የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደው አዋጅ ምን ይዟል? Leave a comment

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ የሚፈቅደውን የባንክ ሥራ አዋጅ በሶስት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

አዋጁ የጸደቀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሚያደርገው ፖሊሲ በስራ ላይ እንዲውል ከወሰነ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በነሐሴ 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ነበር ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ይህን የፖሊሲ ውሳኔ ወደ መሬት የሚያወርድ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ነበር። ረቂቅ አዋጁ ከአምስት ወራት በኋላ ታኅሳስ 8፤ 2017 ዓ.ም. በፓርላማው ጸድቋል።

ትናንት የጸደቀው አዋጅ “ጥንቃቄ በተዘጋጀ የሕግ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ መሰረት የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ የዘርፉን ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት በማሻሻል ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የሚታመን” መሆኑን ያስረዳል።

በአዋጁ መሰረት “ማንኛውም የውጭ ባንክ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት” የሚይዙት ተቀጥላ፣ ውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ወይም እንደራሴ ቢሮ እንዲከፍቱ ይፈቀድላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ አክሲዮን ባለቤቶች መሆን ይችላሉ።

አዋጁ የውጭ ኢንቨስተሮች በአንድ የአገር ውስጥ ባንክ የሚይዙት የአክሲዮን ድርሻ “ከባንኩ አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታል ከአርባ በመቶ መብለጥ አይችልም” የሚል ድንጋጌ አለው።

ከዚህ በተጨማሪም የብሔራዊ ባንክ ጠቀሜታ ያላቸው ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ወይም ችግር ውስጥ ለገባ ባንክ እልባት ለመስጠት እና የፋይናንስ ስርዓቱን ለማረጋጋት ውጭ ባንኮች የሀገር ውስጥ ባንኮችን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲገዙ፤ “በልዩ ሁኔታ” ሊፈቅድ ይችላል።

አዋጁ የውጭ ባንኮች፣ ተቀጥላዎች፣ ቅርንጫፎች እና እንደራሴ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አስቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪም የቁጥጥር ስራው በምን መልኩ እንደሚካሄድ ዝርዝር ድንጋጌዎች አሉት።

በአዋጁ መሰረት “ማንኛውም ባንክ ከብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ የጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ ወይም ንዑስ ቅርንጫፍ መክፈት ወይም የተከፈተ መዝጋት አይችልም”።

አዋጁ የባንክ ቅርንጫፍ ወይም ንዑስ ቅርንጫፍ ለመክፍት እና ለመዝጋት መሟላት ያለባቸው “ዝቅተኛ ሁኔታዎች እና መስፈርቶች” በብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንደሚወሰኑ አስፍሯል።

በፓርላማው የጸደቀው አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜጎች በባንክ ስራ ላይ ስለሚሳተፉበት አግባብም ድንጋጌዎችን ይዟል።

በአዋጁ መሰረት ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆኑ የተረጋገጠ እና እንደ አገር ውስጥ ባለሃብት መቆጠር የፈለገ ግለሰብ “ኢንቨስትመንት የሚያገኘውን ማንኛውንም ክፍያ ወይም ገቢ በውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ማዛወር አይችልም”።

ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆኑ የውጭ ዜጎች “በብር የባንክ አክሲዮን ስለሚገዛበት አግባብ ወይም ባንክ ስለሚያቋቁምበት አግባብ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን” መሆኑ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።

አዋጁ በጸደቀበት ወቅት አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ መግባት በስጋት ተመልክተውታል።

ለእነዚህ ስጋቶች መልስ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ አዋጁ “የውጭ ኢንቨስተሮችን ማምጣት ግቡ [አይደለም]” ሲሉ ተናግረዋል።

የባንኩ ገዢ አክለውም “የነገሩ ውጤት እና ትርጉም የውጭ ኢንቨስተሮችን በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ ስርዓት ውስጥ ማምጣት ሳይሆን የባንኪንግ ዘርፉን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት እና ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያደርገውን አበርክቶ ለማሻሻል መስራት [ነው]” ብለዋል።

አቶ ማሞ ” [አዋጁ] አንድ ባንክ የፋይናንስ ቀውስ ሲያጋጥመው ለተከሰተው ቀውስ ብሔራዊ ባንክ የእልባት ሰጪነት ሚና [የሰጠ] ይሄን ስልጣን እና ኃላፊነት በግልጽ ያስቀመጠ የመፍትሄ ሃሳቦች እና አማራጮችን በግልጽ የደነገገ እና ብሔራዊ ባንክ እንደ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችሉትን የህግ ድንጋጌዎች ያካተተ ነው” ሲሉ የአዋጁን ምንነት አብራርተዋል።

የፋይናንስ እና ገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ የአዋጁ መጽደቅ “የውጭ ባንኮች ተሰልፈው ይገባሉ ማለት አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውንም አይተው በጣም ጥቂት ባንኮች ሊሆኑ ይችላሉ ፍላጎት የሚኖራቸው” የሚሉት ባለሙያው፤” የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም የሚያጓጓ አይደለም ለውጭ ባንክ ስፍስፍ ብለው የሚመጡ አይመስለኝም” ይላሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው ከመግባታቸው በፊት ሰፊ ጥናት እንደሚያካሂዱ ጠቁመዋል።

“እነዚህ ባንኮች ገብተው አገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮችን ይዘው የሚሄዱበት ምክንያት የለም ወደ ኪሳራ ወደ ምናምን ሊዳርጉበት የሚችሉበት ምክንያት አይታየኝም” ሲሉ ባለሙያው አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ስርዓት በትክክል ከተተገበረ “አገር ውስጥ ባንኮችን ወይም ዘርፉን ለከባድ አደጋ የሚዳርግበት ምክንያት አይታየኝም” ይላሉ።

በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ  ብቻ  ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤  ለተጨማሪ መረጃ   ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/

ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon

ምንጭ፡– (ቢቢሲ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Cart

Your Cart is Empty

Back To Shop