ሲሪላንካ ውስጥ የአንድ አደገኛ የወሮበላ ቡድን መሪ ፍርድ ቤት ውስጥ ጠበቃ መስሎ በገባ ግለሰብ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ፖሊስ እንዳለው ግድያው የተፈጸመው አሁን እየተፈለገች ባለች አንዲት ሴት አማካኝነት ሽጉጥ በመጽሐፍ ውስጥ ተደብቆ ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ነው።
የአደገኛው ወሮበላ ቡድን መሪ የሆነው ሳንጂዋ ኩማራ በጥይት የተመታው የቀረበበት ክስ ወደ ሚታይበት ችሎት በፖሊሶች ታጅቦ እየገባ ባለበት ጊዜ ነው።
የወሮበሎች መሪው በበርካታ የግድያ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በመከሰሱ ፍርድ ቤት መቅረቡን ፖሊስ አስታውቋል።
በሲሪላንካ ዋና ከተማ ኮሎምቦ ፍርድ ቤት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ በተቀናቃኝ የወሮበላ ቡድኖች መካከል ከሚፈጸሙ ግድያዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግሥት ባለሥልጣናት ግድያዎቹን ለማስቆም በወሮበላ ቡድኖች ላይ ዘመቻ እንደሚያካሂዱ ቃል ቢገቡም ክስተቱ እንደቀጠለ ነው።
ጋኔሙሌ ሳንጂዋ በሚል መጠሪያ በስፋት የሚታወቀው ፍርድ ቤት ውስጥ የተገደለው የወሮበላ ቡድን መሪ የሆነው ግለሰብ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በቀረበበት ክስ ተይዞ የታሰረው።
ግለሰቡ ፍርድ ቤት ውስጥ በጥይት ከተመታ በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም እዚያ እንደደረሰ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።
ጥቃት ፈጻሚው ከፍርድ ቤቱ በመውጣት ለማምለጥ ቢችልም በኋላ ላይ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ሥር ውሏል። በተጨማሪም ግድያው የተፈጸመበትን ሽጉጥ ወደ ፍርድ ቤት ደብቃ አስገብታለች የተባለችው ሴት ባትያዝም ፖሊስ ማንነቷን መለየቱ ተገልጿል።
ባለሥልጣናት ተፈላጊዋን ግለሰብ ለመያዝ የሚያስችል መረጃ ለሚሰጡ ሰዎች ሽልማት እንደሚሰጡ ማስታወቂያ እያስነገሩ ነው።
በተጨማሪም ከገዳዩ እና ሽጉጡን ወደ ፍርድ ቤቱ አስገብታለች የተባለችውን ግለሰብ ተባብረዋል የተባሉ አንድ የፖሊስ አባል እና ሹፌር በቁጥጥር መዋላቸው ተነግሯል።
በወሮበላ ቡድን መሪው ላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ግድያው በተፈጸመበት ዕለት የአገሪቱ ፓርላማ አባላት እየተባባሰ ባለው የወሮበላ ቡድኖች የወንጀል ድርጊት ላይ ሲወያዩ ነበር።
አንድ የምክር ቤት አባልም ጉዳዩ የአገሪቱ “ዋነኛ የደኅንነት ችግር” ነው ሲሉ አሳሳቢነቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ግድያው በፍርድ ቤቶች ውስጥ ባለው የደኅንነት ጥበቃ ላይ ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት በፍርድ ቤቶች ጥበቃ ዙሪያ ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል።
ግድያውን ተከትሎ አንዳንድ ተከሳሾች ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የታጠቁ ፖሊሶችን ማሰማራትን ጨምሮ በፍርድ ቤቶች አዲስ የደኅንነት ጥበቃ አሠራር ተዘርግቷል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው ሲሪላንካ ውስጥ ከሁለት ወር ባለሰ ጊዜ ውስጥ በወሮበላ ቡድኖች መካከል ባለው ባላንጣነት የተነሳ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።
በድህረ ገጻችን ኢትዮ አማዞን በመግባት የሚፈልጉትን እቃ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን የርስዎንም እቃዎች መሸጥ እንደሚችሉ ስናሳውቅዎት በደስታ ነው ። ለማስታወቂያ ወይንም ለመግቢያ ምንም ክፍያ አይጠበቅብዎትም፤ ለተጨማሪ መረጃ ድህረ ገጻችንን ይጎብ/ኙ። https://ethio-amazon.com/
ለበለጠ መረጃ ሊንኩን በመንካት የቴሌግራም ግሩፓችንን ይቀላቀሉ!https://t.me/ethioamazon
ምንጭ፡– (ቢቢሲ)