በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቆም ለመጠየቅ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሰልፍ መከልከሉ በሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ተቃውሞ ገጠመው።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ይፋዊ በሆነው የፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም አለው” ብለዋል።
ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጧቸው ቃለ ምልልስ እና በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በሚያጋሯቸው ጽሑፎች መንግሥታቸውን በመክሰስ የሚታወቁት ሚኒስትሩ ዛሬ ረፋድ ላይ ባጋሩት ጽሑፍ፣ ሰልፉ በመከልከሉ “ለመመለስ የሚከብድ ጥያቄ ሊነሳብን ይችላል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥታቸው ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በአገሪቷ ውስጥ የተከሰቱ ጦርነቶች፣ ግጭቶችን እና አፈናዎችን በማንሳትም “ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲ የከፈለውን ውድ ዋጋ አራክሰናል” ሲሉ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ኮንነዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩ ፖለቲከኞች መካከል አራቱ ሐሙስ ዕለት ኅዳር 27/ 2016 ዓ.ም በፖሊስ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ 97 ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውንም መንግሥት አስታውቋል።
አስተባባሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት “የታቀደውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማስቀረት ነው” የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ሰልፉ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች “ደም አፋሳሽ ተግባር ውስጥ” ይገኛል ያሉት የመከላከያ ሠራዊት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ጠቅላይ ጦር ሰፈሩ እንዲገባ ፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች “ያለ ምንም ምክንያት” የታሰሩ የአማራ ተወላጆች ከእስር እንዲፈቱ እና በአገሪቷ ያሉ ተፈናቃዮች “በአስቸኳይ ወደቀያቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ ያለመ መሆኑንም አስተባባሪዎቹ ገልጸው ነበር ።
ከአስተባባሪዎቹ መታሰር በኋላ ምሽት ላይ ከፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የወጣ መግለጫ ደግሞ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር በኅቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ መክሸፉን” ገልጿል።
ነገር ግን በጸጥታ ኃይሉ ከተያዙት ሰዎች መካከል አራቱ የሰልፉ አስተባባሪዎች ስለመኖራቸው መግለጫው ያለው ነገር የለም።
ዛሬ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ መቼ እንደሆነ ባይገለጽም ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ተዘግቧል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በማኅበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፣ በሰላማዊ መንገድ መቃወም ወይም መደገፍ የዴሞክራሲ ምሰሶ መሆኑን ገልጸው፣“ ኢህአዴግም ሰላማዊ ሰልፎችን ሲከልክል አምባገነን በማለት ስንከስና ስንኮንን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ ከልክለናል” ሲሉ በመንግሥታቸው የተሻለ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል።
አቶ ታዬ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ጦርነት እንዳይቃወሙ የከለከሉትን አካላት ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። አቶ ታዬ ያሉበትን መንግሥት የሚከሱ እና የሚሞግቱ ሃሳቦችን በመሰንዘር ይታወቃሉ።
ቀደም ብሎ ለቢቢሲ የኦሮምኛ ክፍል በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይም መንግሥት በሽብርተኝነት ከፈረጀው እና ሸኔ እያለ ከሚጠራው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን ጋር በታንዛንያ፣ ዳሬሰላም የተካሄደው ድርድር ላለመሳካቱ መንግሥታቸው ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል። በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቷ እየተፈጠሩ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ስጋታቸውን እንደገለጹ ያስታወሱት አቶ ታዬ፣“ ሰሚ አጥቻለሁ” ብለዋል።
አቶ ታዬ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል ሲሆኑ አገሪቷን በሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለግላሉ።