የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የመሠረቱት ማዕከል ይፋ አደረገ።
የቀድሞው የለውዝ ገበሬ ከየትኛውም የአሜሪካ ፕሬዚደንት በላይ የኖሩ ሲሆን ባለፈው ጥቅምት 100ኛ የልደት በዓላቸውን አክብረው ነበር።
በዓለም ዙሪያ ለዲሞክራሲ እና ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገተው የካርተር ማዕከል እሑድ ከሰዓት በኋላ በጆርጂያ ፕላይንስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል።
የዴሞክራት ፓርቲው ካርተር እአአ ከ1977 እስከ 1981 አሜሪካ በኢኮኖሚያዊ እና በዲፕሎማሲያዊ ቀውሶች በተከበበችበት ወቅት በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል።
ከዋይት ሃውስ ሲወጡ ዝቅተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ቢኖርም ባከናወኑት የሰብዓዊነት ሥራ የኖቤል የሠላም ሽልማትን በማሸነፍ ስማቸውን ተክለዋል።
“አባቴ ለእኔ ብቻ ሳይሆን በሠላም፣ በሰብዓዊ መብቶች እና ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ ፍቅር ለሚያምኑ ሁሉ ጀግና ነበር” ሲሉ ልጃቸው ቺፕ ካርተር ተናግረዋል።
ካርተር ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት የጆርጂያ ግዛት ገዥ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል ሌተናንት እና ገበሬ ነበሩ። አራት ልጆች፣ 11 የልጅ ልጆች እና 14 የልጅ ልጅ ልጆች አይተዋል።
ለ77 ዓመታት በትዳር አብረዋቸው የኖሩት ባለቤታቸው ሮዛሊን ካርተር እአአ ህዳር 2023 ህይወታቸው አልፏል።
እአአ ከ2018 ከጆርጅ ኤችደብሊው ቡሽ ሞት በኋላ በህይወት ያሉ በዕድሜ ትልቁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ።