የሶማሊ ክልል ሴት ታዳሚዎች ስፖርታዊ ውድድር ለመመልከት ስታድየም እንዳይገቡ የከለከለው ለምንድነው? Leave a comment

የሶማሊ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ በየዓመቱ የሚካሄደውን ደማቁን የእግር ኳስ ውድድር እያስተናገደች ትገኛለች።

ይህን ክልላዊ የስፖርት ውድድር ለመታደም በርካቶች ከክልሉ የተለያዩ ክፍሎች ወደ ጅግጅጋ ስታድየም ያቀናሉ።

የውድድሩ አዘጋጅ የሶማሊ ክልል የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሲሆን በርካቶች ለስፖርት ዕድገት ይበጃል የተባለውን ይህን ስፖርታዊ ውድድር አስታከው ማሕበራዊ ቅንጅታቸውን ለማጠናከር ይመጣሉ።

ስፖርታዊው ውድድር ደጋፊዎች በጩኸት እና ጭብጨባ የሚያፈኩት፤ በግጥምና ዘፈን የሚበሻሸቁበት፤ ሴቶች ደግሞ ከበሮ እየደለቁ የሚሳተፉበት ነው።

ውድድሩ ለወትሮው በጣም የደመቀና የጅግጅጋ ስታድየም ጠጠር መጣያ እስኪያጣ ጢም ብሎ የሚታይበት ሲሆን የዘንድሮው ውድድር ግን አወዛጋቢ ውሳኔ ተጭኖታል።

የክልሉ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ በዘንድሮው ውድድር ሴት ታዳሚዎች እንዳይሳተፉ ማገዱ ውዝግብ አስነስቷል። ቢሮው ለዚህ ምክንያቱ ሴት ደጋፊዎች የሚወርውሯቸው ቃላት ግጭት የሚቀሰቀሱ ናቸው የሚል ነው።

ቢሮው እንደሚለው ሴት የውድድሩ ታዳሚዎች የሚያሳዩት ባሕርይ “ከስፖርታዊ ጨዋነት ወጣ” ያለ እና የጨዋታውን ሕግ የማያከብር ነው።

ጉዳዩን በተመለከተ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰጡ አስተያቶች ውሳኔውን በመተቸት፣ አጠቃላይ ሴቶችን ለመቅጣት መወሰን ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

‘ከስፓርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ተግባር’ ተፈጽሟል ከተባለ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች (ሴቶችም ይሁኑ ወንዶች) ላይ ያነጣጠረ እርምጃ መውሰድ ሲቻል፣ አንድ ፆታን በጅምላ መቅጣት ተገቢ እንዳልሆነ በማንሳት የሰላ ትችት የሰነዘሩ አስተያየት ሰጪዎችም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

በጅምላ ሴቶችን መቅጣት ያስነሳውን ትችትና ጥያቄ በተመለከተ የሶማሊ ክልላዊ መንግሥት የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያለው ነገር የለም።

የሶማሊ ክልላዊ መንግሥት የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሞሐመድ ማሕዲ አዳን በዘንድሮው መክፈቻ ንግግር አድርገዋል። ሴት ደጋፊዎች አንዳንድ ጊዜ የሚያሳዩት ባሕርይ “የጎሳ ግጭት” የሚቀሰቅስ ነው ብለዋል።

ቢሮው እንዳለው ሴት የውድድሩ ታዳሚዎች ስታድየም ገብተው እንዳይመለከቱ የተከለከሉ ሲሆን ነገር ግን ቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት መታደም ይችላሉ።

የስፖርት ዓላማ ማሕበረሰብን ማጣመር እንጂ መከፋፈል አይደለም ያለው ቢሮው በዚህ ምክንያት ዕግዱን መጣሉን አስታውቋል።

ኃላፊው ይህንን ውሳኔ ለመወሰን የደረሱበትን ምክንያት ሲያስረዱ “በርካታ ማስረጃዎች አሉን። ሴት ታዳሚዎች ስታድየም ገብተው የሚያሳዩ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ቪድዮዎች አሉ። ጥላቻ የሚነዙና ከፋፋይ ቃላትን ሲሰነዝሩ ታይተዋል” ይላሉ።

ሞሐመድ አክለው “ፀብ አጫሪ ቃላት የሚሰነዝሩት ሴቶች ብቻ ነው። ለምሳሌ ትላንት [ረቡዕ] በነበረው ውድድር ወንዶች ብቻ ነበር የታደሙት። ስታደየሙ የተረጋጋና ብጥብጥ ያልነበረበት ነበር” ብለዋል።

የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮው ይህ ውሳኔ ጊዜያዊ መሆኑን ገልጦ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ሴቶች ውድድሩን ከቤታቸው እንዲታደሙ አሳስቧል።

“ሴት ታዳሚዎች ወደ ስታድየም እንዳይገቡ ያሳለፍነው ውሳኔ ጊዜያዊ ሲሆን ዘላቂ መፍትሔ እስኪገኝ የሚቆይ ነው። በሰላማዊ መንገድ ውድድሩን መታደም የሚችሉ ከሆነ ድጋሚ እንዲታደሙ ይደረጋል፤ ምክንያቱም [ሴቶች] የማሕበረሰቡ አካል ናቸው” ብለዋል ኃላፊው።

ሞሐመድ እንደሚሉት “በተቀረው ዓለምም ግጭት የሚቀሰቅሱ ታዳሚዎች ከሜዳ ይታገዳሉ አሊያም ቅጣት ይጣልባቸዋል።”

በተያያዘ ከሀገረ ሶማሊያ የመጡ ስፖርተኞች በውድድሩ ይሳተፋሉ የሚባለው እውነት ነው? ተብለው የተጠየቁት የቢሮው ኃላፊው “ትክክል ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊትም ይህ ነበር። ውድድሩ ከባድ እና ጥሩ ብቃት የሚጠይቅ ስለሆነ ክለቦች ከሌሎች ቦታዎች ተጫዋቾች ማስመጣት እንዲችሉ አድርገናል።”

በ2002 ዓ.ም. የተጀመረው የሶማሊ ክልል ስፖርታዊ ውድድር 11 የዞን አስተዳደሮች የሚሳተፉበት ሲሆን በክልሉ መዲና ጅግጅጋ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው።

ውድድሩን ስታድም ገብተው ከሚመለከቱ ደጋፊዎች በተጨማዊ በቴሌቪዥን መስኮት እና በማሕበራዊ ሚደያዎች አማካይነት ለታዳሚዎች ይደርሳል።

ይህን ዓመታዊ ውድድር በቁጥር የበረከቱ ሴት ደጋፊዎች ስታድየም ገብተው በከበሮ፣ ጭፈራና በዘፈን ታጅበው ይመለከቱታል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop

የሚፈልጉትን ይዘዙን

Order what you want