የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥን ተከትሎ በምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታየ…… Leave a comment

የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ ከመሠረታዊ ሸቀጦች እስከ ግንባታ ግብዓቶች ድረስ ከፍተኛ የዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱን ተጠቃሚዎች ገለጹ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፣ ቸርቻሪዎች፣ የጅምላ ነጋዴዎች እንዲሁም የግንባታ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች የሸቀጦች እና የግብዓቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ይናገራሉ።

መንግሥት አዲሱን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ እርምጃውን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህ ማሻሻያ የብር ከዶላር አንጻር ያለው የመግዛት አቅም ከዚህ በፊት ከነበረው በመንግሥት ከሚቀመጠው ተመን ውጪ በገበያ ተመን እንዲወሰን ማድረጉ የተለያዩ አስተያየቶች ሲያሰጡበት ቆይቷል።

በርካቶች ውሳኔው የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል የሚል ስጋት ያላቸው ሲሆን፣ መንግሥት ግን የብርን የመግዛት አቅም በገበያው እንዲወሰን ማድረጉ “ፈታኝ” ቢሆንም ለአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ግን “እጅግ አስፈላጊ” ነው ብሏል።

የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ አቅም በገበያ እንዲተመን ከተወሰነ በኋላ የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አንጻር በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከም መጥቷል።

ከሳምንት በፊት በባንኮች 1 ዶላር ዋጋ 57 ብር ገደማ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ብር የመግዛት አቅሙ በ58 በመቶ ገደማ ቀንሶ አንድ ዶላር 91 ብር ገደማ ዋጋ ገበያው ተምኖለታል።

በጥቁር ገበያው ደግሞ 1 ዶላር እስከ 146 ብር እየተሸጠ መሆኑ ለግብይቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ የብር የምንዛሪ ተመን በገበያ አማካይነት እንዲወሰን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በመንግሥት ላይ ግፊት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ መንግሥት ይህንን ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረጉን እና ሌሎች የምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ እርምጃ ወስዷል።

በዚህም የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ድጋፍ የሚውል ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች እንደሚያርቡ ገልጸዋል።

አሁን በገበያው ላይ እየታየ ያለው የብር ዋጋ መዳከም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወደ ገበያው ሲገባ እንደሚረጋጋ እና ጥቁር ገበያውም ከግብይቱ ውጪ እንደሚሆን መንግሥት ገልጿል።

ምን ጨመረ?

ቢቢሲ ዛሬ [አርብ] ሐምሌ 26/2016 ዓ.ም. ያናገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ቢተው “ያልጨመረ ነገር የለም” ይላሉ።

በኪሎ ከ40 እስከ 50 ብር ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት ባለፉት ቀናት ዋጋው ወደ 70 ብር ደርሷል። ቲማቲም ቢያንስ የ10 ብር ጭማሪ ታይቶበት እስከ 50 ብር እየተሸጠ ነው።

1100 ብር ይሸጥ የነበረው 5 ሊትር ዘይት አሁን ላይ 1500 ብር ይጠየቅበታል።

ሌላ ነዋሪ ጤፍ “ትናንት በኩንታል 16 ሺህ 500 ሲባል ነበር” ያሉ ሲሆን፤ አንዲት እናት ደግሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ አንድ ኩንታል ጤፍ 19 ሺህ ብር ሲባል ሰምቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

ከምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በተጨማሪ የግንባታ ቁልፍ ግብዓቶች በሆኑት በብረት እና በሲሚንቶ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል።

አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ1400 ወደ 2000 ብር ከፍ ብሏል። በኪሎ 130 ብር ሲሸጥ የነበረ ፌሮ ብረት ፌሮ ወደ 170 ከፍ ብሏል።

በአዲስ የቤት አውቶሞቢል መኪኖች ዋጋ ላይ እንዲሁ በመቶ ሺዎች ጭማሪ መታየቱ ተገልጿል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በጅምላ ንግድ እና በግንባታ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በዶላር እና በብር መካከል ያለው የምንዛሪ ለውጥን ምን ይሆናል ብሎ መተንበይ አዳጋች በመሆኑ ሥራ መሥራት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

የግንባታ ባለሙያው ከግልም ሆነ ከመንግሥት ጋር የሥራ ውል ለመግባት የዋጋ ዝርዝር ማቅረብ አልቻልኩም ይላሉ።

“ነገ የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ስንት እንደሚገባ ማወቅ ስለማይቻል” ወጪን ገምቶ የጨረታ ሠነድ ማስገባት ከባድ ነው ብለዋል።

ብር
የምስሉ መግለጫ,ብር

አነስተኛ ሱቅ ያላቸው አንድ ቸርቻሪ ደግሞ በዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ኖሮ እንኳ ዋጋውን ጨምረው ከጅምላ ነጋዴዎች ላይ በሚፈልጉት መጠን ሸቀጦችን እያገኙ አለመሆኑን ይናገራሉ።

ነጋዴው ለዚህ ምክንያት የሚሉት የሸቀጦች እጥረት ኖሮ ሳይሆን፣ ነጋዴዎች በቀጣይ ቀናት የብር ዋጋ ሊወድቅ ስለሚችል የዕቃዎች ዋጋ ይጨምራል በሚል ሸቀጦችን እየደበቁ በመሆናቸው ነው ብለዋል።

ሸማቾች አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ የብር የመግዛት አቅም ዕለት ከዕለት እየታየ እንዳለው ከዶላር አንጻር እየቀነሰ የሚሄድ ከሆነ የሸቀጦች ዋጋም እንዲሁ እየተወደደ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በተለያዩ ሸቀጦች እና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሙስ 26/2016 ዓ.ም. የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ላይ በጽህፈት ቤታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረጉ ወቅት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ውስጥ ከልክ ያለፈ እና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ ባለሥልጣናት የማሸግ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸው ዘግቧል።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop