ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ያህል በከባድ ውዝግብ ውስጥ ከቆዩ በኋላ በቱርክ አሸማጋይነት በደረሱት ስምምነት ግንኙነታቸውን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በዚህም መሠረት መሪዎቹ ወደ አገራቱ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት እንዲሻሻል ለወራት ጥረት ያደረገችው ቱርክ ባለፈው ታኅሣሥ ወር በመሪዋ ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን አማካይነት ከስምምነት ተደርሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን አንካራ ላይ ስምምነት መፈረማቸው ይታሳል።
በስምምነቱ መሠረት የሁለቱ አገራትን ግንኙነት ለማሻሻል እና ለማጠናከር ባለፉት ወራት የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።
ይህንንም ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ ከተከሰተ በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ጥር 3/2017 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ አቅንተው የነበረ ሲሆን፣ በምላሹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የካቲት 20/2017 ዓ.ም. በሞቃዲሾ የአንድ ቀን ጉብኝት አድርገዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት ዜና መሰማት የጀመረው በዋና የሞቃዲሾ ጎዳናዎች ላይ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ሰንደቅ ዓላማዎች እንዲሁም የሁለቱ አገራት መሪዎች ፎቶ ግራፎች መሰቀል በጀመሩበት ረቡዕ ዕለት ጀምሮ ነበር።
ሶማሊያ ባለባት የደኅንነት እና የጸጥታ ስጋት ምክንያት የአገራት መሪዎች እምብዛም ለጉብኝት ወደ ማይሄዱባት ሞቃዲሾ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደሚሄዱ ሲታወቅ በርካታ የሶማሊያ መንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት ኃይሎች በከተማዋ ጎዳናዎች ከወትሮው በተለየ ተሰማርተው ነበር።
ለዚህ የደኅንነት ስጋት ምክንያት የሆነው በርካታ የአገሪቱን ግዛቶች ተቆጣጥሮ የሚገኘው እና በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው ታጣቂው ቡድን አል ሻባብ ነው።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው የሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ በታጣቂዎች፣ ተሽከርካሪ ላይ በሚጠመዱ ቦምቦች እና በተወንጫፊ መሳሪያዎች ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም የበርካታ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።
በዚህም ምክንያት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉብኝት ቀደም ብሎ የሶማሊያ ዋና ከተማ ጎዳናዎች በተለይም ከአደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አስከ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ድረስ ያለው መንገድ ዝግ ከመሆኑ በተጨማሪ ጥብቅ ጥበቃ ይደረግለት እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ምን ነበር የተከሰተው?
ሐሙስ ረፋድ ላይ ጠንካራ ጥበቃ በሚደረግለት በሞቃዲሾ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና ሌሎችም የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለመቀበል ተገኝተዋል።
በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ እና በዙሪያው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሶማሊያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተሰማሩ ሲሆን በዙሪያው ያሉ መንገዶች በሙሉ ለተሽከርካሪዎች ዝግ ተደርገው ነበር።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የሶማሊያ መንግሥትን ለዓመታት ሲጠበቅ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮችም በአውሮፕላን ማረፊያው ዙሪያ ወታደራዊ ሰፈር አላቸው።
በዚህ ሁሉ የደኅንነት ጥበቃ መካከል ግን ሐሙስ ረፋድ ላይ በርካታ የሞርታር ተወንጫፊዎች ወደ አውሮፕላን ማረፊያ መተኮሳቸውን የሶማሊያ እና ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
የቱርክ ዜና ወኪል አናዱሉ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለመቀበል በአየር ማረፊያው ሳሉ የሞርታር ጥቃቱ መፈጸሙን ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ ጨምሮም የተተኮሱት ሞርታሮች በቀጥታ አውሮፕላን ማረፊያውን የመቱ ሳይሆን በአቅራቢያው ባሉ አካባቢዎች መውደቃቸውን የደኅንነት ምንጮችን እንዳረጋገጡለት ገልጿል።
በተመሳሳይ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የሞርታር ጥቃቱ የተፈጸመው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር እና ልዑካቸው ሞቃዲሾ ደርሰው አየር ማረፊያውን ለቅቀው ከወጡ በኋላ መሆኑን ነዋሪዎችን በመጥቀስ ዘግቧል።
ኤኤፍፒ ያነጋገረው አንድ የአካባቢው ነዋሪ ሁለት የሞርታር ጥይቶች ቡሎሁቤይ ከተባለ ሰፈር ከሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ ላይ ወድቀው አንዲት በዕድሜ የገፉ ሴትን መቁሰላቸውን ተናግሯል።
በሞቃዲሾ አየር ማረፊያ የነበሩ የደኅንነት ባለሥልጣናትም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸው ከአየር ማረፊያው በመውጣት ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተመንግሥት እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት ነገር አለመከሰቱን ለዜና ወኪሉ አረጋግጠዋል።
አንድ ወደ ሞቃዲሾ ካመራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዑክ ውስጥ አባል የሆኑ ግለሰብ ለዜና ምንጩ እንደተናገሩት ቡድኑ የሞርታር ጥቃት ስለመፈጸሙ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ይህ የኢትዮጵያው መሪ በሶማሊያ ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ የተፈጸመው የሞርታር ጥቃት ከጉብኝቱ ጋር ስለመያያዙ የታወቀ ነገር የለም። ለጥቃቱም በይፋ ኃላፊነቱን የወሰደ ወገን እስካሁን የለም።
ሐሙስ ረፋድ ሞቃዲሾ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካን ቡድናቸው ከሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ከሰዓት በኋላ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት,pm office
ቱርክ፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሞቃዲሾ ጉብኝት ሁለቱ አገራት ቱርክ አንካራ ላይ የደረሱትን የትብብር ስምምነት የበለጠ ለማጠናከር እና ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው።
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው በሰላም እና በፀጥታ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በጋራ ሊሠሩ በሚችሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የአሸማጋይነት ሚና የተጫወቱት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን በቅርቡ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ጉብኝት የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ዝርዝርሩ እስካሁን ይፋ ባይሆንም፣ በሶማሊላንድ በኩል ለንግድ እና ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል የባሕር በር እንደምታገኝ በምላሹም ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና እንድምተሰጥ ሲነገር ቆይቷል።
ይህ ስምምነት ከ30 ዓመታት በላይ ነጻ አገርነቷን አውጃ የቆየችውን ሶማሊላንድ የግዛቴ አካል ናት የምትላት ሶማሊያን አስቆጥቶ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ከግዛቷ እንዲወጡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ያሏትን አምባሳደር እንድትጠራ በማድረግ ውዝግቡ ተባብሶ እንደነበር ይታወሳል።
ሁለቱ አገራት በቱርክ አማካይነት በመጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ተደጋጋሚ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው በመሪዎቻቸው አማካይነት ከስምምነት ላይ ደርሰው ወደ ግጭት ያመራል የተባለውን ፍጥጫ መፍትሄ ያበጁለት።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)