“የተረሳው” ዕፅ፡ ከኢትዮጵያ የሚሄደው፤ በዩናይትድ ኪንግደም የታገደው ጫት እውን ከገበያ ጠፍቷል? Leave a comment

ዩናይትድ ኪንግደም በጥቂት ፓውንዶች መንገድ ላይ ይሸጥ የነበረው ጫት ጥቅም ላይ እንዳይውል ዕግድ ከጣለች አስር ዓመታት አለፉ።

በእንግሊዝኛው ‘ኻት’ ተብሎ የሚታወቀው ቅጠል ሲታኝክ እንደ አምፊታሚን ዓይነት አነቃቂ ስሜት ይሰጣል።

ምንም እንኳ ዩኬ ይህ ቅጠል ዕፅ ስለሆነ ገበያ ላይ እንዳይውል ብትልም ባለሙያዎች ግን አሁንም እየተሸጠ ነው፤ እንደውም ዋጋው 10 እጥፍ ጨምሯል ይላሉ።

እገዳው ምን ያክል ለውጥ እንዳመጣ ለማወቅ የሚረዳ ጠብሰቅ ያለ መረጃ የለም።ዶ/ር ኒል ኬሪዬር በኦክስፈርድ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ-ምረቃ ድግሪያቸውን ሲማሩ ጥናታቸውን ጫት ላይ ነው የሠሩት።

ጫት በባለሥልጣናት ዘንድ “የተረሳው” ዕፅ “ዕገዳው ምን ያክል ውጤታማ ነው የሚለው ጥናት ሊደረግበት ይገባል” ይላሉ።

ስሙ ለዚህ ፅሑፍ ሲባል የተቀየረው የ25 ዓመቱ ሞሐመድ በአውሮፓውያኑ 2028 ጫት ከታገደ ከአራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሞከረው ለቢቢሲ ይናገራል።

“እንደው በዩናይትድ ኪንግደም በጣም በብዛት ተዘጋጅቶ ለገበያ ይቀርባል” ይላል።

“በአነስተኛ አብረቅራቂ ከረጢት ታሽጎ ይሸጣል። ከረጢቱ የታሸገ ሲሆን ከቅጠላ ቅጠል የተሠራ የፊት ማሳመሪያ የሚል ፅሑፍ ተለጥፎበታል። ነገር ግን ስትከፍተው ጫት ነው።”

እሱ የደረቀ ጫት ነው የሚጠቀመው። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት የደረቀ ጫት መጠቀም እየተለመደ መጥቷል።

ዶ/ር ኒል አሁን በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር ናቸው። በ2000 እና ከ2010 በኋላ ባሉት ዓመታት ‘ፍሬሽ’ የሚባል ጫት 250 ግራም 3 ፓውንድ ነበር የሚሸጠው ይላሉ።

ማፍሪስሽስ በሚባሉ የጫት ካፌዎች [መቃሚያዎች] ውስጥ ነበር የሚዘወተሩት። አብኛዎቹ ተጠቃሚዎች ሶማሊዎች፣ የመኖች እና ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ሰብሰብ ብለው ነው የሚጠቀሙት።

ምሑሩ በመንግሥት በሚደገፍ አንድ መፅሔት ላይ ጫት ማኅበራዊ ተስስሮሽ ላይ ያለውን ጉዳት የተመለከተ ፅሑፍ አሳትመዋል።

“እኛ አንትሮፖሎጂስቶች ስለዕፅ ስናወራ ዕፁ ምን ዓይነት ጉዳት ያመጣል ብቻ ሳይሆን በሰፊው ባሕላዊ ትርጉሙ ምን ይመስላል እንደ ትስስር ላይ ምን ተፅዕኖ ያመጣል የሚለውንም እንመረምራለን” ይላሉ።

ዶ/ር ኒል እንደሚሉት ጫት ላይ የተጣለው ክልከላ ሌሎች አዝናኝ የሚባሉ ዕፆች ክልከላ ቢደረግባቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ለማየት መልካም ዕድል ይፈጥር ነበር፤ ነገር ግን “አልተጠቀምንበትም” ባይ ናቸው።

“ለምሳሌ ዩኬ ውስጥ ጫትን የሚጠቀሙ ማኅበረሰቦች ከዕፁ ጋር የተያያዘ ምን ጉዳዮች ነበሩባቸው የሚለውን ማየት እንችል ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ዕፁ ለማኅበራዊ ችግሮች ሰበብ ተደርጎ ሲወሰድ አያለሁ።”

በ2 ሺህዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ጫት ለቤተሰብ እና ለማኅበራዊ ትስስር እክል እንደሆነ ሰዎች ሲናገሩ እንደሰሙ ዶ/ር ኒል ይናገራሉ።

“ለምሳሌ ጫት የሚጠቀሙ ‘ወንዶች መልካም አባት እየሆኑ አይደለም’ የሚሉ ሐሳቦች እሰማ ነበር። ሌላው እሰማው የነበረው ጫት የሚቅሙ ሰዎች ሥራ መሥራት አይሹም የሚል ነበር።”

ነገር ግን ይላሉ ምሑሩ “አንዳንድ ጊዜ ይህ የችግሩን ያልተሟላ ምስል የሚያሳይ” ነው።

“በማኅበረሰባችን ውስጥ ዕፆችን ትልቅ ቦታ ሰጥተናቸው ለችግራችን መንስዔ እንደሆኑ እናስባለን። ነገር ግን ሁኔታው እና ከምናስበው በላይ ውስብስብ ነው።”

ባለፈው ዓመት የዩናይትድ ኪንግደም የድንበር ጥበቃ 2 ሺህ 760 መደብ ሲ የተባሉ ዕፆች ወደ ሀገር ቤት ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የድንበር ጉዳዮችን የሚከታተለው ሆም ኦፊስ ቃል አቀባይ “የድንበር ጥበቃ እና ፖሊስ በጋራ ሕገ-ወጥ የሆኑ ዕፆች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እና መንገዶች ላይ እንዳይሸጡ እየሠሩ ነው” ብለዋል።

“እስከዛሬ ዓይተን በማናውቀው ደረጃ ድንበር ላይ በርካታ መጠን ያላቸው ዕፆች ተይዘዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና መረጃ በመጠቀም ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እያደረግን እንገኛለን።”

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2014 ጫትን ያገደችው ዩናይትድ ኪንግደም ዕፁን ከከለከሉ የመጨረሻዎቹ የአውሮፓ ሀገራት መካከል ናት።

ከእገዳው በፊት በየዓመቱ 2500 ቶን አሊያም 2 ሚሊዮን 500 ሺህ ኪሎ ግራም ጫት ወደ ዩኬ ይገባ እንደነበር ኤሲኤምዲ የተባለው ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

አብዛኛው ጫት የሚሸጠው ከምስራቅ አፍሪካ መጥተው ብሪታኒያ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ሲሆን በተለይ ኢትዮጵያዊያን እና ሶማሊያዊያን ቀንደኛ ተጠቃሚ ነበሩ።

የዩኬ ድንበር ጥበቃ ጫትን “ሌሎች ዕፆች” የሚል ቋት ውስጥ ነው የሚያስገባው።

ዶ/ር ኒል ጫት በተከለከለ ጊዜ ሰዎች ይሆናል ብለው የፈሩት ነገር እየሆነ ነው ይላሉ።

“ጫት አሁን በተለይ ደርቆ እየመጣ ነው። በአብዛኛው የሚመጣው ከኢትዮጵያ ነው። ተፈላጊነቱም እየጨረ ይገኛል። ምንም እንኳ ዕፁ ቢከለከልም አሁን መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ቅርፁን ቀይሮ ቢሆንም ይጠቀሙታል።”

የደረቀ ጫት የማነቃቃት ኃይል እንደ ‘ፍሬሽ’ ጫት አይደለም። “ጣዕሙ እና ይዘቱም ብዙም አርኪ እንዳልሆነ” ይነገራል።

ዶ/ር ኒል ደረቀም አልደረቀም ጫት መጠቀም የሚችሉ ሰዎች “አሁንም እየተጠቀሙት ነው” ይላሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ  ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop