሴል ምርትን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር የኦክስጅን ዝውውርን በማጎልበት ብቃትን የሚያሳድግ ቅመም ነው።) ብንወሰድ መያዝ የሚፈቀድላቸው ፋርማሲዎች አሉ። ሳይፈቀድላቸው ይዘው ሲገኙ እነሱ ላይ እገዳ ይጣላል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። “[እንደ አበረታች ቅመም ጥቅም ላይ የሚውሉት] መድኃኒቶቹ በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ ናቸው። ያለሐኪም ትዕዛዝ ሸጠው የተገኙባቸው ሁኔታዎችም አሉ። ስፖርተኞችም ያለማዘዣ መግዛታቸው በመረጃ እና በማስረጃ ተደርሶባቸዋል። በዚህ መንገድ ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ የገቡ ፋርማሲዎች ተገኝተው እርምጃ ተወስዶባቸው የታገዱ አሉ” ሲሉም አስረድተዋል። በዚህ ድርጊት ውስጥ ጥሰት ፈጽመው የተገኙ አካላትም ጉዳያቸው በሕግ ተይዟል። በዚህ ምክንያትም ጉዳዩን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የስፖርተኞች ምርመራ ከውድድር በፊትም ሆነ በኋላ ይከናወናል። ምርመራው የሚደረገው ከአገር ውጭ ባሉ ቤተ ሙከራዎች ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ቤተ ሙከራዎቹን ለማቋቋም ባለሥልጣኑ እየሠራ እንደሚገኝ ባለሥልጣኑ አመልክቷል። ከዚህ አንጻር ጥሰቶች ተፈጽመው ሲገኙ የሚተላለፈው ቅጣት በቅንጅት የሚተላለፍ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን እና ሌሎችም ተቋማት በሕግ የተሰጣቸው ተግባር እና ኃላፊነት አለ።“ፋርማሲዎች እና የሕክምና ተቋማት ላይ እርምጃዎችን መውሰድ የሚችለው የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው። እርምጃዎችንም የወሰደው እሱ ነው።” በአትሌቶች ላይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥስልጣን ነው ኃላፊነት የተሰጠው። ስለዚህ ባለሥልጣኑ እርምጃዎችን ይወስዳል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ የሚወስዳቸው እርምጃዎች አሉ። በወንጀል የመጠየቁ ኃላፊነት ደግሞ የፖሊስ ይሆናል።
አበረታች ቅመሞች የሚያስከትሉት ምስቅልቅል
አቶ መኮንን ምርመራ ተደርጎላቸው አበረታች ቅመሞችን መጠቀማቸው ለተጋገጠባቸው ስፖርተኞች ውጤቱን በማሳወቅ ረገድ ብዙ ጉዳዮችን ተመልክተዋል።“ኢትዮጵያ ውስጥ [አበረታች ቅመም] የተወገዘ ነው። አበረታች ቅመሞች ተጠቀመ ተብሎ ከተጠረጠረ በሕብረተሰቡ ዘንድ እንደ ወንጀለኛ እና አጭበርባሪ ስለሚታይ በብዙ መንገድ አይበረታታም።”“ብዙ አትሌቶች ውጤቱ ሲነገራቸው ራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉበት ሁኔታ አለ። ብዙ ማስታወስ የማልፈልጋቸው አጋጣሚዎች አሉ። አንዳንዶች ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱት በሚያገኙት አነስተኛ ደመወዝ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸውን መርዳት የማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ።”
“በአጠቃላይ ከተቀጡ በኋላ ሕይወታቸው ይመሰቃቀላል። ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም የተጠቀሙት ላይ የሚደርሰው ጫና የሚያሳዝን ነው። ስፖርቱን እና አገርን ለማዳን ግን የግድ መቀጣት አለባቸው” ብለዋል። ቅጣት ሲተላለፍባቸው አልፎ አልፎ የሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት እንደሚሠራም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል። በጥናት ማረጋገጥ እንደሚያስፈለግ በመጠቆም “አንዳንድ ስፖርተኞች የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ትንሽ ችግር የሚፈጥሩ ናቸው” ሲሉም መድኃኒቶቹ ስላላቸው የጎንዮሽ ጉዳትም አንስተዋል።“በተለይ ሴት አትሌቶቻችን የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ባዮሎጂካል ሲስተማቸውን ጭምር የሚያዛቡ ናቸው። በተለይ ቴስቴስትሮን በሴቶች አካባቢ ችግር ይፈጥራል። እያየናቸው ያሉ ምልክቶችም አሉ። በተለያየ መንገድ ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ። ይህ ግን በጥናት መረጋገጥ አለበት” ብለዋል አቶ መኮንን።
አበረታች ቅመሞች ምን ያህል ስጋት ሆነዋል?
አበረታች ቅመሞች ጉዳይ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ስፖርት ላይ ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል። ስፖርቱ በጣም እያደገ እና እየዘመነ፣ በቴክኖሎጂ እየታገዘ ሲሄድ አበረታች ቅመሞች ጉዳይም በዚያው ልክ እየተወሳሰበ ነው። “ገንዘብ እና ጥቅም ባለበት ቦታ አጭበርባሪዎችም ከኋላ መምጣታቸው የታወቀ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ሲያድግ የፀረ አበረታች ቅመሞች ሥራም ካላደገ ስፖርቱ እየፈተነው ነው የሚሄደው።”አንደ አቶ መኮንን ከሆነ የአበረታች ቅመሞች አጠቃቀም አሁን ባለበት ደረጃ ብዙ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም እና ብዙ አድጓል የሚባልበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። ከስፖርቱ ዕድገት ጎን ለጎንም የፀረ አበረታች ቅመሞች እንስቃሴውም እያደገ የሚሄድ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። “እንቅስቃሴውን ዜሮ አድርገነዋል የምንለበት ደረጃ አይኖርም። የበለጠ ከስፖርቱ ጋር ጎን ለጎን እያደገ የሚሄድ ነው የሚሆነው። የተጋላጭነት ደረጃው ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው ምንለው ነው” ብለዋል። ስፖርቱን በአጠቃላይ በዚህ መልኩ የሚገልጹት አቶ መኮንን፣ አትሌቲክሱን ግን ለብቻ ማየትን ይመርጣሉ። አትሌቲክሱ የተሻለ ደረጃ ላይ በመገኘቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጋላጭነቱም ከፍ ያለ ነው መሆኑን ያነሳሉ። “ስፖርቱ ሲያድግ የሚያንቀሳቅሰው ኢኮኖሚ ከፍ ይላል። ተጋላጭነቱም በዚያው ልክ ይጨምራል” ብለዋል። ከመቆጣጠር በፊት ግን ባለሥልጣኑ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት አድርጓል። ስፖርተኞች የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡም ይሠራል። የሥልጠና መድረኮችም አሉት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ–አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 በይፋ የተቋቋመ ነው። ሁሉም ስፖርቶች ከአበረታች ቅመሞች የጸዱ እና ነፃ የሆኑ የሰፖርት ውድድሮች ሊተገበሩ ይገባል ብሎ ይሠራል። ኢትዮጵያ ስፖርት ከአበረታች ቅመሞች ነፃ የሆኑ ጤናማ ስፖርተኞችን በመፍጠር ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ተወዳድረው የማሸነፍ ባህል ለማየት ራዕይ ሰንቋል፡