የነዳጅ መኪኖችን አስቀርታ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመጠቀም ቀዳሚ የሆነችው ኖርዌይ……. Leave a comment

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ኖርዌይ በዓለማችን ቁንጮ ስፍራ ላይ ተቀምጣለች።

ባለፈው ዓመት በኖርዌይ ካሉ አስር መኪኖች መካከል ዘጠኙ የኤሌክትሪክ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሌሎች አገራት ከኖርዌይ ምን መማር ይችላሉ?

በኦስሎ መቀመጫውን ያደረገው የመኪና አምራቹ እና አስመጪው ሃራልድ ኤ ሞለር ባለፉት 75 ዓመታት ቮልስዋገን መኪኖችን ያስገባ ነበር። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ግን በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን ተሰናብቻለሁ ብሏል።

በአሁኑ ወቅት በሽያጭ ላይ ያሉት ተሽከርካሪዎቹ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ናቸው።

“ወደዚህ የሚመጣ ደንበኛችን በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን እንዲገዙ መምከር ስህተት ነው ብለን እናስባለን። ምክንያቱም መጪው ጊዜ የኤሌክትሪክ መኪኖች ናቸው” ሲሉ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኡልፍ ቶሪ ሄክኒቢ ይናገራሉ።

በኖርዌይ መዲና ኦስሎ ጎዳናዎች በባትሪ የሚንቀሳቀሱ (የኤሌክትሪክ መኪኖች) በጣም የተለመዱ ናቸው። አካባቢያችሁን ስትቃኙ በርካታ መኪኖች የሰሌዳ ቁጥራቸው ላይ ‘ኢ’ (ኤሌክትሪክ) መለያ እንደለጠፉ ማስተዋል ይቻላል።

5.5 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የኖርዲክ አገሯ ኖርዌይ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ከየትኛውም አገር በበለጠ በፍጥነት በመቀበል ቀዳሚ ናት።

በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የነዳጅ መኪናዎችን ሽያጭ በማቆም የመጀመሪያዋ ለመሆን በዝግጅት ላይ ናት። ባለፈው ዓመት በኖርዌይ ያሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ቤንዚን ከሚጠቀሙት በልጧል።

በአገሪቷ በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሠሩ መኪኖች ተደምረው አንድ ሦስተኛውን የሚይዙት የኤሌክትሪክ መኪኖች ናቸው።

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ውስጥ ከተሸጡት አዳዲስ መኪኖች 88.9 በመቶ የሚሆኑት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ናቸው። በአውሮፓውያኑ 2023 የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር 82.4 እንደነበር ከኖርዌይ የመንገድ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሠሩ መኪኖች ሽያጭ ሲያሽቆለቁል በተቃራኒው በአንዳንድ ወራት ላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ሽያጭ እስከ 98 በመቶ ከፍ ብሏል።

በአንጻሩ በዩናይትድ ኪንግደም የኤሌክትሪክ መኪኖች ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 20 በመቶ መሆኑን የመኪና ምዝገባ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአውሮፓውያኑ 2023 የኤሌክትሪክ መኪኖች 16.5 በመቶ ነበሩ። በአሜሪካ ያለውን ደግሞ መረጃ ስናይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ቁጥር ባለፈው ዓመት 8 በመቶ የነበር ሲሆን፣ ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት ደግሞ 7.6 በመቶውን ቁጥር ይይዙ ነበር።

መንገዶቿን የኤሌክትሪክ መኪኖች ብቻ ለማድረግ ጫፍ ላይ የደረሰችው ኖርዌይ ይህንን የኤሌክትሪክ አብዮት ለማምጣት ሦስት አስርት ዓመታትን አስቆጥራለች።

የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለአገልግሎት ማዋል “የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ነው” ሲሉ የኖርዌይ የኤሌክትሪክ መኪኖች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ክርስቲና ቡ ይናገራሉ።

“በቤንዚን እና በናፍጣ የሚሠሩ መኪኖች በዓመታት ውስጥ የተጣለባቸው ግብር በጣም ያስወደዳቸው ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መኪኖች ግን ከቀረጥ ነጻ ተደርገዋል” ይላሉ።

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ድጋፍ የተጀመረው ‘በዲ’ እና ‘ቲንክ ሲቲ’ የተሰኙትን ሁለት ቀደምት የኖርዌይ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቾችን ለመደገፍ ነበር።

እነዚህ ኩባንያዎች ከንግድ ሥራው ቢመጡም ለአካባቢ ደኅንነት ቅድሚያ ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚሰጠው ማበረታቻ ቀጠለ።

“የእኛ የሁልጊዜ ግባችን ጠቃሚ የሆነውን ዜሮ ልቀትን መምረጥ ነው” ሲሉ የኖርዌይ ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትር ሴሲሊ ክኒቤ ክሮግሉንድ።

ምንም እንኳን ኖርዌይ ዋነኛ ነዳጅ እና ጋዝ አምራች ብትሆንም በ2025 የሚሸጡ አዳዲስ መኪኖች በሙሉ “ዜሮ ልቀት” ያላቸው እንዲሆን ጥረት እያደረገች ነው።

አገሪቷ ይህንን የካርበን ልቀት መቀነስ እና በዘንድሮው ዓመት ዜሮ ለማድረግ ዕቅዱን የወጠነችው በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር።

“ወደ ኢላማችን እየተጠጋን ነው በቅርቡም ግባችንን እናሳካለን ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ሚኒስትሯ ይናገራሉ።

ለኖርዌይ ስኬት ዋነኛው ቁልፍ ጉዳይ የረጅም ጊዜ እና ውጤታቸው ሊተነበዩ የሚችሉ ፖሊሲዎች መሆናቸውን ሚኒስትሯ ይገልጻሉ።

የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ከመከልከል ይልቅ የሸማቾች ምርጫዎች ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ተሠርተዋል ይላሉ።

በነዳጅ በሚሠሩ መኪኖች ላይ ከፍተኛ ግብር በመቆለል እና የምዝገባ ክፍያዎችን ከመጨመር ባለፈ ዝቅተኛ ልቀት ላላቸው መኪኖች የተጨማሪ እሴት ግብር እና ሌሎች ግብሮች እንዲሰረዝላቸው ተደርጓል።

በተጨማሪም ነጻ የመኪና ማቆሚያ፣ በአንዳንድ ጎዳናዎች ያሉ ክፍያዎችን ማስቀረት እና የአውቶብስ መስመሮች መዳረሻዎችን ክፍት ያደረጉ ጥቅማጥቅሞችን ለኤሌክትሪክ መኪኖች አሽከርካሪዎች እንዲኖራቸው መንግሥት አድርጓል።

በአንጻሩ የአውሮፓ ኅብረት አዳዲስ የነዳጅ መኪኖችን ሽያጭ በአውሮፓውያኑ 2035 እንዲሁም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2030 ለመከልከል ዕቅድ አስቀምጠዋል።

በነዳጅ እና በናፍጣ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ በኖርዌይ አሁንም ፍቃድ አላቸው። ነገር ግን እየገዙ ያሉት ጥቂቶች ናቸው።

የመጀመሪያ የኤሌክትሪክ መኪናውን ከ15 ወራት በፊት የገዛው ስቴል ፋይን ከምጣኔ ሀብት አንጻር ትርጉም እንዳለው አይቷል።

“በኖርዌይ ለኤሌክትሪክ መኪኖች ግብር አለመክፈልን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ከገንዘብ አንጻር ጉልህ ጥቅም ያለው እንደሆነ ማሳያ ነው” ይላል የኤሌክትሪክ መኪናውን ቻርጅ እያደደረገ የነበረው ስቴል።

ሌላኛዋ ሜሬት ኤግስቦ በአውሮፓውያኑ 2014 ቴስላ የኤሌክትሪክ መኪናን በመግዛት ቀዳሚ ከሆኑት አንዷ ናት።

“በእውነቱ አካባቢን የማይበክል መኪና እፈልግ ነበር። አሁን መኪናዬን ስነዳ ለህሊናዬ ቀለል ብሎኛል” ስትል ታስረዳለች።

በኖርዌይ ያሉ የነዳጅ ማደያዎች በፍጥነት ቻርጅ በሚያደርጉ አገልግሎት ሰጪዎች ተተክተዋል። በመላው ኖርዌይ በአሁኑ ወቅት ከ27 ሺህ በላይ የሕዝብ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ስፍራዎች አሉ።

በሕዝብ ብዛት 12 ጊዜ በምትበልጣት ዩናይትድ ኪንግደም ያሉት 73 ሺህ 699 ቻርጅ ማድረጊያዎች ናቸው።

ይህም ማለት በኖርዌይ 100 ሺህ ነዋሪዎች 447 የሕዝብ ቻርጅ ማድረጊያ ስፍራዎች ሲኖራቸው፣ በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በዚሁ የህዝብ ቁጥር 89 እንደሆነ በቅርቡ የወጣ ዘገባ አመልክቷል።

በአገሪቱ ቴስላ፣ ቮልስዋገን እና ቶዮታ ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ የኤሌክትሪክ መኪኖች ምርቶቻቸውን የሸጡ ድርጅቶች ሆነዋል። በተጨማሪ የቻይናዎቹ ኤምጂ፣ ቢዋይዲ፣ ፖለተስታር እና ኤክስፔንግ 10 በመቶ የሚሆነውን የገበያ ድርሻ እንደሚይዙ ከኖርዌይ የመንገድ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ኖርዌይ እንደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ከቻይና በሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ ታሪፍ አልጣለችም።

እንዲህ ዓይነት ስኬቶች የተገኙት የኖርዌይ ሕዝብ በሌሎች አካባቢዎች ካሉ ሰዎች በበለጠ ለአካባቢ ጥበቃ ተቆርቁረው እንዳልሆነ የሚናገሩት ሚኒስትሯ “ከጠንካራ የመንግሥት ፖሊሲዎች ጋር የተያያዘ ነው፤ እናም ሰዎች ቀስ በቀስ የኤሌክትሪክ ተሽካርካሪዎችን መንዳት እንደሚቻል ተረዱ” ይላሉ።

ኖርዌይ በዓለማችን ከበለጸጉት አገራት አንዷ ስትሆን ወደ ውጭ ከምትልከው ነዳጅ እና ጋዝ 1.7 ትሪሊየን የመንግሥት ኢንቨስትመንት ፈንድ አላት። ይህም ማለት ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶችን በቀላሉ መገንባት እንዲሁም ከነዳጅ እና ከናፍጣ መኪኖች ሽያጭ የሚገኘው የግብር ቢቀር የሚቋቋም ምጣኔ ሀብት አላት።

“በአሁኑ ወቅት አንድ ሦስተኛውን የሚይዙት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ናቸው፤ ይህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከ50 በመቶ ያልፋል” ሲሉ የኖርዌይ የትራንስፖርት ጥናት እና ምርምር ማእዕል ባልደረባ የሆኑት ኪጀል ቨርነር ዮሃንሰን ይናገራሉ።

“ጥቂት አዳዲስ ቤንዚን ወይም ሁለቱንም የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በገበያ ላይ እንደሚቆዩ መንግሥት የሚቀበለው ይመስለኛል። ነገር ግን በዚህ ዘመን የነዳጅ መኪና መግዛት የሚፈልግ ሰው አላውቅም” ብለዋል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop