ናይጄሪያዊያን ብዙ ምክክር ሳይደረግበት ብሔራዊ መዝሙራችን ተቀይሯል በማለት ቁጣቸውን እየገለጡ ይገኛሉ።
ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ ረቡዕ ዕለት በአውሮፓውያኑ 1978 ወታደራዊው መንግሥት አግዶት ወደነበረው የቀድሞ መዝሙር እንዲቀየር የሚል አዋጅ ፈርመዋል።
እንደ አዲስ የተሠራው ብሔራዊ መዝሙር “ናይጄሪያ እናወድስሻለን” ብሎ የሚጀምር ሲሆን በ1959 ዓ.ም. በሊሊያን ዦን ዊሊያምስ ተፅፎ በፍራንሲስ በርዳ የተቀናበረ ነው።
ሥልጣን የያዙበትን አንደኛ ዓመት እያከበሩ ያሉት ፕሬዝደንት ቲኑቡ ብሔራዊ መዝሙሩ የናይጄሪያን ሕብረ-ብሔራዊነት የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ነገር ግን በርካቶች ፕሬዝደንቱ ለኑሮ መወደድ መፍትሔ እንደማበጀት መዝሙር ላይ አተኮሩ ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ሐሳባቸውን እየሰጡ ያሉ ናይጄሪያዊያን ሀገራቸው እንደ የፀጥታ ችግር፣ የዋጋ ግሽበት እና የውጭ ምንዛሪ መናር ያሉ ከባድ ችግሮች እንጂ የብሔራዊ መዝሙር ችግር የለባትም ይላሉ።
“ቲኑቡና ጀሌያቸው ያሰጨነቃቸው አዲስ ብሔራዊ መዝሙር ነው። ሕዝባቸውን የሚበላው አጥቶ፤ ሰላም ተጠምቶ፤ ሕይወት ገሀነም ሆኖ ሳለ?
እንዴት ያለ ቀልድ ነው ይሄ! እስቲ እንዴት እንደሚያስፈፅሙት እናያለና” ሲል አንድ ግለሰብ በኤክስ [በቀድሞው ትዊተር] ገፁ ሐሳብ ሰጥቷል።
አንድ ሌላ አስተያየት ሰጪም እንዲሁ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በምን ያክል ፍጥነት አዋጁን እንዳፀደቀው በመገረም ሐሳቡን አጋርቷል።
“በናይጄሪያዊ የተፃፈን የናይጄሪያ ብሔራዊ መዝሙር ቅኝ ገዥዎች ወደፃፉት መዝሙር መቀየር በጣም የረከሰ ውሳኔ ነው፤ ከብሔራዊው ጉባዔ አንድ ተወካይ እንኳ ተነስቶ ይሄ ሊሆን አይገባም አለማለቱ ደግሞ አሳፋሪ ነው” ብሏል።
የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስትር ኦቢ ኤዜዌሲሲሊ አዲሱን ብሔራዊ መዝሙር በፍፁም አልዘምርም ሲሉ ሐሳባቸውን በኤክስ ገፃቸው አጋርተዋል።
“እኔ ኦቢያጌሊ ኦቢፁም አዲሱን ብሔራዊ መዝሙር እንደማልዘምር ሁሉም ይወቅልኝ።”
በርካታ ናይጄሪያዊያን በማሕበራዊ ሚድያ ገፆች አዲሱን መዝሙር በተመለከተ ያላቸውን ሐሳብ እያጋሩ ይገኛሉ።
የቀድሞው የፕሬዝደንት ፅ/ቤት አማካሪ ባሽር አሕመድ በበኩላቸው መዝሙሩ መቀየሩ ሌሎች ጥያቄዎችንም ያጭራል ይላሉ።
“ብሔራዊ መዝሙሩ መቀየሩን ተከትሎ አንዳንዶች ናይጄሪያ የሚለው ስምም ይቀየር እያሉ ነው። ምን ታስባላችሁ? ናይጄሪያ የሚለውን ስም ይዘን እንዝለቅ?”
ነገር ግን አዋጁ እንዲፀድቅ ካደረጉ ሰዎች መካከል ዋናው የሆኑት የፓርላማ ኮሚቲ ሊቀ-መንበር ታሂር ሞጉኑ የናይጄሪያዊያንን ቁጣ ችላ ብለው ውሳኔው “ፈጣን፣ ጊዜው የሚጠይቀው እና አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
“ሀገር ወዳድነት እና ትብብርን የሚያነቃቃ ነው። ባሕላዊ ሽግግርን ያስተዋውቃል። ብሔራዊ መዝሙሩ መቀየሩ ወደታላቅ አንድነት የሚመራን ነው” ይላሉ ታሂር።
አንዳንዶች መዝሙሩ መቀየሩ ለናይጄሪያ አንድነት ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ ( ቢቢሲ ዜና )