ኤችአይቪን የሚከላከለው መድኃኒት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል? ለማንስ ነው የሚሰጠው? Leave a comment

5 ታህሳስ 2023

በቅርቡ ይፋ በሆነ ጥናት ፒአርኢፒ (ፕሪ ኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ) የተባለው መድኃኒት በሰውነት ውስጥ የኤችኤይቪ ቫይረስ ሥርጭትን በመግታት ውጤታማ መሆኑን አሳይቷል። ፒአርኢፒ በኤችአይቪ የመያዝ ዕድልን 86 በመቶ ይቀንሳል። በክሊኒክ ደረጃ የተደረጉ ሙከራዎች ደግሞ መድኃኒቱ 99 በመቶ ውጤታማ መሆኑን አሳይተዋል። ፒአርኢፒ የተሰኘውን ይህን መድኃኒት የኤችአይቪ ቫይረስ ወደ ሰውነት እንዳይገባ እና በሰውነት ውስጥ ከገባም በኋላ ራሱን እንዳያባዛ ማድረግ መቻሉ በዩናይትድ ኪንግደም በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል።

ፒአርኢፒ ምንድን ነው?

ፕሬፕ ወይንም ፕሪኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ (ፒአርኢፒ) ማለት ኤችአይቪን ቅድመ መከላከል ማለት ነው ይላሉ / አስቴር ሸዋማረ። በዘውዲቱ ሆስፒታል የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ኃላፊ የሆኑት / አስቴር ፕሬፕ ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ፣ አንዲሁም የተለያየ የኤችአይቪ ውጤት ባላቸው የትዳር አጋሮች መካከል ቫይረሱ በደሙ የሚገኝ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መውሰድ ሲጀመር፣ ሌላኛው አጋር ተመርምሮ ነጻ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ እንዲወስድ የሚደረግ መድኃኒት መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ጥንቃቄ የጎደለው ወሲባዊ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወይም ሌሎች በሚጋሩት በመርፌ/ስሪንጅ ዕጽ የሚጠቀሙ ሰዎችን በኤችአይቪ የመያዝ ዕድልን የሚቀንስ መድኃኒት ነው። ይህ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ቢወስዱት በሽታው የመያዝ ዕድላቸውን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሰው መድኃኒት በእንክብል ወይም በመርፌ መልክ ሊወሰድ ይችላል። እንደ የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ከሆነ ፒአርኢፒ የሚያስከትለው ይህ ነው የሚባል የጎንዮሸ ችግር የለውም።  አንዳንድ ሰዎች መድኃኒቱን ከወሰዱ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠፋ የራስ ምታት፣ ተቅማጥ፣ የድካም ስሜት እና የሆድ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ከመጋለጥ በፊት እና በኋላ የሚሰጥ

ፕሪኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ (ፒአርኢፒ) አንድ ሰው ከመጋለጡ በፊት የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከተጋለጠ በኋላ የሚሰጥ ደግሞ ፓስትኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ የሚባል መድኃኒት መኖሩንም / አስቴር አክለው ገልጸዋል። ለቅድመ መከላከል የሚሰጠው ፕሪኤክስፖዠር ፕሮፍላክሲስ (ፒአርኢፒ) መድኃኒትን ግለሰቡ ቢያንስ ለአንድ ዓመት እየወሰደ መቆየት እንደሚያስፈልገው / አስቴር ጨምረው ተናግረዋል። እንዲሁም ይህንን መድኃኒት መውሰድ የጀመረ ሰው በስድስት ወር ልዩነት የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ እና የቫይረሱ መጠን የማይቆጠር ደረጃ ላይ መድረሱን ማረጋገጥ ያስፈልገዋል። አንደ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ በኋላ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚወሰደው ፖስት ኤክስፖዠር የተባለው መድኃኒት የሚሰጠው ግን ለአንድ ወር ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ። / አስቴር ሸዋአማረ እንደሚሉት ከሆነ ፖስት ኤክስፖዠር የሚወስዱ ግለሰቦች በሥራ አጋጣሚ ለኤችአይቪ የተጋለጡ ናቸው። እነዚህም የሕክምና ባለሙያዎች ሆነው በሥራ አጋጣሚ ምክንያት ስለት ሲወጋቸው ወይንም ሲቆርጣቸው ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ በሚል የሚወስዱት መሆኑን / አስቴር ያስረዳሉ።

ፒአርኢፒ መውሰድ ያለበት ማነው?

ፒአርኢፒ ጠቃሚ የሚሆነው ኤችአይቪ በደሙ የሌለበት ሰው፣ እንዲሁም የኤችአይቪ ቫይረስ ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት የመፈጸም ዕድላቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ይህ ማለት መድኃኒቱን ቀድመው እንዲወስዱ የሚመከሩት በተደጋጋሚ ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ የሚፈጽሙ ወይም በዘላቂነት በኤችአይቪ ቫይረስ የመጋለጥ ዕድል ያለው ሰዎች ናቸው። ድንገተኛ በሆኑ አጋጣሚዎች ለኤችአይቪ ቫይረስ ሳልጋለጥ አልቀርም ብለው የሚገምቱ ሰዎች 72 ሰዓታት ውስጥ የዚህ መድኃኒት ዝርያ የሆነውን እና ፒኢፒ (ፖስትኤክስፖዘር ፕሮፒላሲስ) የተባለውን መድኃኒት ለመውሰድ ከጤና ባለሙያዎች ጋር መመካከር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ለደም ንክኪ ተጋላጭነት ያላቸው እና ለመደፈር የተጋላጭ የሆኑ ሰዎች መድኃኒቱን በመውሰድ በኤችአይቪ ቫይረስ የመያዝ ዕድላቸውን ለመቀነስ እንደሚችሉ ጥናቱ አረጋግጧል። አሜሪካንን ጨምሮ በበርካታ አገራት ፒአርኢፒ የሚወሰደው ወይም ከፋርማሲ መግዛት የሚቻለው በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ ነው። መድኃኒቱን መውሰድ የሚፈልግ ሰው ቀድሞ የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ እና ቫይረሱ በደሙ ውስጥ አለመኖሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ መድኃኒት ቅድመ መጋለጥ ዕድል ያላቸው፣ በቫይረሱ የመያዝ ከፍተኛ ተጋላጭነት ባላቸው ግለሰቦች በኤችአይቪ የመያዝ አደጋን ለመቀነስ ከማገልገሉ ውጪ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ላሉ ሰዎች የሚሰጥ አይደለም።

የመድኃኒቱ ተደራሽነት በኢትዮጵያ

ፕሬፕ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያም ውስጥ ለረዥም ዓመት ሲሰጥ እንደነበር የሚናገሩት / አስቴር በኢትዮጵያ ላሚቩዲን (lamivudine) እና ቴኖፎቪር (Tenofovir) የሚባሉ ሁለት መድኃኒቶች ተጣምረው የተሰራ አንድ መድኃኒት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ መድኃኒት በሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን፣ መድኃኒቱ የሚታዘዘው ግለሰቡን ሐኪም አይቶት፣ ምርመራ ተደርጎ እንዲሁም የተለያየ ውጤት ያላቸው ጥንዶችም ቢሆኑም የምክር አገልግሎት ተሰጥቶ እና መድኃኒቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው። ፕሪኤክስፖዠር በመድኃኒት ቤቶች የሚገኝ ሳይሆን፣ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት በሚሰጡ የመንግሥትም ሆነ የግል የሕክምና ተቋማት ብቻ የሚገኝ መሆኑንም ባለሙያዋ አክለው ተናግረዋል። የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች በሙሉ በነጻ እንደሚሰጥ ያስታወሱት / አስቴር፣ መድኃኒቱን መውሰድ የጀመረ ሰው በሚገባ ተከታትሎ መውሰድ እንደሚገባው እና የሚቋረጥ ከሆነ ምናልባትም ውጤቱ ሊቀየር ይችላል ሲሉ ያለውን አደጋ ይገልጻሉ።

መድኃኒቱ እንዴት ይወሰዳል?

በተለያዩ ምክንያቶች ለኤችአይቪ የመጋለጥ ከፍተኛ ዕድል ያላቸው ሰዎች መድኃኒቱን በክኒን መልክ በቀን አንዴ አሊያም ከወሲባዊ ግንኙነት ቀደም ብለው ሊወስዱት ይችላሉ። ይሁን እንጂ አርኢፒ 2-1-1 በሚባል መርሃ ግብር ሲወሰድ፣ በተለይ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ላሉ ወንዶች የበለጠ ውጤታማ እንደሆነ ጥናቱ ያሳያል። በመጀመሪያ 2 እንክብሎች ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት ከመፈጸሙ 2 አስከ 24 ሰዓታት ውስጥ ባለው ጊዜ ቀድሞ ይወሰዳሉ። ከዚያ የመጀመሪያዎቹ ሁለት እንክብሎች ከተወሰዱ 24 ሰዓታት በኋላ 1 እንክብል ይወሰዳል። ከዚያ ሁለተኛው ዙር እንክብል ከተወሰደ 24 ሰዓታት በኋላ የመጨረሻው 1 እንክብል ይወሰዳል። ነገር ግን የመድኃኒቱን ውጤታማነት የበለጠ ለማስጠበቅ ሐኪም በሚያዘው መሠረት መወሰዱ የበለጠ ጠቃሚ እንደሆነ ይመከራል። ፒአርኢፒ ሰዎች በኤችአይቪ የመያዝ ዕድላቸውን ይቀንሳሉ እንጂ እርግዝናን እና ሌሎች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በሚፈጸሙ ወሲባዊ ግንኙነቶች የሚመጡ በሽታዎችን አይከላከልም።  ስለዚህም ሰዎች ከሌሎች ተጓዳኝ የአባላዘር በሽታዎች እራሳቸውን ለመጠበቅ ኮንዶም መጠቀም እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።

መድኃኒቱን ተደራሽ ማድረግ

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ውስጥ በኤችአይቪ እና በሥነተዋልዶ ጤና ላይ የሚሠራው ትሬንስ ሂጊንስ የተባለ ድርጅት መድኃኒቱን ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ መሠራት አለበት ብሏል። የድርጅቱ የፖሊሲ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑ ዴቢ ላይኮክብዙ ሴቶች ፒአርኢፒ ስለመኖሩ እንኳ ጨርሶ አያውቁምያሉ ሲሆን፤ከፒአርኢፒ ብዙ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ የማኅብረሰብ አባላት እና ግለሰቦች እንዳሉ ብናውቅም መድኃኒቱን ግን ማግኘት አይችሉምብለዋል። ይህንን መድኃኒት ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ተደራሽ ለማድረግፒአርኢፒ በመድኃኒት ቤቶች እና በበይነ መረብ (ኦንላይን) ተደራሽ እንዲሆንዴቢ ጠይቀዋል። የዩኬ ጤና ደኅንነት ኤጀንሲ የመድኃኒቱ ውጤታማ መሆን የአገሪቷ መንግሥት 2030 የኤችአይቪ/ኤደስ ሥርጭትን ዜሮ ለማድረስ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ይረዳል ብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want