በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ የሚገኘው የአህያ ማረጃ ቄራ የአህያ ምርቶች በሙሉ ለቻይና ገበያ የሚቀርብ እንጂ አገር ውስጥ የሚቀር ምርት የለም ሲል ለቢቢሲ ገለጸ። ሮግቻንድ የተባለው የአህያ ማረጃ ቄራ አስተባባሪ የሆኑት ቺቺ አማን ቄራው በቀን ከ50 እስከ100 አህዮችን እያረደ ቆዳቸውን፣ ሥጋቸውን እና አጥንታቸውን ወደ ቻይና እንደሚልክ ተናግረዋል። ድርጅቱ እንደሚለው ከአህዮች እርድ የሚገኙት ሁሉም ምርቶች “አንጥንታቸው እንኳ ሳይቀር ተፈጭቶ ወደ ውጪ ይላካል። እዚህ የሚቀር ምንም የለም” በማለት ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀር ነገር እንደሌለ አመልክቷል። በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የአህያ ሥጋ ምርት ከበሬ ሥጋ ጋር ተመሳስሎ በልኳንዳ ቤቶች ለገበያ እየቀረበ ነው የሚል መረጃ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።
ይሁን እንጂ አቶ ቺቺ ይህ መረጃ “የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ነው” ያሉ ሲሆን፣ እርሳቸው የሚያስተዳድሩት ቄራ በግብርና ሚኒስቴር ክትትል እንደሚደረግበት ጭምር ተናግረዋል። የአህያ ሥጋ፣ ቆዳ እና አጥንት በቻይና ገበያ ተፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ቁጥር አንድ ምክንያቱ የቻይና ባሕላዊ መድኃኒቶችነ ለመሥራት የሚረዳው ኢጂአኦ የተባለ ንጥረ ነገር በአህዮች ውስጥ ስለሚገኝ ነው። ይህ ቄራ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአህያ ቆዳ፣ ሥጋ እና አጥንት ወደ ቻይና ሲልክ መቆየቱን የሚገልጹት አስተባባሪው፤ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ እያስገኘ ነው ይላሉ። ይህ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቄራ ከዚህ ቀደም ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ተቃውሞዎች ተሰምተው ሥራው እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር። በርካቶች በባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች የአህዮች መታረድን በመቃወም ድምጽ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም አህዮች ለገጠሩ ማኅብረሰብ በተለይ ለሴቶች የሚሰጡትን ግልጋሎት እንዲሁም ሰብዓዊነትን ከግምት በማስገባት የአህያ እርድን የሚቃወሙ በርካቶች ናቸው።