“እርዳታ ያስፈልገናል”: ከምያንማር የወንጀል ካምፖች የተለቀቁ ኢትዮጵያውያን ስጋት ውስጥ ገብተዋል!!! Leave a comment

“እግዚአብሔርን፤ እርዳታ ያስፈልገኛል” ይላል በምያንማር ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያለው ኢትዮጵያዊው ወጣት።

ራሱን “ሚኪ” ብሎ የሚጠራው ይህ ወጣት፤ ምያንማር ወስጥ በታይላንድ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ህንጻ ውስጥ ከሌሎች 450 ሰዎች ላይ ታስሮ እንዲቆይ መደረጉን ይናገራል።

በመጠለያው ውስጥ የታሰሩት 450 ሰዎች፤ ላለፉት ዓመታት በድንበር አካባቢው ላይ ሲስፋፉ ከቆዩት ታዋቂዎቹ የማጭበርበሪያ ግቢዎች የተለቀቁ ናቸው። ተጎጂዎቹ ከግቢዎቹ የተለቀቁት፤ በታይላንድ እና ምያንማር ድንበር ላይ በሚፈጸመው በዚህ የወንጀል ‘ኢንዱስትሪ’ ላይ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እርምጃ በመወሰዱ ነው።

ነገር ግን የተለቀቁት ተጎጂዎች ላይ ሚደረገው ምርመራ እና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ የማመቻቸቱ ሂደት አዝጋሚ በመሆኑ ብዙዎቹ በምያንማር ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ለመቆየት ተገድደዋል።

ተጎጂዎቹን የያዛቸው ታጣቂ ቡድን ከሰባት ሺህ በላይ የሚሆኑትን እነዚህን ተጎጂዎች ለመደገፍ የሚያስችል አቅም የለውም። ከምፖቹ የሚወጡ ተጎጂዎችን ወደ አጎራባቿ ታይላንድ የማዘዋወር ሂደት ፈጣን ባለመሆኑ በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሰዎችን ማስወጣት ማቆማቸውን ከታጣቂዎቹ አንዱ ይናገራል።

ተጎጂዎቹ የተቀመጡባቸው መጠለያዎች ንህፅና የጎደላቸው እና ምግብ በበቂ ሁኔታ የማይቀርብባቸው ናቸው። በውስጣቸውም እንደ ኢትዮጵያዊው ሚኪ፤ የጤና እክል ያላቸው ብዙ ነጻ የወጡ የግዳጅ ሠራተኞችን ይዘዋል።

በካምፑ የሚገኙ ሰዎች ግድግዳ ተደግፈው ተኝተው

የፎቶው ባለመብት,Getty Images

ሚኪ፤ በማጭበርበሪያ ካምፕ ውስጥ ለአንድ ዓመት የሠራ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ድብደባ ይፈጽምበት ነበር። አሁን በድንገተኛ የመረበሽ ስሜት እና ህመም (panic attack) እየተሰቃየ ነው።

በቀን ሁለት ጊዜ እዚህ ግባ የማይባል ምግብ እንደሚሰጣቸው የሚናገረው ሚኪ፤ ለ450 ሰዎች የተዘጋጀው መጸዳጃ ቤት ሁለት ብቻ እንደሆነ ያስረዳል። ብዙ ሰዎች ወደ መጸዳጃ ቤት ሚሄዱት ዕድል ቀንቷቸው ክፍሉ ሰው በማይኖርበት ጊዜ ነው።

ሚኪ፤ ወደ ምያንማር የሄደው ከአንድ ዓመት በፊት ታይላንድ ውስጥ ጥሩ እንግሊዘኛ እና ኮምፒውተር ላይ የመጻፍ ችሎታ ብቻ የሚጠይቅ ጥሩ ሥራ እንደሚያገኝ ቃል ተገብቶለት ነው።

ከሀገሩ ከወጣ በኋላ ግን ራሱን ያገኘው በቻይናዊ አለቆች በሚመሩ አስከፊ የበይነመረብ (ኦንላይን) ማጭበርበሪያ ካምፕ ውስጥ፤ በየቀኑ አጭበርብሮ ገቢ እንዲያደርግ የሚሰጠውን የገንዘብ መጠን ለማሳካት ለረጅም ሰዓታት ሲሠራ ነው።

“በሕይወቴ እንደዚህ አስከፊ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። አዎ፤ ይደበድቡኝ ነበር። ግን እመነኝ ከመደብደብ በብዙ የከፋ ነገር ሌሎች ሰዎች ላይ ሲፈጸም አይቻለሁ” ሲል ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ተናግሯል።

ሚኪ፤ በታይላንድ እና ምያንማር ድንበር ላይ ባሉት የማጭበርበሪያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ከሚገመቱት 100 ሺህ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ የካምፖች ብዙውን ጊዜ የሚመሩት፤ በዚህ የምያንማር አካባቢ ያለውን ሕግ አልባነትን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው በሚንቀሳቀሱ ቻይናውያን የማጭበርበር እና የቁማር ቡድኖች ነው።

ከዚህ ቀደም ከካምፖቹ ያመለጡ ሰዎችን ውስጥ የሚፈጸሙትን አስከፊ ድርጊቶች ሲናገሩ ቢቆዩም፤ አሁንም ድረስ ጥሩ ገንዘብ እንደሚያገኙ የተነገራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ማግኘት ችግር ከሆነባቸው ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ ምያንማር ይመጣሉ።

አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች የሚመጡባት ቻይና፤ ከምያንማር ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ የሚገኙ እንደዚህ ዓይነት ካምፖችን ዘግታለች። ነገር ግን እስከዚህ ዓመት ድረስ ቤይጂንግም ሆነች ባንኮክ በታይላንድ እና ምያንማር ድንበር ላይ በሚገኘው እንቅስቃሴ ላይ ብዙም እርምጃ አልወሰዱም።

በዚህ አካባቢ በሚገኙ የማጭበርበሪያ ካምፖች ውስጥ የነበሩ የግዳጅ ሠራተኞችን ማስለቀቅ የተጀመረው ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት ታይላንድ የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎ ነው። ከቻይና እና በሀገሪቱ ከሚገኙ የተወሰኑ ፖለቲከኞች ጫና የተደረገባት ታይላንድ፤ ወደ ካምፖቹ ይደርሱ የነበሩ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የቴሌኮሚዩኒኬሽን መስመሮችን አቋርጣለች።

የካምፖቹ አለቃዎች የሚያገኙት የባንክ አገልግሎት ላይ ገደብ የጣለች ሲሆን ለእንቅስቃሴ ከለላ ሲሰጡ በነበሩ የተወሰኑ የታጣቂ ቡድን አለቃዎች ላይም የእስር ትዕዛዝ አውጥታለች። እነዚህ እርምጃዎች የካምፖቹን እንቅስቃሴ ጎድተዋል።

ከካምፖቹ በበለጠ የእነዚህ እርምጃዎች ክንድ የበረታው በድንበር አካባቢ የሚገኙት የካረን ግዛት ነዋሪዎች ላይ ነው። ይህም አካባቢውን የሚቆጣጠረው ታጣቂ ቡድን አዛዦች ላይ ጫና እንዲበረታ እና በማጭበርበሪያ ካምፖቹ ውስጥ የሚፈጸመውን ድርጊት በፈቃዳቸው ለማስቆም እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል።

ከካምፖቹ ለማምለጥ ሚሞክሩ ሰዎችን መርዳት እንዲሁም ከአንዳንድ ካምፖችም የግዳጅ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ ማድረግ ጀምዋል።

ሚኪ የነበረበት ካምፕ ይጠበቅ የነበረው ከካረን ብሔር ታጣቂዎች አንዱ በሆነው “ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ” በተባለው ቡድን ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በግዛቱ ለተስፋፉት ማጭበርበሪያ ካምፖች ከለላ ይሰጥ የነበረው ይህ ታጣቂ ቡድን ነው።

ምያንማር እና ታይላንድን የሚከፍለው ሞይ ወንዝ አካባቢ ላይ ታጣቂዎቹ በብዛት ይታያሉ። በጦርነት በሚታመሰው ይህ የካረን ግዛት አካባቢ፤ በታይላንድ ከሚያጎራብተው ገጠራማ አካባቢ ጋር ሲታይ አዳዲስ ህንጻዎችን የተገነቡበት ነው።

ከምያንማር የሚለቀቁ የግዳጅ ሠራተኞችን የሚዘዋወሩባት ታይላንድ፤ ተጎጂዎቹን የመለየት እና ወደ ሀገራቸው የመመለስ እንቅስቃሴን በተቻለት ፍጥነት እያከናወነች መሆኑን ትናገራለች።

ከሦስት ሳምንት ገደማ በፊት 260 ከካምፖቹ የወጡ የግዳጅ ሠራተኞች ሞይ ወንዝን ተሻግረው ወደ ታይላንድ ገብተዋል። ከእነዚህ የግዳጅ ሠራተኞች ውስጥ 138 ያህሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ታይላንድ የነበሩ 621 ተጎጂዎች በቻርተርድ አውሮፕላን ወ ደሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ ግን ነጻ የወጡ የግዳጅ ሠራተኞችን የተመለከቱ ሌሎች እንቅስቃሴዎች የቆሙ ይመስላል።

ነጻ ወጡ ሰዎች በቶሎ እንዳይመለሱ እንቅፋት የሆነው አንዱ ጉዳይ ተጎጂዎቹ ከብዙ የተለያዩ ሀገራት መምጣታቸው ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ሀገራትም ዜጎቻቸውን ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት አነስተኛ ነው።

በየካቲት ወር መጀመሪያ ከተለቀቁት 261 ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላዩ የመጡባት ኢትዮጵያ፤ በታይላንድ ኢምባሲ የላትም። የኢትዮጵያ መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ የሚሸፈነው በሕንድ ኒው ዴልሂ በሚገኘው ኢምባሲ በኩል ሲሆን፣ ኤምባሲውን ማግኘትም አዳጋች እንደሆነ ነጻ የወጡ ሰዎችን ወደ ሀገራቸው ለመላክ የሚሠሩ ድርጅቶች ይናገራሉ።

በሕንድ የሚገኘው ኤምባሲ በበኩሉ 138ቱን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ፤ በምያንማር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማስለቀቅ መንግሥት ካደራጀው ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተወጣጣ “ብሔራዊ ኮሚቴ” እና ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር እንደሚሠራ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

ቢቢሲ የደረሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በግዳጅ ሠራተኝነት የቆዩ ዜጎቻቸውን ወደ ሀገራቸው የሚመልሱት የበረራ ወጪው በሌላ አካል ከተከፈለ ነው። ፓስፖርታቸው ጭምር በአሠሪዎቻቸው ተይዞባቸው የሚቆዩት ብዙዎቹ ተጎጂዎች፤ ነጻ ሲወጡ ምንም ገንዘብ አይኖራቸውም።

ታይላንድ፤ ነጻ የሚወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የምትቀበል ከሆነ እስከ መጨረሻው እዚያው ድጋፍ እየተቀበሉ ሊቆዩ ይችላሉ የሚል ስጋት አላት።

በተጨማሪም ከምያንማር ከሚመጡት ሰዎች መካከል የትኞቹ በትክክል የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ፣ የትኛዎቹ ደግሞ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳተፉ እንደሆነ መለየት ትፈልጋለች። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ብዙ ሰዎችን ለመለየት የሚያስችል አቅም የላትም።

በማጭበርበሪያ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ተጎጂዎችን የሚረዳን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚመራው አውስትራሊያዊው ጁዳህ ታና፤ ነጻ የወጡ የግዳጅ ሠራተኞችን ከታይላንድ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ “የቆመ እንደሚመስል” ይናገራል።

“[መጠለያዎቹ ውስጥ ያለውን] የንህጽና እና የመጸዳጃ ቤት እጥረት በተመለከተ የሚረብሹ መረጃዎችን እየሰማን ነው። ከ260 ዎቹ ውስጥ አብዛኛዎቹ የ’ቲቢ’ ምርመራ ተደርጎላቸው፤ በሽታው ተገኝቶባቸዋል። ውስጥ ካሉ ሰዎች እንደምንሰማው ሰዎቹ ደም እያሳላቸው ነው። ከማጭበርበሪያ ካምፖቹ ነጻ በመውጣታቸው በጣም ደስ ብሏቸዋል። የእኛ ስጋት ግን በሚፈለገው ፍጥነት እየተንቀሳቀስን አይደለም የሚል ነው” ይላል።

ታይላንድ፤ ኤምባሲያቸው ጥረት ሲያደርግላቸው የነበሩ እና የአውሮፕላን ትኬት የተቆረጠላቸውን 94 ኢንዶኔዥያውያንን ወደ ሀገራቸው ልትልክ ዝግጅት እያደረገች ነው።

አሁንም ቢሆን ግን ቀጣይ ዕጣ ፋንታቸው ምን እንደሆነ ያላወቁ ሰባት ሺህ ተጎጂዎች ምያንማር ውስጥ ይገኛሉ።

በምያንማር ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ሚኪ በቶሎ ወደ ታይላንድ ካልተሻገሩ አሁን የያዟቸው ታጣቂዎች ወደ ማጭበርበሪያ ካምፖቹ ሊመልሷቸው እንደሚችሉ ይሰጋል። ወደ ካምፑ የሚመለሱ ከሆነ ለማምለጥ በመሞከራቸው ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሚኪ፤ ረቡዕ ዕለት ምሽት ያለበት ድንገተኛ የመረበሽ ስሜት እና ህመም (panic attack) እንዲሁም የትንፋሽ መቆራረጡ ሲብስበት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር።

በስጋት እና በተስፋ መካከል የሚዋልለው ሚኪ፤ “የምፈልገው ወደ ቤቴ መሄድ ብቻ ነው። ወደ ሀገሬ እንዲመልሱኝ ብቻ ነው የምጠይቀው” ይላል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop